Connect with us

“የትግራይ ክልል ለድርድር ፍላጎት አላሳየም”

"የትግራይ ክልል ለድርድር ፍላጎት አላሳየም"
የክራይሲስ ግሩፕ አጥኚ ዊሊያም ዳቪሰን

ነፃ ሃሳብ

“የትግራይ ክልል ለድርድር ፍላጎት አላሳየም”

“የትግራይ ክልል ለድርድር ፍላጎት አላሳየም”

የክራይሲስ ግሩፕ አጥኚ ዊሊያም ዳቪሰን 

የዓለም አቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ ከፍተኛ አጥኚ ዊሊያም ዳቪሰን በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ክልል መካከል ያለው ውዝግብ ለመገምገም ወደ መቀለ ከተጓዘ በኋላ ለድርድር ፍላጎት እንዳለ የሚያሳይ ነገር የለም ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

በአይሲጂ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ከፍተኛ አጥኚ የሆነው ዊሊያም ዳቪሰን፤ ከሰሞኑ ወደ መቀለ ያቀናው ክልሉ ከፌደራል መንግሥት ጋር ስለገባበት ውዝግብ ያለውን አቋም ለመገምገም እና ከገቡበት አጣብቂኝ የሚወጡበትን መፍትሄው ለማፈላለግ መሆኑን ይናገራል።

በመቀለ ቆይታውም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ከበርካታ የክልሉ ኃላፊዎች ጋር መነጋገሩን የሚያስረዳው አጥኚው፤ በቆይታው ለድርድር ፍላጎት መኖሩን የሚያሳይ ነገር የለም ብሏል።

ከሁለት ወራት በፊት ዓለም አቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ (አይሲጂ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አስታራቂና የሚያቀራርቡ ንግግሮቻቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጧቸው መጠየቁ ይታወሳል።

አይሲጂ ጨምሮም በሁለቱ አካላት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ አስፈላጊ ከሆነም የአፍሪካ ሕብረት ወይም የአፍሪካ መሪዎች በማሸማገሉ በኩል ተሳትፎ ሊያደርጉ ይችላሉ ከማለት በተጨማሪ በተለይ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር የሆኑት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ከትግራይ ክልል ጋር የተከሰተው አለመግባባት “በሕግ እና ሕግ ብቻ የሚመለሰው ይሆናል” ያሉ ሲሆን የፌዴሬሽን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጡት ውሳኔ ላይ ብቻ በመመሠረት ጉዳዩ በሕግ የሚመለስ መሆኑን ተናግረዋል።

የአይሲጂ አጥኚ ዊሊያም ዳቪሰን “በክልሉ እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለው ፍጥጫ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው። በፓርቲዎቹ መካከል ያለው ትስስር እየቀነሰ ነው። የፌደራል መንግሥት የትግራይን በጀት ካቋረጠ ነገሮች ሊባባሱም ይችላሉ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ዊሊያም ጨምሮም፤ የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚሰጠውን በጀት ካቋረጠ “ክልሉ ይህንን እንደ ጦርነት ትንኮሳ እና ከፌደሬሽኑ እንደመገፋት አየዋለሁ ብሏል። ይሄም አሳሳቢ ነው” ሲል ተናግሯል።

ዊሊያም “ሁለቱም ወገኖች ወደ ጠረጴዛው መጥተው የሚወያዩበት መንገድ ማግኘት አለባቸው። ይህ ካልሆነ ቀውስ ይከተላል” ብሏል።

“በኢትጵያ ያሉ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች መወያየት ይፈልጋሉ ብዬ አስባለሁ። ብልጽግና ፓርቲ፣ የኦሮሞ፣ የሶማሌ፣ በደቡብ የሚገኙ ፓርቲዎች፣ ሕወሓትና የትግራይ ተቃዋሚዎችም መወያየት ይፈልጋሉ። ችግሩ ግን ምን አይነት ድርድር ማድረግ እንዳለባቸው፣ ግባቸው ምን እንደሚሆን፣ ቅድመ ሁኔታዎቹ ምን መሆን እንዳለባቸው የተለያየ አመለካከት ነው ያላቸው። ይህም ፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ መድረክ መጥተው ውይይት እንዳያደርጉ እክል ይሆናል” ይላል።

 በትግራይ በነበረው ቆይታ የተረዳውንም ሲያስረዳ፣ የትግራይ ክልል መንግሥት ወደ መሰል ድርድር ወይም ውይይት ሊገባ የሚችለው ጠንከር ያሉ ቅድመ ሁኔታዎች ሲጠበቁ ነው።

“ለምሳሌ ምርጫውን የሚመራ ባለአደራ መንግሥት ይቋቋም የሚል ነጥብን አላቸው። አሁን ላይ የፌደራል መንግሥቱ ወይም ገዢ ፓርቲው ይህን ቅድመ ሁኔታ የሚቀበልበት ሁኔታ ያለ አይመስልም።”

ዊሊያም በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጋር ተገናኝቶ የመነጋገር ፍላጎት ቢኖረውም እድሉ ግን እስካሁን እንዳልተመቻቸ ይናገራል።

የክራይሲስ ግሩፕ ከፍተኛ አጥኚ የሆነው ዊሊያም ዳቪሰን፣ ድርጅታቸው አሸማጋይ አለመሆኑን ይናገራል። “ሁለቱንም አካሎች የምናነጋግረው ግንዛቤያችንን ለማዳበር ነው። ትንታኔያችን የሁሉንም አካላት አስተያየት የያዘ እንዲሆን የተሟላ ጥናት እየሠራን ነው። ከዛ ምክረ ሐሳባችን ለሁሉም አካል ትርጉም የሚሰጥ ይሆናል” ብሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ሕውሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል አለመግባባቶች እየተካረሩ መጥተዋል።

ባለፈው ዓመት ለማካሄድ ታስቦ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ስርጭት ስጋት እንዲራዘም ተደርጎ የትግራይ ክልል የራሱን ክልላዊ ምርጫ ማከናወኑ በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን ውጥረት ከፍ አድርጎታል። (BBC)

ፎቶ፡- የክራይሲስ ግሩፕ አጥኚ ዊሊያም ዳቪሰን

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top