ብርሃነ መስቀል የወሰዱት የህዝብ ንብረትን በጫና መለሱ
(ታምሩ ገዳ)
በአሜሪካ አገር፣በሎሳንጀለስ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጄኔራል የነበሩት ዶ/ር ብርሃነ መስቀል አበበ ሰኚ ከኃላፊነት ከተነሱ በሁዋላ ወዲያውኑ ማስረከብ የነበረባቸው የኢምባሲው መኪናን ክብርቱ ጉትጎታ በሁዋላ እንዲመልሱ መደረጋቸው ታወቀ።
ከቆንጽላ ጄኒራል ሀላፊነት ከተነሱ ከሶስት ወራት በላይ ያስቆጠሩት ብርሃነ መስቀል ለመንግስት እና ለህዝብ አገልግሎት ይጠቀሙበት የነበረው ማርቸዲስ የ2019 እኤአ ሞዴል መኪናን እንዲያስረክቡ ተደጋጋሚ ጥሪዎች ቢደረግባቸውም “አሞኛል፣፣አልተመቸኚም፣ከከተማ ውጪ ነኝ..ወዘተ” የሚሉ መሰል ምክንያቶችን ሲያቀርቡ መክረማቸውን የገለጹት የህብር ራዲዮ ምንጮች ሁኔታው ተካሮ ከአሜሪካ የአገር ውስጥ ጉዳይ ክፍል(ሆምላንድ ሲኪዊሪቲ) እና የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስተር ከዘለቀ በሁዋላ ሰሞኑን በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር ወደ ቆንጽላ ጽ/ቤቱ ፖሊሶች በመጡበት ወቅት ብርሃነ መስቀልም በሚገርም ሁኔታ መኪናውን ይዘው መጥተው ማስረከባቸውን ለጉዳዩ ቅርበትነት ያላቸው በውጪ ጉዳይ የህብር ራዲዬ ታማኝ ምንጮች አረጋግጠዋል።
ብርሃነ መስቀል አበበ ሰኚ ፣የአሜሪካ ዜግነት ይዘው በዝቅተኛ የጽ/ቤት ስራ ላይ መስራት ሲገባቸው ፣በከፍተኛ ኃላፊነት ማእረግ ሲሰሩ እንደነበር እና ይህም ሹመት እና አሰራር ትልቅ ስህተት እንደ ነበር የሚገልጹት የቅርብ ምንጮቹ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተቃጣው ግድያን ተከትሎ በተነሳው የፖለቲካ ቀውስ እና አለመረጋጋት ላይ “የዘር ተኮር ጭፍጨፋ እንዲካሄድ በአደባባይ ሲቀሰቅሱ” እንደነበር የገለጹት እነዚሁ ምንጮች የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት የሆነው የኢምባሲ መኪናን ሳይመልሱ ለወራት ከተገለገሉ በሁዋላ ሰሞኑን መመለሳቸው ጠቀማቸው እንጂ ከሰሞኑ የቅስቀሳ ዘመቻቸው ጋር ተዳምሮ እራሳቸውን ለከፋ አደጋ ሊዳርጉ ይችሉ እንደነበር ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ፍጹም አረጋ ሰሞኑን በአሜሪካ እና በተለያዩ አገራት ቁጭ ብለው በአገር ቤት የዘር ጭፍጨፋ እንዲካሄድ የሚያቀነቅኑ ወገኖች ከእኩይ ተግባራቸው በአስቸኳይ ካልተቆጠቡ በእያሉት አገራት የጸረ ጥላቻ ቅስቀሳ ህግ እና ደንብ ለፍርድ የሚቀርቡበት እርምጃ እንደሚወስድ ሰሞኑን ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም።