ይድረስ ለኢ/ር ታከለ ኡማ ~ በነካ እጅዎ መንግሥትዎንም ይማፀኑልን?
ክቡር ከንቲባ፤ ሠላምታዬ ባሉበት ይድረስዎ!!
የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ ሆይ፤ የኮሮና ወረርሽኝ ( የኮቪድ 19) በኢትዮጵያ መከሰት ተከትሎ በማህበረሰብ ውስጥ የመተሳሰብ፣ የመደጋገፍ ባህል እንዲሰፍን በማሰብ በቀና ልቦናዎ እያደረጉ ያሉትን መጠነ ሰፊ ጥረት በማየቴ በእውነቱ ደስ መሰኘቴን ልነግርዎ እፈልጋለሁ። ካከናወኑት ተግባራት መካከል ቤት አከራዮች የኪራይ ዋጋ እንዲቀንሱ ወይንም የተወሰኑ ወራት በነፃ እንዲተው፤ የግል ት/ቤቶች እንዲሁ ወርሀዊ ክፍያ የመጠየቁን ነገር እንዲያስቡበት መማፀንዎ በእውነቱ ለህዝቡ ያልዎትን ቀናኢነት ስለሚያሳይ በበጎ መልኩ የምወስደው ነው።
ክቡርነትዎ፤ ይህን ወገናዊ ጥሪዎን አክብረው የቤት ኪራይ ዋጋ የቀነሱ ወይንም የተወሰኑ ወራትን ለመተው የወሰኑ አከራዮች ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣት የእርስዎ ተማፅኖ ፍሬ በመሆኑ ሊኮሩ ይገባል።
ክቡርነትዎ፤ ይኸም ሆኖ ግን እንደጥያቄ አንስቼ ማለፍ የምፈልገው አንድ ትልቅ ነጥብ አለ። በዚህ መልክ የግብር ከፋዩ ገቢ ሲቀንስ የመንግሥት የግብር ገቢም እንደሚቀንስ ልብ ብለውታል ወይ የሚለውን ነው። የመንግሥት ገቢ መቀነስ ጋር ተያይዞ እንደገና ነገ ተነገ ወዲያ የከተማው ህዝብ እንዳይጎዳ ምን ታስቧል የሚለው እንደአንድ ዜጋ አሳስቦኛል። ለዚህም ግን መላ እንደማያጡለት ስለማምን ብዙ ከማውራት ተቆጥቤአለሁ።
ክቡር ከንቲባ ሆይ፤ እንዲያው በነካ እጅዎ የሚከተሉትን ጉዳዮች መንግሥትዎን እንዲማፀኑልን ሳሳብዎ በታላቅ አክብሮት ነው። ያው በአሁን ሰዓት የግሉ ዘርፍ ህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ጫና እንዲካፈል ደጋግመው በመወትወትዎ ፈጣንና አኩሪ ምላሽ እያገኙ ነው። ነገር ግን መንግሥትዎስ የህዝቡን ሸክም በማቃለል ረገድ ምን እየሰራ ነው? በግሉ ዘርፍ ያደረጉት ሁሉ የሚደነቅ ሆኖ ሳለ ነጋዴ መንግሥትዎን በተሳሳይ ሁኔታ የህዝቡን የወጪ ጫና እንዲያቃልል እንዲወተውቱልን የምናስታውስዎ በታላቅ አክብሮት ነው።
ክቡርነትዎ፤ ያው እርስዎም እኛም እንደምናውቀው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ በአለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ አሽቆልቁሏል። ነገርግን ዋጋ በአለም አቀፍ ደረጃ ዋጋ ሲጨምር ፈጥኖ የሚጨምረው መንግስታችን ጉዳዩን ባላየ አልፎታል። የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ በዚህ ወቅት እንዲቀንስ ቢደረግ የትራንስፖርትና ተያያዥ ዘርፎች ዋጋ ሊቀንስ፣ ሊረጋጋ እንደሚችል ለእርስዎ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል።
በተጨማሪ እንደኢትዮ ቴሌኮም ያሉ መንግሥታዊ ተቋማት በኮቪድ 19 ምክንያት ቤቱ እንዲቀመጥ ለተገደደው ህዝብ የኢንተርኔት ተደራሽነትን ለማሳደግ እና የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማሳለጥ በድምፅም ሆነ በዳታ ቋሚ ወይንም በፓኬጅ መልክ ጊዜያዊ የዋጋ ቅናሽ እንዲያደርግ ቢያመላክቱልን እጅግ አድርገን እናመሰግንዎታለን።
በተመሳሳይ ሁኔታ የአዲስአበባ የውሀና ፍሳሽ መ/ቤት የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ከማሻሻል ጎን ለጎን የታሪፍ ቅናሽ ሁኔታ የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስድ ከሚመለከተው አካል ጋር እንዲመክሩልን እናስታውሳለን።
የፌደራሉም ሆነ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ለግብር ከፋዮች በዚህ ክፉ ወቅት ሊኖር የሚችለውን የንግድ መቀዛቀዝና መቆም ግምት ውስጥ ያስገባ የታክስና ግብር ቅነሳ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ቢመካከሩልን ስንል ጥያቄያችንን እናቀርባለን።
ባንኮችም የተበዳሪዎቻቸውን ቢያንስ ወለዱን እንኳን በመተው ይኸን ክፉ ጊዜ በመተጋገዝ ማለፍ እንዲቻል እንዲማፀኑልን ማስታወስ እንፈልጋለን።
ክቡርነትዎ፤ ይኸንንም አሳክተው እንደሚያስደምሙን እናምናለን።
ፈጣሪ የመጣብንን መቅሰፍት በጥበቡ ይመልስልን!!
አክባሪዎ:- ጫሊ በላይነህ