የደብረብርሃን ከተማ ኢንቨስትመ ንት ፍሰት በ2011 በጀት ዓመት ከነበረበት 10 ቢሊዮን ብር ወደ 17 ቢሊዮን ብር ማደጉን የደብረብርሃን ከተማ ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ለዓመታት መሬት አጥረው ወደ ልማት ካልገቡ ባለሃብቶች 80 ሄክታር መሬት ተመላሽ በማድረግ ለአልሚዎች ተላልፏል።
የደብረብርሃን ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃን ገብረሕይወት በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለፁት፤ የደብረብርሃን ከተማ በፈጠነ መልኩና አገራዊ ፋይዳቸው የጎላ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መዳረሻ እየሆነች መምጣቷን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ባለሃብቶች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰሳቸው ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አብራርተዋል።
በ2011 ዓ.ም 11 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት መሳቡን ያስታወሱት አቶ ብርሃን፤ በ2012 በጀት ዓመት የሦስት ቢሊዮን ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ ሲሰራ ቢቆይም 17 ቢሊዮን ብር ፈሰስ ያደረጉ 270 ኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን አረጋግጠዋል። በበጀት ዓመቱም 112 የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ፍሰቱ ከፍተኛ ስለነበር ከእቅዱ በላቀ መልኩ 270 የኢንዱስትሪ ፈቃዶችን መሠጠቱንም ኃላፊው ገልፀዋል። ከኢንቨስተሮችም መካከል 85 ከመቶ የሚሆኑት የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ናቸው ተብሏል።
አቶ ብርሃን እንዳሉት፤ በአካባቢው 76 አዋጭና ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ የኢንቨስትመንት አማራጮች በጥናት ተለይተዋል። የመሬት አቅርቦቱ ደግሞ ለምግብና ምግብ ነክ፣ ለጋርመንትና ጨርቃጨርቅ፣ ኬሚካልና ኢንዱስትሪዎች ብሎም እንጨትና ብረታ ብረት በሚል አራት ክላስተሮች የተደራጀ ሲሆን፤ ይህም ባለሃብቶች ሥራቸውን በተቀላጠፈ መንገድ ለማከናወን ብሎም የሚመለከታቸው አካላትም ለቁጥጥር እንዲያመች ታስቦ የተደራጀ ነው።
ኃላፊው እንዳብራሩት፤ በክላስተር የተደራጀ የመሬት አቅርቦት መኖሩ፤ የአካባቢው ማህበረሰብ ለኢንቨስትመንትና ለኢንቨስተሮች ንብረት ጥበቃና ከለላ በመሆን ከመንግሥት ጋር ጠንካራ ትብብር መፍጠሩ፣ ከተማዋ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት መገኘቷ፣ ምቹ የአየር ንብረትና ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸው፣ ቢሮክራሲ የበዛባቸውና የተንዛዙ አሠራሮች መቃለላቸው፣ በአካባቢው በየዓመቱ በአማካይ 10ሺ በላይ ሰዎች የሚመረቁ መሆናቸውና ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን የተማረ የሰው ኃይል ማግኘታቸው ለኢንቨስትመንቱ ማደግ ትልቅ አበርክቶ አድርገዋል።
አንድ ባለሃብት የሚጠበቅበትን መስፈርት ካሟላ ከሦስት ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መሬት ይሰጣል ያሉት አቶ ብርሃን፤ የኢንቨስትመንት መምሪያ ባለሙያዎች እሁድና ቅዳሜን ጨምሮ ሣምንቱን ሙሉ እንደሚሰሩና በተለይም እሁድና ቅዳሜ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ባለጉዳዮችና ባለሃብቶች እንደሚስተናገዱም ገልፀዋል።
(ኢፕድ)