ክቡር አቶ ለማ ዛሬ ከዶክተር አብይ ጎን ብንሆንም ከጎናችን ሆነው አምባገነኑን ሥርዓት ስለገረሰሱት ውለታዎን አንረሳም፤
ዶክተር አብይን የሰጡን እርስዎ ነዎት ዛሬ ስፍራችንን አለቀቅንም ዛሬም የሰጡንን ስጦታ አክብረን አብረን እየተጓዝን ነው፡፡ እስከ ቀራንዮ! | ከሰለሞን ክብረት
የአቶ ለማ መገርሳ ከኦሮሚያ ብልጽግና መሰናበት ወይም መታገድ ሰበር ዜና አይደለም፡፡ ሰውዬው አስቀድመው መደመር አለመፈለጋቸውን በመግለጽ ከብዙ የመደመር ደጋፊዎች ልብ ተቀንሰዋል፡፡ ቀጥሎ የሚሆነውን ሲጠብቅ ለነበረ የሰውዬው ደጋፊ እንዲህ በለየለት አግባብ ከብልጽግና ተለይተዋል የሚለውን ሲሰማ የሚሰማውን ስሜት ብንረዳም ዛሬ የዶክተር አብይ ደጋፊዎች ከአቶ ለማ መገርሳ መንገድ ተለይተናል፡፡
መንገዳችን ለየቅል ቢሆንም ትናንትናን አንረሳውም በተለይም አስከፊውን የአንድ ቡድን ሥርዓት በመገርሰስና በብሔር ስም ኮንትሮባንድ ውስጥ ተዘፍቆ ኪሱን ያደልብ የነበረ አፋኝን በማስወገድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በዛሬው አቋምዎት የሚሻር ወይም የሚረሳ አይደለም፡፡ ትናንትን ስናስብ እርስዎ ባለውለታችን መሆንዎን አንረሳም፡፡
እምቢ ማለትን አሳይተዋል፤ ነጻ የመውጣት አብዮት ሲፈነዳ እሳቱን የለኮሱት ቤንዚሉን ያርከፈከፉት አጋዚን ያጋለጡት አንድነትን የሰበኩት መቼም በማንም የሚረሳ ተጋድሎ አይደለም፡፡ የዛሬው አቋምዎት የትናንት ውለታዎትን አያደበዝዘውም፣ አያጠፋውም፡፡ ሁሌም ስምዎት ሲነሳ ያለ ጥይት ጥይት ማስወረድዎትን፣ ያለ ደም መፋሰስ ቤተ መንግስት ዲሞክራሲ ማስገባትዎትን እናስበዋለን እናወድስዋለን፡፡
ቀሪው የሰው ድክመት ነው፤ ዛሬ መንገዳችን ተለያይቷል፡፡ ትንናንት አብረን ነን ካሉን ጓድዎት ጋር አብረን ዘምረንላችኋል፡፡ ዶክተር አብይን የሰጡን እርስዎ ነዎት ዛሬ ስፍራችንን አለቀቅንም ዛሬም የሰጡንን ስጦታ አክብረን አብረን እየተጓዝን ነው፡፡ እስከ ቀራንዮ!
ጸሐፊው አርብ ሲሆን መከራው ይበዛል እንዳለው ሁሉ እኛ ትንሳኤውን አስበን ስቅለቱን እንውለዋለን፡፡ ዛሬ ሞት መከራ ስደት ብጥብጥ ከኢትዮጵያ ምድር አልጠፋም፤ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚያስቡ ሰዎች ብዙ ምኞት ብዙ ስቃይ እያሳየን ነው፤ እንሻገራለን ያሉንን አምነን በዚህ ሁሉ ስቃይ ውስጥ የመሻገር መንፈስን የተሞላን ነን፡፡
ሙሴ ተብለው ነበር፤ ግጥሙና ዜማው በስምዎት ጎርፏል፡፡ ያ ሁሉ አብረን ስንጓዝ የሆነ አብረን መንገድ እንድንጀምር ለከፈሉት መስዋዕትነት የተከፈለ ነው፡፡ ዛሬ ትናንት አይደለም፤ ትናንት የሰሩትን የምንረሳ የዛሬ ሰዎች አይደለንም፡፡ ዛሬ መንዳችን ቢለያይም የትናንቱን ውለታዎን ግን በክብር ጽፈነዋል፡፡ አምባገነን ያስተነፈሰ፣ ስደተኛ ለሀገሩ ያበቃ፣ ዲሞክራሲ እንዲወገግ ያደረገ አስተዋጽኦ አይረሳም፡፡