Connect with us

ሱስ በወጣቶች ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ

ሱስ በወጣቶች ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ
Photo: Facebook

ጤና

ሱስ በወጣቶች ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ

ሱስ ስንል ማንኛውም ነገር በሰዎች ላይ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥገኝነት ስሜት በመፍጠር ሰዎች ለመነቃቃት፣ ድብርትን ለማስወገድ፣ ጀብዱ ለመሥራት፣ ህመምን ለማስታገስና ከፍተኛ የደስታ (Euphoria) ስሜትን ለመጎናጸፍ ብለው የሚያጨሷቸው፣ የሚቅሟቸው በአፍንጫ የሚስቧቸውንና በደም ስር የሚወስዷቸውን ነገሮች በሙሉ ያካትታል።

ያለ እነኚህ ሱሶች/ዕፆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴአቸውን ማከናወን ሲሳናቸው ሱስ ወይም የሱሰኝነት ጠባይ እንዳላቸው ይገለጻል፡፡ ሰዎች ከላይ ከተገለጹት ዕውነታዎች በተጨማሪ ሱስ የሚያሲዙ ነገሮችን በተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀማሉ፡፡ ከእነኚህም የጓደኛ፣ የቤተሰብና የአካባቢ ተጽንኦ እንደ ዋንኛ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ እንደ ቀልድ አንድ ብለው የጀመሩት ሲውል ሲያድሩ አንድ የህይወታቸው አካል ይሆንና ህይወታቸውን በማመሰቃቀል እስከ ህይወት ህልፈት ሊያደርሳቸው ይችላል፡፡

በተለይ ሱስ አምራች ኃይል በሚባሉት ወጣቶች ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ወጣቶች ያሏት እንደመሆኗ ወጣቱ በሱስ የተያዘ ከሆነ የአገሪቱ መጻኢ ዕድል የተንሰራፋ ድህነት፣ ኋላ ቀርነት፣ ወንጀልና ለሀገር ሸክም የሚሆን ዜጋ ስለሚኖር በቀጣይ ጤናማ ትውልድ ማፍራት አዳጋች ይሆናል፡፡ ወጣቶች ለረጅም ጊዜ በሱስ ውስጥ የሚኖሩ ከሆነ ብዙ ችግሮችና ተግዳሮቶች በፊታቸው ይደቀኑባቸዋል፡ ፡ ከዚህ የሚከተሉት ነጥቦች ወጣቶች ሱስ ውስጥ በመግባታቸው ምክንያት የሚከሰቱ ተጽዕኖዎችን ለአብነት ያህል እንመለከታለን፡፡

ትምህርት

በተማሪ ወጣቶች ላይ የውጤት ማሽቆልቆል፤ ከትምህርት ቤት መቅረትና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ አለመሆን፤ እንዲሁም ትምህርት ማቋረጥ፤ በሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ናቸው። ይህም የሚሆንበት ምክንያት አደንዛዥ ዕፅና ሱሰኝነት በአዕምሯቸውና በጠባያቸው ላይ በሚያሳድረው ተጽእኖ ትምህርታቸውን በትኩረት መከታተል እንዳይችሉ ስለሚያደርጋቸው ነው፡፡

አካላዊ ጤና

አብዛኛውን ጊዜ በከተማዎች አካባቢ የሚታዩት አደጋዎች (ለምሳሌ የመኪና)፤ የአካል ጉዳትና የተለያዩ በሽታዎች (ተላላፊ በሽታዎች ኤች አይቪ/ኤድስን የመሳሰሉት) በወጣቶች ላይ የሚከሰቱት በሱስና አደንዛዥ ዕፅ ምክንያት የሚከሰቱ የጤና እክሎች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ማታ ማታ ከሚደርሱት / ከሚያደርሱት/ የመኪና አደጋዎች ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት የቤት አውቶሞቢሎች ሲሆኑ ለአደጋውም መንስኤ ጠጥቶ ማሽከርከር ነው። አብዛኛውን ጊዜ አሽከርካሪዎቹም ወጣቶች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በንብረት ላይ ጉዳት ከማድረስ ባሻገር ለአካል ጉዳተኝነትና ለሞት የተጋለጡ ናቸው፡፡

አዕምሯዊ ጤና ድብት (depression)

የዕድገት ውስንነት፣ ተስፍ መቁረጥ፣ መገለል፣ ስነ-ልቦናዊና ማኅበራዊ ችግሮች ከሱሰኝነት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አላቸው፡፡ በሱስ የተጠመዱ ወጣቶች ከሱስ ነፃ ከሆኑ ወጣቶች ጋር ሲነጻጸሩ ለተለያዩ የአዕምሮ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ድብርት፣ አስቸጋሪ ጠባይ፣ የስብዕና መቃወስ፣ እራስን ለማጥፋት ማሰብና መሞከር እንዲሁም ማጥፍት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ሱስና አደንዛዥ ዕፅ የወጣቶችን የማስታወስ ስርዓትና ከዚህ ቀደም በቀላሉ የሚያከናውኗቸውን ስነ-ልቦናዊና አካላዊ ክህሎቶችን ያዛባል፡፡

ጓደኝነት

በሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ከጓደኞቻቸው ወይም አቻዎቻቸው መገለል ይገጥማቸዋል፡፡ እንዲሁም በሱስ የተያዘ ጠባያቸውን በመመልከት ማኅበረሰቡ የተለያዩ አካባቢያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሌሎችንም ያበላሻሉ ብሎ በማሰብ እንዳይሳተፉ ይከለክሏቸዋል። ይህም ለለውጥና እራሳቸውን ለመቀየር ያላቸውን መነሳሳት ያኮላሸዋል፡፡

ቤተሰባዊ

ሱሰኝነት ከግላዊ ተግዳሮቶች ባሻገር በቤተሰብ ህይወት ውስጥ ትልቅ ችግር ይፈጥራል፡፡ በተለይ በወንድምና እህቶች ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል አይደለም፡፡ ወንድማቸው/እህታቸው ወይም አንድ የቤተሰብ አካል በሱስ መጠመዱ በጓደኞቻቸውና በማኅበረሰባቸው ውስጥ ከመልካም ቤተሰብ እንዳልመጡ አድርጎ ስለሚመለከታቸው ከሌላው ጋር ማኅበራዊ መስተጋብር ለመፍጠር ይሸማቀቃሉ። እራሳቸውንም ያገላሉ፡፡ በተጨማሪም የቤተሰብን ስሜትና ኢኮኖሚአዊ አቅም ይፈታተናል፡፡

ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮት

በሱስ ለተጠመዱ ወጣቶች የሚወጣው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ወጪ ቀላል አይደለም፡፡ በሱስ በመጠመዳቸው ምክንያት እራሳቸውን ማስተዳደር ስለማይችሉ በሌሎች ላይ ጥገኛ ይሆናሉ፡፡ ከፍ ሲልም የሚያገኙትን ገንዘብ ሁሉ ሱሳቸውን ለማስታገስ ይጠቀሙበታል። ያን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ወደ ወንጀል ሊሰማሩ ይችላሉ፡፡ ይህም በመሆኑ ከእዚህ ህይወት ውስጥ እንዲወጡ የሚደረገው እገዛና የህክምና ዕርዳታ ቀላል የማይባል ወጪ ያስወጣል፡፡

የወጣት ጥፋተኝነት (Delinquency)

ዕድሜቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ወንጀል ቢሠሩ እንኳን ወንጀለኞች ሳይሆን ወጣት ጥፋተኞች ነው የሚባሉት፡፡ ማንኛውም ሰው ሊክደው የማይችል የወጣት ጥፋተኝነትና ሱስ ግንኙነት አላቸው፡፡ በሱስ ምክንያት ወጣቶች የተለያዩ ጥፋቶችን ሲያጠፉ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው ተመርምሮ ጥፍተኛ ሆነው ከተገኙ ወደ ወጣቶች ተሐድሶ ማዕከል እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ ሱሰኝነት ወጣት ጥፋተኝነትን፤ ወይም ወጣት ጥፋተኝነት ሱሰኝነት አያስከትልም። ነገር ግን አንዱ የአንዱ ምክንያትና ውጤት መሆን ባይችሉም ቁርኝነት አላቸው። በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ወንጀል፤ ማኅበራዊ ቀውሶች፤ ሴተኛ ወይም ወንድ አዳሪነት ከሱስ ጋር የመያያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011

Continue Reading
Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top