Connect with us

‹‹ሙሌቱ ኢንቨስተሮች ከፍተኛ የሞራል ስንቅ ይሆናል›› አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ

‹‹ሙሌቱ ለነባርም ሆነ ለአዳዲስ ኢንቨስተሮች ከፍተኛ የሞራል ስንቅ ይሆናል›› አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ
Photo: Ethiopian Press Agency

ኢኮኖሚ

‹‹ሙሌቱ ኢንቨስተሮች ከፍተኛ የሞራል ስንቅ ይሆናል›› አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ኢንቨስተሮች ፕሮጀክቶቻቸውን እንዲያስፋፉና አዳዲሶቹም ወደ አገሪቱ እንዲያማትሩ ከፍተኛ የሞራል ስንቅ እንደሚሆን ጀግናው አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረ ስላሴ ተናገረ፡፡

ሙሌቱን አስመልክቶ የጋዜጣው ሪፖርተር ያነጋገረው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማራው ጀግናው ሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ፣ ህዳሴ ግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት የታላቅ ድል መጀመሪያ ነው፣ በተግባሩም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል›› ብሏል፡፡

የውሃ ሙሌቱ የኤሌክትሪክ ሃይል ማግኘት ፈተና በሆነበት አገር በተለይ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ለቀጣይ ስራዎች ስንቅና ማበረታቻ እንደሚሆን ያመላከተው ሃይሌ፣ የሙሌቱ ብስራት ‹‹ነገ ኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ የሃይል ችግር ፈተና ሆኖ እንዳይቀጥልና እኔ እና ሌሎችም በርካታ ኢንቨስተሮች ካለ ጭንቀት በልበ ሙሉነት ስራችንን እንድንቀጥል መተማመኛ የሚለግስ ነው›› ብሏል።

አገሪቱም የውስጥ ፍላጎትን ከማርካት በተጓዳኝ በሽያጭ መልክ ለሌሎችም እንድትተርፍና ተጠቃሚነቷን እንድታጎለብት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

‹‹እንደ አንድ የአትሌቲክስ ስፖርተኛ በጥሩ ብቃት ከአንድ ኦሎምፒክ ወደ ሌላ ኦሎምፒክ ከአንድ ድል ወደ ሌላ ድል፣ ከአንድ ክብረ ወሰን ወደ ሌላ ክብረ ወሰን መተላለፍ አለብን›፣ ህዳሴ ላይ የፈፀምነው ገድል መንደርደሪያችን እንጂ መቋጫችን ባለመሆኑ በተግባሩ ሳንኩራራ ሁለተኛውንም ሶስተኛውንም ሙሌት ማፋጠን እና እስከመጨረሻው በመዝለቅ በሙሉ አቅም ኤሌክትሪካችንን ማመንጨት ይገባናልም›› ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በህገወጦች የሚፈፀሙ ተግባራት መሰል የደስታ ዜናዎችን እንደሚያደበዝዙ የጠቆመው ሃይሌ፤ የህገወጦቹ ተግባር የአገሪቱን ገፅታ የሚያበላሽ በተለይ ኢንቨስተሮችን ተስፋ የሚያስቆርጥ እንደመሆኑ ሊታረም እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡

መንግስትም በህገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩትን በቃችሁ በማለት ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ መፈፀም እንዳለበት አፅንኦት የሰጠው ሃይሌ፤ ይህ እስካልሆነም ግድቡን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች ኪሳራ እንደሚሆኑ መረዳት አግባብ መሆኑንም አመላክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚከሰት ሁከት ለጥፋት ከመነሳት ይልቅ ቆም ብሎ የሚያስብና “ለምን” የሚል የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የሚያወድም ሳይሆን የራሱ መሆኑን በመረዳት የሚጠብቅና የሚንከባከብ ትውልድ መፍጠር እንደሚያስፈልግም አፅንኦት ሰጥቶታል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ትሩፋት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ የሚያደርግና ጥቅሙም ለመቶና ለሁለት መቶ አመት የሚዘልቅ እንደመሆኑ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚሉ አንዳንድ አካላትም በዚሁ አቋማቸው ዙሪያ ቆም ብለው ማሰብ እንደሚገባቸውም አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያውያን የጋራ አሻራ የሆነውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ መደገፍ የምርጫ ሳይሆን የግዴታም ጉዳይ በመሆኑ ከቀደመው በበለጠ የሁሉም ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበትና ህዝቡም ሆነ ባለሀብቶች የጀመሩትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸውም አትሌት ሃይሌ ጥሪ አቅርቧል፡፡

አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2012
ታምራት ተስፋዬ

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top