Connect with us

ይድረስ ለክቡር ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ

ይድረስ ለክቡር ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ
Photo: Facebook

ጥበብና ባህል

ይድረስ ለክቡር ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ

ይድረስ ለክቡር ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ

ልምከርዎ?!….የፕረስ ሴክሬቴሪያት ቢሮዎን እንደገና በብቃት ያደራጁ!

የህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል አስመልክቶ በቅርብ ከተቀሰቀሰው ውዝግብ ጋር ተያይዞ በሁለቱ አገራት መካከል ከፍተኛ ውጥረት መንገሱ የሚታወቅ ነው፡፡ አሁን ባለንበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት የግብጽ መንግሥትና መገናኛ ብዙሃን በሚገርም ሁኔታ እየተናበቡ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ለእነሱ በሚበጅ መረጃ እያጥለቀለቁት ሲሆን በአንጻሩ በኢትዮጵያ በኩል ግን ችግሩን የሚመጥን መልስ የሚሰጥ የህዝብ ግንኙነት ሥራ እየተከናወነ አለመሆኑ ያሳዝናል፤ ያሳስባልም፡፡

ሌላው ቀርቶ በአገር ቤት ያሉ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙሃን አንድ ወጥ በሆነ መልክ ተከታታይ መረጃዎች ከመንግሥት እያገኙ አለመሆኑ ያስደነግጣል፡፡ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ከተደራዳሪ አባላት እና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቃለመጠይቅ መልክ በግል ከሚያገኙት የተበጣጣሰ መረጃ በስተቀር ይህ ነው የሚባል ተከታታይነት ያለው የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አለመከናወኑ እንደአንድ ዜጋ ያሳስበኛል፡፡

ክቡር ጠ/ሚኒስትር በቢሮዎ የፕረስ ሴክረቴሪያት የሚባል መኖሩን አውቃለሁኝ፡፡ ግን ይህ ክፍል ቀደም ሲል የመንግስት ኮምኒኬሽን ይባል የነበረውን መ/ቤት ሲያከናውን የነበረውን ሩብ ያህል ሥራ የማያከናውን፣ ሹመኞቹም ቢሆኑ ራሳቸውን እንደአንድ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሳይሆን እንደባለሥልጣን የሚያዩ፣ መረጃ ከመስጠት ይልቅ መረጃ የሚያፍኑ ስለመሆናቸው ባለፉት ጊዜያት በደንብ የታዘብነው ጉዳይ ነው፡፡

ክቡር ጠ/ሚኒስትር እንደአንድ ተራ ዜጋ እና የአገሩ ጉዳይ እንደሚመለከተው ሰው በባለሙያዎች የተዋቀረ የፕረስ ሴክረቴሪያት በፍጥነት እንዲያዋቅሩ እመክርዎታለሁ፡፡ በተጨማሪም በፕረስ ሴክረተሪያት ውስጥ የሚመደቡ ሰዎች ሙያንና ብቃትን ብቻ መሠረት አድርገው ቢመደቡ የኮምኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ሥራ በዕውቀት እንዲመራ ይረዳዎታል፡፡ እንዲህ እንደህዳሴ ግድብ ዓይነት ወጣሪ መረጃዎች በሚያስፈልጉበት ወቅት በየቀኑ የተደራጀ መረጃ የሚሰጥ፣ የግብጽ ባለሥልጣናት እና ሚዲያዎች እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በአረብኛ እና በሌሎች ቋንቋዎች የሚሰጡትን ቃለምልልሶች እና ተያያዥ መረጃዎች በፍጥነት ሞኒተር የሚያደርግ የተደራጀና 24 ሰዓት የሚሰራ ከፍል ማደራጀት ለነገ የሚባል አይሆንም፡፡ በተጨማሪም በማህበራዊ ድረገጾች፣ በሜይንስትሪም ሚዲያዎች በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በሶማሌኛ፣ በአረብኛ ፣ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በመሳሰሉ ዓለም የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አቀፍ ቋንቋዎች በብቃት የሚጽፉ፣ ሁነቶችን የሚተነትኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ እየወጡ ስለህዳሴ ግድብ በቂ የሆነ መረጃ ሊሰጡ የሚችሉ ባለሙያዎችንም በፕረስ ሴክረቴሪያት ውስጥ ማደራጀት ይገባል፡፡

ክቡር ጠ/ሚኒስትር ሆይ፤ በአሁኑ ወቅት በግብጽ ሚዲያዎች ተበልጠናል፡፡ በፕሮፖጋንዳው በመሸነፋችን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለግብጾች ከንፈሩን እየመጠጠ ነው፡፡ የራሳችን ሐብት በሆነው የህዳሴ ግድብ ግብጾች በኢትዮጵያ እንደተበደሉ ሆነው እያስተጋቡ ያሉትን የተሳሳተ መረጃ ተከታታሎ ማረም የሚቻለው በተደራዳሪ ቡድኑ ጥቂት አባላት ወይንም በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ብቻ በገጠመኝ በሚሰጥ መረጃ ሊሆን አይችልም፡፡ እናም በፍጥነት የፕረስ ሴክሬቴሪያቱ በብቃት እንዲደራጅ በማድረግ ኢትዮጽያውያን ባለሙያዎች በአገራቸው ጉዳይ የድርሻቸውን እንዲወጡ በሩን ይክፈቱ፡፡

ስላዳመጡኝ አመሰግንዎታለሁ፡፡

አክባሪዎ ጫሊ በላይነህ

Click to comment

More in ጥበብና ባህል

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top