Connect with us

የ40/60 የቤት ዕድለኞች አስተዳደሩ ቤታቸውን ባለማስረከቡ …

የ40/60 የቤት ዕድለኞች አስተዳደሩ ቤታቸውን ባለማስረከቡ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ገለፁ
Photo Facebook

ዜና

የ40/60 የቤት ዕድለኞች አስተዳደሩ ቤታቸውን ባለማስረከቡ …

18 ሺህ 576 የ40/60 የቤት ዕድለኞች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ውል አስረው የአስር ወራት ክፍያ ቢፈፅሙም እስከ አሁን ቤታቸውን የአስረከባቸው አካል እንደሌለና ለከፋ የኢኮኖሚ ችግር እየተጋለጡ መሆኑን ተናገሩ።

ቅሬታ አቅራቢ የሁለተኛው ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባለዕድለኞችም ከነሐሴ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ውል በመግባት ወርሐዊ ክፍያ መጀመራቸውን ገልፀዋል። ይሁን እንጂ ለአስር ወራት ክፍያ ቢፈፅሙም እስካሁን የከተማ አስተዳደሩ ቤታቸውን እንዳለስረከባቸው ጠቅሰው ይህም በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ የይኢኮኖሚ ጫና እያደረሰባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በሃያት ሁለት ባለሁለት መኝታ ቤት የደረሳት ወይዘሪት ሰላማዊት ውቤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገረችው፤ ባለፈው ነሐሴ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውል በመግባት የአርባ በመቶ ክፍያውን ከመስሪያ ቤቷ የቁጠባ ተቋም ብድር በመውሰድ በየወሩ 3 ሺህ 173 ብር ትከፍላለች። በተጨማሪም የቤቱን ዕዳ በመክፈል ኑሮዋን ከዘመድ ጋር በጥገኝነት አድርጋ ለተደራራቢ ወጪ መዳረጓን ገልፃለች። ይህም በኑሮዋ ላይ ጫና እንደፈጠረባት መሆኑን ተናግራለች።

አስተዳደሩ የቤቱን ግንባታ ሳይጠናቀቅ ውል በማስገባት ክፍያ እንዲፈጽሙ ማስገደዱን የምታነሳው ወይዘሪት ሰላማዊት፤ ቤቱን ሳያስረክብ ወለድ ማስከፈል ተገቢ እንዳልሆነ ገልፃለች። በዚያ ላይ ውል ከተገባው እስከ ሁለት እጥፍ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉና የእፎይታ ጊዜም አለመኖሩ ለባለድለኞች አስቸጋሪ ሆኗል ትላለች። ከምንም በላይ ግን እየተቸገረችበት ያለው የከተማ አስተዳደሩ ቤት ሳያስረክብ ወርሃዊ ክፍያ ማስከፈሉ ሲሆን፤ መንግሥት በአስቸኳይ ይህንን ችግራቸውን ሊፈታላቸው እንደሚገባ አበክራ ትናገራለች።

በቱሪስት መገናኛ የባለሁለት መኝታ ባለዕድለኛው አቶ አዳነ አወቀ በበኩላቸው፤ ውል ከገቡ በኋላ ለደረሳቸው ቤት በየወሩ 3 ሺህ 500 እንዲሁም ለመኖሪያቸው ቤት ኪራይ 4 ሺህ 500 ብር እየከፈሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የአራት ቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸውም የተናገሩት አቶ አዳነ አወቀ ቤቱን ሳይረከቡ እንዲከፍሉ መደረጋቸው ከፍተኛ ጫና እንደሆነባቸው አስረድተዋል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ዕጣ ሲወጣ ግድግዳቸው ያልተከፈሉ ቤቶች መኖራቸውን ያነሱት አቶ አዳነ፤ መሰረተ ልማቱና የቤቶቹ ሥራ ሳይጠናቀቅ ውል አስገብቶ ገንዘብ ማስከፍል ከሞራልም ከህጋዊነትም አንፃር አግባብነት የሌለውም ይላሉ።

በአስኮ ሳይት የቤት እድለኛው ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ አቶ እስጢፋኖስ ዘኪሮስ ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ ባለተረከቡት ቤት በየወሩ 2 ሺህ 973 ብር እየከፈሉ መሆኑን ተናግረዋል። ቤቱ የግድግዳ ግርፍ፣ መፀዳጃ ቤት፣ የመሠረተ ልማት፣ የበርንዳና ሌሎች ሥራዎቹ ያልተጠናቀቀ መሆኑን ገልፀው የከተማ አስተዳደሩ ዕጣ ማውጣትና ቤቱ ሳይጠናቀቅ ውል ማሰሩ ተገቢ አለመሆኑን አመልክተዋል። ይህም የቤት እድለኞችን ከዕቅዳቸው ውጭ በኢኮኖሚ ጫና እንዲጎዱ አድርጓል። በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ ቤቱን በፍጥነት አጥናቆ ማስርከብ አለበት ብለዋል።

በመገናኛ ቱሪስት ባለሁለት መኝታ እድለኛው አቶ ማለደ ዋሲሁን በበኩላቸው፤ የ40/60 የቤት ፕሮግራም ከግንባታ እስከ ዕጣ አወጣጡ አወዛጋቢ መሆኑን አንስተው መንግሥት በቃሉ መሠረት ቤቶቹን ሠርቶ ማስረከብ አልቻለም ይላሉ።

ከግንባታው ማዕቀፍ ውጭ መንግሥት ባለአራት መኝታ ግንብቶ አስረክቧል። የቤቱ ስፋት ካሬውም በተመሳሳይ ደረጃ የተለያየ ነው። ዕጣውን ለመውጣት የክፍያ መጠኑ አወዛጋቢ ነበር። ዕጣው ወጥቶ ውል ከታሰረም በኋላ ለአስር ወራት አስተዳደሩ ቤት ሳያስረክብ ገንዘብ በመሰብሰብ ዜጎችንም ችግር ላይ ጥሏል። ይህ ደግሞ ለዜጎች አለማሰብ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

በአጠቃላይ የቤት ፕሮግራሙ በመመሪያና በደንብ የማይመራ፤ ለመንግሥትም ባዕድ ፕሮጀክት ነው። ተጠያቂነትም የለም። ለበርካታ ዓመታት ተገንብተው የተወሰነ ደረጃ ከደረሰ በኋላ ሳይጠናቀቅ በማቆም የአገር ሀብት እየባከነ መሆኑን ጠቅሰው ዜጎችም በቤት እጦት እና በተለያየ የዕዳ ክፍያ በኢኮኖሚ ጫና እየተሰቃዩ ይገኛሉ ብለዋል።

ለዝግጅት ክፍላችን በቀረበው ቅሬታ ዙሪያ ምላሽ ለማግኘት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወይዘሪት የንጋትኮከብ ምላሽ ለመስጠት በተደጋጋሚ ቃል ቢገቡም ለሦስት ሳምንት ያህል የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር በአካልም ሆነ በተደጋገሚ የስልክ ግንኙነት መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በቀጣይም የሚሰጡን ምላሽ ካለ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን እንገልፃለን።

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም የወጣ ሲሆን፤ ባለአንድ መኝታ 3 ሺህ 60፣ ባለሁለት 10 ሺህ 322 እና ባለሦስት መኝታ 5 ሺህ 194 በድምሩ 18 ሺህ 576 መሆናቸው ይታወሳል።

(አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2012)

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top