ለግብር ከፋዮች የታክስ እዳ ምህረት ተደረገ
…
ከግብር ጋር በተያያዘ የተላለፉ ውሳኔዎች በተመለከተ የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫቸውም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የሚኒስተሮች ም/ቤት የወሰነውን ውሳኔ መሰረት ተደርጎ የወጣው መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ይጀመራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሰረት የግብር ዕዳ ምህረት ማድረግ፣ የመከፈያ ጊዜ ማራዘምና የሚከፍሉትን ማበረታታት የተመለከቱ ውሳኔዎች ከዛሬ ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በየቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ተግባራዊ ይደረጋል፡፡
የግብር ዕዳ ምህረት፣ የመክፍያ ጊዜ ማራዘምና የሚከፍሉትን ማበረታታት በሁለት ምድብ ተከፍሎ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን የመጀመሪያው ምድብ እስከ 2007 ዓ.ም ወይም የገቢ መከፍያ ጊዜያቸው እ.አ.አ እስከ 2014 የሆነ መቀጫ፣ ፍሬ ግብርና ወለድን ጨምሮ ሙሉ ሙሉ እንዲነሳላቸው ተደርጓል፡፡
በሁለተኛው ምድብ ከ2008-2011 ዓ.ም ወይም እ.አ.አ ከ2015-2018 ያለው ጉዳያቸው የታየው በሶስት ዓይነት ሲሆን የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ የደረሳቸው ግብር ከፋዮች መቀጫ፣ ፍሬ ግብርና ወለድ ያለባቸው ከሆነ የፍሬ ግብሩን 25 በመቶ በአንድ ወር (ከዛሬ ሚያዝያ28-ግንቦት 28) ጊዜ ውስጥ ከፍለው 75 በመቶውን በአንድ ዓመት እንዲከፍሉ የተወሰ ሲሆን የዚህ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች መቀጫና ወለድ እንዲነሳላቸው ተወስኗል፡፡
በሌላ በኩል በአንድ ወር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ፍሬ ግብሩን ለሚከፍሉ 10 በመቶ ከፍሬ ግብሩ ተቀንሶላቸው መቀጫና ወለድም እንዲቀርላቸው ተደርጓል፡፡ በሁለተኛው ምድብ ውስጥ ገቢያቸውን አስታውቀው የከፈሉ ነገር ግን በተቋሙ ኦዲት ተደርጎ የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ ያልደረሳቸው ግብር ከፋዮች በ30 ቀናት ውስጥ በኦዲት የተገኘውን የፍሬ ግብር 25% ቅድሚያ በመክፈል ቀሪውን 75 % በአንድ ዓመት ውስጥ ለመክፈል የክፍያ ጊዜ ውል ተፈራርሞ በውሉ በተገለፀው ጊዜ ውስጥ ከፍሎ ካጠናቀቀ ቅጣትና ወለድ የሚነሳ ሲሆን በአንድ ወር ውስጥ የፍሬ ግብሩ 100 % ለመከፈል የሚስማማ ወለድና ቅጣት ከማንሳት በተጨማሪ ከፍሬ ግብሩ 10% ይቀነስላቸዋል፡፡
ሌላው ገቢን አሳውቀው ክፍያ ያልጀመሩትን የሚመለከት ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ አሳውቀው ከከፈሉ በተመሳሳይ የምህረቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ውሳኔው ተፈፃሚ የሚሆነው ግብር ከፈዮች የጀመሩትን የታክስ ይግባኝ ወይም በየደረጃው ያሉ ክርክሮችን ካቋረጡ እና በውሳኔው መስማማታቸውን ግብር ለሚከፍሉበት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሲያመልክቱና ሲያሳውቁ ነው፡፡
ሌላው በመግለጫው ወቅት በታክስ ዕዳ ምክንያት የተያዘ ንብረት የሚመለስበትም አግባብ የተገፀ ሲሆን ንብረቱ ተመላሽ የሚሆነው ንብረቱ ለሶስተኛ ወገን ያልተላለፈ ከሆነ፣ ድርጅቱ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ መኖሩ ሲረጋገጥ እና ንብረቱ ተንቀሳቃሽ ከሆነ ዋስትና አቅርቦ መጠቀም እንደሚችልም ተገልአፆል፡፡
ውሳኔው የተወሰነበት ዓላማ በኮቪዲ-19 የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ በመደጎም ግብር ከፋዮች ወደ ንግድ እንቅስቃሴ ገብተው የምርትና አገልግሎት አቅርቦት እንዲሳለጥ ለማድረግ፣ ድርጅቶች ሰራተኞቻቸውን በስራ ላይ እንዲያቆዩ እና ግብር ከፋዮች ቫይረሱን ለመከላከል ለሚደረገው እንቅስቃሴ የጀመሩት ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ነው፡፡
(የገቢዎች ሚ/ር)