የፌዴሬሽን ምክርቤት በሕገመንግሥት ትርጉም ጉዳይ ነገ ውሳኔ ይሰጣል
~ አዲስ አፈጉባኤ ሊመርጥ ይችላል፣
~ በሲዳማ የክልልነት ሕዝበ ውሣኔ ጉዳይ ይወስናል፣
የፌዴሬሽን ምክርቤት ከሕገመንግሥት አጣሪ ጉባዔ የቀረበለትን የሕገመንግሥት ትርጉም የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ለማሳለፍ ነገ ረቡዕ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ስብሰባ መጥራቱ ተሰማ።
የም/ቤቱ ምንጮች በተለይ ለድሬቲዩብ እንደገለፁት 153 አባላት ያሉት የብሄር ብሄረሰቦች ውክልና ያለው የፌደሬሽን ምክርቤት ሕገመንግሥታዊ ትርጓሜውን ረቡዕ ዕለት ካፀደቀ በሀላ ሐሙስ ዕለት ከህዝብ ተወካዮች በጋራ በመሰብሰብ ያፀድቁታል ተብሎ ይጠበቃል።
ይኸንኑ የሕገመንግሥት ትርጉም ሒደት ኢ- ሕገመንግሥታዊ ነው በሚል በይፋ ተቃውመው በትላንትናው ዕለት ከኃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ያሳወቁትና ከሚያዝያወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ የተሾሙት የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሂም ምትክ ምክር ቤቱ ነገ ዕረቡ አዲስ አፈጉባኤ ይሾማል ተብሎ እንደሚጠበቅም ምንጫችን ፍንጭ ሰጥቷል።
የትግራይ ክልል በፌዴሬሽን ምክር ቤት ያለው ውክልና ስምንት መቀመጫ ብቻ ነው። ምንጫችን እነዚህ ተወካዮች ህወሓትን ሙሉ በሙሉ ቢደግፉ እንኳን የሕገመንግሥት ትርጉሙ በአብላጫ ድምፅ ስለሚወሰን መፅደቁ እንደማይቀር ምንጫችን ጠቁሞ የአፈጉባኤዋ ከስብሰባው ቀደም ብሎ ከኃላፊነት የመልቀቅ ውሳኔ ሳልቀደም፣ ልቅደም አይነት ይመስላል ብሏል። ምክንያቱም በእሳቸው መድረክ መሪነት እያንገሸገሻቸውም ቢሆን አጀንዳው በአብላጫ ድምፅ መፅደቁ አይቀርምና ይህንን ሁኔታ ቁጭ ብለው ላለማየት ሲሉ ቀድመው ለመልቀቅ ሳይወስኑ እንዳልቀረ ምንጫችን ግምቱን አስቀምጧል።
የአፈጉባኤዋ መልቀቅ የህወሓትን ፍላጎት ከማስፈፀም ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነው ያሉት ምንጫችን ይኸን ደግሞ የምክርቤቱ አባላት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በነገ ዕለት በሚካሄደው ስብሰባ ላይ የሚያሳርፈው አንዳችም አሉታዊ ተፅዕኖ አይኖርም ብለዋል።
በተያያዘ ዜና በቅርቡ በሕዝበ ውሣኔ ክልል ይሁን የተባለውን የሲዳማ ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክርቤት የፊታችን ዕረቡ ተመልክቶ ውሳኔ ያሳልፋል ብሏል ምንጫችን።
የኢፌድሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት የብሄር ብሔረሰቦች ውክልና የያዘ እና በጠቅላላው 153 አባላት ያሉት ምክርቤት ሲሆን በአንድ ሚልየን የሕዝብ ቁጥር የተሰላ አንድ መቀመጫን የያዘ ነው። በዚህ መሰረት በደቡብ ክልል ካሉ ከ56 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች 67 መቀመጫ፣ ኦሮምያ 31፣ አማራ 29 ሲሆን የትግራይ ክልል ስምንት መቀመጫ እንዳለው ይታወቃል።