የኢትዮጵያውያኑ ሰቆቃ ከወደ ቤይሩት!!
(ታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ)
ኢትዮጵያዊቷ ሶፊያ የእራሳቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን ህይወትን ለመቀየር ወደ ቤይሩት፣ሊባኖስ ከተጓዙ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ ለፍቶ አዳሪዎች መካከል አንዷ ነች። ይሁን እንጂ ለወትሮውም የሰብአዊ መብት በእጅጉ የሚረገጥባት ቤሩት ፣በዘመነ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ነገሮች በእጅጉ የከፋባት ለመሆኑ የተለያዩ ዘገባዎች ይናገራሉ።
የፈረንሳይ የዜና አገልግሎት፣ኤኤፍ ፒ ያነጋገራት ሶፊያ”ቀጣሪዬ/ማዳም ለስድስት ወራት ከአስራ አምስት ቀናት የሰራሁበትን የላቤን ዋጋ ሳትከፍለኝ፣ፓስፖርቴን እና ሻንጣዬን ሳትስጠኝ ወደ ጎዳና ላይ ካባረረችኝ ሳምንት አልፎታል፤ አሁን የምፈልገው ነገር ቢኖር ወደ አገሬ መመለስ ብቻ ነው”ስትል ሰኞ እለት ከኢትዮጵያ ቆንስላ ደጃፍ ላይ ተኮልኩለው ወደአገራቸው ለመመለስ ከሚጥብቁት እርሷን መሰል እህቶች ጋር ተቀላቅላ ቀጣዩ ለመመዝገብ ትጠባበቅ ነበር።
ሊባኖስ የውጪ ዜጎች አገሯን ለቀው እንዲወጡ የአየር ግዛቷን በእሮብ ለኢትዮጵያዊያን እህቶች እና ግብጻውያን ወንዶች ልዩ ፍቃድ ብትሰጥም ሁለት ልጆቿን ላለፉት ሶስት አመታት ያላየችው ሶፊያ የእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ብትጥርም የአገሪቱ የጥበቃ ሰራተኞች ከዘጠኝ ቀናት በኋላ እንዲመለሱ ቀጣሪዎቻቸውም የትራንስፖርት ወጪያቸውን እንዲከፍሏቸው በመግለጸ ሸኝተዋቸዋል ።
ከቀጣሪዎች መካከል አንዷ የሆኑት ኢቫ አዎድ በሰጡት አስተያየት “ሰራተኛዬን ከዚህ በኋላ የምከፍላት ገንዘብ ስለማይኖር አልፈልጋትም ፣የቀረ ደሞዟን ግን እከፍላለሁ ” በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል። ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የገባችው ሊባኖስ አንዳንድ ቀጣሪዎች እንደወትሮው በዶላር መክፈል ትተው በአገሬው ገንዘብ ለመክፈል ተገደዋል።ከዚያም የከፋ ችግር የገጠማቸው አሰሪዎች እንደ ሶፊያ የመሰሉ ምስኪን ሰራተኞችን ወደጎዳና ላይ አውጥተው እንደሚጥሏቸው ዘገባው አክሎ ገልጿል።
በዚህ አስከፊ ወቅት ለኢትዮጵያውያን እህቶች ምንም አይነት አለማቀፋዊ እና መንግስታዊ እገዛ የማያገኙ ሲሆን በቤይሩት የሚገኘውም የኢትዮጵያ ቆንጽላ በችግረኞች መጨናነቁ ተደምሮ ለቀረበለት ተደጋጋሚ ጥሪ “ምላሽ አልስጠንም “ብሏል ኤኤፍ ፒ።ሶፊያ ለጊዜው በአንዲት የአገሯ ልጅ እገዛ ጎዳና ላይ ከመቅረት የዳነች ብትሆንም ቀጣዩ እጣ ፈንታዋን ግን በጭራሽ አታውቀውም።
ባንቺ ይመር ትባላለች። በአንድ ወቅት አንደ ሶፊያ ወደ ቤይሩት ተጉዛ እድል ቀንቷት ወደ ካናዳ በመሻገር በአሁኑ ወቅት “እኛ ለእኛ/ Egna Legna association/” ግብረ ሰናይ ድርጅት በማቋቋም ሶፊያን የመሰሉ ብዛት ያላቸው የወረርሽኙ ኢኮኖሚያዊ ተጠቂ ወገኖችን ለመርዳት እሷ እና ጓደኞቿ ከአስራ ሁለት ሺህ ዶላር በላይ በማሰባሳብ መሄጃ ላጡ ከአንድ መቶ በላይ ወገኖች እና መሰል እህቶች የምግብ እና የመጠለያ እገዛ እያበረከቱ ሲሆን የችግረኞቹ ብዛት፣ከኢትዮጵያ ቆንስላ ደጃፍ በቀጣሪዎቻቸው እንደ እቃ እየተወረወሩ የሚጣሉ በርካታ የአገሯ ልጆች ሁኔታ ትልቅ ስጋት እንደፈጠረባት ባንቺ ይመር “ሁኔታው በእጅጉ እንቅልፍ ነስቶኛል ” ስትል ትናገራለች።
በወረርሽኙ ሳቢያ ካለፈው ሚያዚያ /አፕሪል27 አንስቶ እስከ መጪው ሰኔ 8 /2020 እኤአ የሚጽና የእንቅስቃሴ እገዳ የጣለችው ሊባኖስ ዘጠኝ መቶ አስራ እንድ ተጠቂዎች እና ሃያ ስድስት ሰዎች የሞቱባት ሲሆን ወረርሽኙ ባሳደረው ተጽእኖ ሳቢያ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ስራ አጥ በመሆናቸው በእነርሱ ስር የነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩት ኢትዮጵያዊያን እህቶች እና ከመሰል አገራት የመጡ ለፍቶ አዳሪዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን፤ በቅርቡ ሁለት ቀጣሪዎች ሰራተኞቻቸውን በፌስ ቡክ አማካኝነት ለሽያጭ ማቅረባቸው እና ድርጊቱን ከፍተኛ አለማቀፋዊ ቁጣ መቀስቀሱ አይዘነጋም።