Connect with us

ትራምፕ የቻይና ባንክ ሒሳብ ደብተር ተገኘባቸው

ትራምፕ የቻይና ባንክ ሒሳብ ደብተር ተገኘባቸው
BBC Amharic news

ዜና

ትራምፕ የቻይና ባንክ ሒሳብ ደብተር ተገኘባቸው

ትራምፕ የቻይና ባንክ ሒሳብ ደብተር ተገኘባቸው

የአሜሪካ ኩባንያዎች ወደ ቻይና መሄዳቸውን ክፉኛ በመተቸት የሚታወቁት ዶናልድ ትራምፕ እሳቸው ራሳቸው በቻይና የባንክ የሒሳብ ደብተር እንዳላቸው አመኑ።

ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እንዳጋለጠው ትራምፕ የባንክ ደብተሩን ለትራምፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል ማኔጀመንት የከፈቱት ሲሆን ከእአአ 2013 እስከ 2015 ግብር እንደተከፈለበትም ያሳያል።

የትራምፕ ቃል አቀባይ ደብተሩ የተከፈተው በእሲያ የሆቴል ልማት ያለውን እድል ለማየት ሲባል እንጂ በሌላ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል። ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ኩባንያዎች ወደ ቻይና መትመማቸውን ለዓመታት ሲተቹ የኖሩ መሪ ናቸው።

የዚህ የቻይና ባንክ ሒሳብ ደብተር መገኘት ወደፊት የሚያስተቻቸው ይሆናል።

ኒው ዮርክ ታይምስ የትራምፕን የግብር ወረቀቶች ማግኘቱን ተከትሎ ነው የባንክ አካውንት ደብተሩን ይፋ ያወጣባቸው።

ዝነኛው ጋዜጣ ኒው ዮርክ ታይምስ ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ ትራምፕ እጅግ አነስተኛ ግብር እንደከፈሉ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በዚህ ጋዜጣ ልዩ መረጃ መሰረት ቢሊየነሩ ዶናልድ ትራምፕ የሚከፍሉት ግብር ከአንድ የመንግሥት ሰራተኛ እንኳ ያነሰ ነው።

ቢሊየነሩ ትራምፕ በ2016 እና በ2017 ለፌዴራል የከፈሉት የገቢ ግብር 750 ዶላር ብቻ መሆኑን ኒው ዮርክ ታይምስ ማጋለጡ ይታወሳል። ይህ ትራምፕ በቻይና ባንክ የከፈቱበት የሒሳብ ደብተር 188ሺ ዶላር ግብር ተከፍሎበታል።

ትራምፕ ተቀናቃኛቸው ባይደንን ለቻይና ይራራል፣ የቻይና አሻንጉሊት ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ይተቻሉ። በተለይም የባይደን ልጅ ሀንተር ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት በማንሳት ትራምፕ ጆ ባይደን ላይ የሰላ ትችት ሲሰነዝሩ ነበር።

አለን ጋተር የትራምፕ ድርጅት ጠበቃ ናቸው። የዶናልድ ትራምፕ የቻይና የሒሳብ ደብተር ጋር በተያያዘ በሰጡት አስተያየት የባንክ ሒሳቡ የቻይና ቢሆንም ግብር ለአገር ውስጥ ስንከፍልበት ነበር ብለዋል።

ጠበቃው እንደሚሉት የቻይና ባንክ አካውንቱ አሁንም ድረስ ያለ ቢሆንም እንቅስቃሴ ግን ተደርጎበት አያውቅም። ቢሊየነሩ ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በባህር ማዶም በርካታ የንግድ ተቋማት በስማቸው ይገኛሉ።

በተለይም በስኮትላንድና አየርላንድ ባለ 5 ኮከብ ቅንጡ ሆቴሎችና የጎልፍ ሜዳዎች ባለቤት ናቸው። ኒው ዮርክ ታይምስ እንደሚለው ትራምፕ የብሪታኒያ፣ የአየርላንድና የቻይና የባንክ ሒሳብ ደብተሮች አሏቸው።

ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ኩባንያዎች ቢዝነሳቸውን ከቻይና እንዲያስወጡ የግብር እፎይታ እሰጣለሁ ሲሉ ነበር። ትራምፕ ኩባንያዎቻችንን ከቻይና ወደ አገር ውስጥ በማምጣት በ10 ወራት ውስጥ 10 ሚሊዮን የሥራ እድሎችን እፈጥራለሁ ሲሉ ዝተዋል።

ኒው ዮርክ ታይምስ ባወጣው ዘገባ ግን ትራምፕና ድርጅታቸው ለበርካታ ጊዜ በቻይና ንግድ ለመስራት ሙከራ ያደርጉ ነበር። በሻንጋይም ቢሮ ከፍተዋል።

የግብር ወረቀቶች እንደሚያሳዩትም 192ሺ ዶላር የሚያወጡ ትንንሽ ኢንቨስትመንቶችን ትራምፕና ድርጅታቸው የጀመሩት በቻይና ፕሮጀክቶችን ለማግኘት ነበር። (BBC)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top