በሕዝብና በወላጆቹ የተሠጠውን ሥም ማስቀጠል የቻለው ታማኝ በየነ
አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ
ያለፈው ሥርዓት ከሥልጣኑ ይወገድ ዘንዳ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ካፈሰሱ ሰዎች መሃከል ታማኝ በየነ ዋነኛው ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ያደረገውን ነገር ሁሉ እንደ ዜግነት ግደታ እንጂ እንደ ውለታ ስለማይቆጥረው ‹‹እኔ ባመጣሁት ለውጥ›› እያለ መታበይ አያውቅበትም፡፡ ‹‹እውቅና ካልተሰጠኝ›› ወይንም ደግሞ ‹‹ካልተዘመረልኝ›› ብሎ አይጨነቅም፡፡
አገሩ በምትፈልገው ሰዓት ላይ ቀድሞ ይደርሳል፡፡ ‹‹አስፈላጊ አይደለሁም›› ብሎ በሚያምንባቸው ነገሮች ላይ ደግሞ ጸጥ ብሎ መኖር ይችላል፡፡
ታማኝ በየነ የቀድሞው ሥርዓት እንደተወገደ ሰሞን ወደናፈቀችው አገሩ መጣና ‹‹ይህ ለውጥ ሳይቀለበስ ወደ ትክክለኛ የዲሞክራሲ ጎዳና ይገባ ዘንድ ከወንድሜ ጃዋር ጋር አብሬ ለመሥራት ዝግጁ ነኝ›› የሚል የአብረን እንሥራ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡
አቦ ጃዋር ግን ለዚህ ወንድማዊ ጥሪ የሰጠው መልስ ጥያቄው ከቅንነት የመነጨና የዘገየ መሆኑን ገልጾ ‹‹አሁን እኮ ትግሉን ጨርሰን ወደ ተቋማት ግንባታ ገብተናል›› የሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡ በትህትና የቀረበለትን ጥያቄ የመለሰው በትዕቢትና በሹፈት ቋንቋ ነበር፡፡
የሆነው ሆኖ ታማኝ የአርበኝነት ፉክክር ውስጥ አልገባም፡፡ ከመጀመሪያውም ቢሆን ጥያቄው ለውጡን ለማስቀጠል እንጂ የለውጡን ባለቤትነት ለመካፈል አስቦ ያቀረበው ስላልነበር የነገሮች አካሄድ አልጥመው ሲል ራሱን ከፖለቲካው ገለል አድር መኖር ጀመረ፡፡
በሌላ መልኩ ግን ‹‹ትግሉን ጨርሰናል›› ባዩ ኦቦ ጃዋር አሁንም ትግል ላይ ነው፡፡ እንደውም ‹‹ሠራሁት ያለሁት ካልኩሌተር ባግባቡ እየደመረ አይደለም›› በሚል ምክንያት ኦፊኮን ተቀላቅሎ ደማሪውን ለማስወገድ 24/7 ጠንክሮ እየሠራ ነው፡፡
ታማኝ እራሱን ከፖለቲካው አግልሎ በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ሲሰማራ ይሄኛው ግን አሁንም ድረስ የቁልቁለት መንገድ ላይ ነው፡፡ ለማስረጃም ያህል ታማኝ ለጌድዮ ተፈናቃዮች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በጎፈንድሚ ሰብስቦ ለወገን ደራሽ መሆኑን ሲያሳይ ኦቦ ጃዋር ግን ሲያሻው ቤተክርስቲያን ገብቶ አደረጃጀት በመስራት፣ ሲያሻው ተከብቤያለሁ በሚል ጥሪ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ሲያደርግ ሰንብቷል፡፡
ባሁኑ ሰዓት ደግሞ ታማኝ ከኮሮና ክስተት ጋር ተያይዞ ‹‹ግሎባል አሊያንስ›› በተባለ ድርጅቱ ሥም በሰበሰበው ገንዘብ ለጤና ባለሙያዎችና ለዜጎች አገልግሎት የሚውሉ የህክምና ቁሳቁሶችን በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ እኒህም የሕክምና መሳሪያዎች በ11.5 ሚሊዮን ብር የተገዙ ሲሆን ቁሳቁሶቹንም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ በተገኙበት አስረክቧል፡፡
‹‹ትግሉን ጨርሰን ወደ ተቋማት ገንባታ ገብተናል›› ያለው አካል ግን ከኮሮና ክስተት በላይ የሚያሳስበው ነገር የምርጫው መዘግየት ሆኗል፡፡ በመሆኑም ይህ በሽታ በአገር ኢኮኖሚና በዜጎች ሕይወት ላይ ከደቀነው አደጋ ይልቅ ቤተ-መንግሥት የመግባቱ ጉዳይ እረፍት ነስቶት ‹‹ኮሮና አምሥት ዓመት የቆየ እንደሁ ብልጽግና ያን ያህል ጊዜ ሥልጣን ላይ ሊቆይ ነወይ?›› የሚል ጥያቄ በማንሳት ተጠምዷል፡፡ ከዚህም አልፎ ‹‹ምርጫው ካልተደረገ ወይንም ደግሞ የሽግግር መንግሥት ካልተመሠረተ ከመስከረም ሰላሳ በኋላ የገዥው ፓርቲ ቅቡልነት ያበቃል›› እያለ የመንግሥትን ቅቡልት አደጋ ውስጥ ለመክተት ደፋ ቀና እያለ ነው፡፡
ሐሳቤን ጠቅለል ሳደርገው ለዚች አገር በብዙ መልኩ መልካም ነገር ማድረግ ይቻላል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲም ሆነ የገዥው ፓርቲ አመራር በመሆን፣ ወይም ደግሞ እንደ ታማኝ ገለልተኛ ሆኖ በራስ ሥም በመንቀሳቀስ ወገንን ማገልገል ይቻላል፡፡
በሌላ መልኩ ግን ተቃዋሚ ሆኖ አራት ኪሎ መግባት የሚፈልግ አካል ሁሌ የመንግሥትን ስህተት እየዘረዘረ ከመተቸት ባለፈ የእራሱን ታላቅነት ማሳየት ቢችል አገሩንም እራሱንም ይጠቅማል፡፡
ኮሮናን እና የምርጫ ጊዜ ማለፍን ተገን አድርጎ የመንግሥትን ስልጣን ለመቆናጠጥ ከማሰብ ይልቅ ኢትዮጵያም ሆነች ሕዝቧ ይሄን ወረርሽኝ ያልፉ ዘንዳ የግልን አስተዋጾ ማድረግ ሥኬታማ ያደርጋል፡፡ ከሥልጣን በፊት መልካም ሥም መትከል ይበጃል፡፡
ከዚህ ውጭ ግን አገሪቷንም ሆነ ሕዝቡ እረስቶ ቤተ-መንግሥቱ ላይ ትኩረት ማድረግ የመንግሥትን ሥልጣን ከማራዘም ውጭ ፋይዳ የለውም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ሕገ-መንግሥቱን ለመተርጎምና ሥልጣኑን ለማራዘም አቅዶ ሲንቀሳቀስ ከባድ ተቃውሞ ያልገጠመው አገሪቷን በትክክለኛ መንገድ ላይ እየመራ ነው ተብሎ በመታመኑ ሳይሆን ከተረካቢው ይልቅ ሥልጣን ላይ ያለው የተሻለ መሆኑ ስለተረጋገጠ ነው፡፡