ወንድና ሴት በፍቅር ሲወድቁ እርስ በእርስ ፍላጎት ማሳየታቸው አይቀርም። የሚያሳዩት ፍላጎት ግን ለእህልና ውሃ ካላቸው ፍላጎት ፍፁም የተለየ ነው። ሰዋዊ ፍትዎት ሁለት አይነት መከሰቻዎች አሉት። አንዱ የፍቅር መግለጫ ሆኖ የሚከሰተው የወሲብ አይነት ነው። ሁለተኛው ከፍቅር የተፋታው “የፍትዎት መቋመጥን” የሚያመላክተው ነው። አንድ ሰው ለምግብና ለመጠጥ የሚያሳየውን ምኞት ወደ ፆታ ፍላጎት ቀይሮ በሰው ላይ ከደገመው ያ ለፍትዎት መቋመጥን ያመላክታል። ፍፁም የራስ ወዳድነት ተግባር እንደሆነ ልብ ማለት ያሻል። ፍቅርን ተንተርሶ የሚከሰተው ወሲብ የነፍስና የስጋ ጥምረት ያለበት ፍፁም ንፁህ ተግባር ነው። በተፋቃሪዎች መተዋወቅ፣ መግባባት፣ መተሳሰብና ራስን አሳልፎ መስጠት ውስጥ የሚገለጠው ፍቅርን ተንተርሶ የሚከሰተው ወሲብ ነው ።
“ከመውደድ” እና “ከመፈለግ” የትኛው ይቀድማል? ተብለን ብንጠየቅ ምላሽ አይኖረን ይሆናል። እንደዚሁም ምኞት በፍቅር ላይ ያብባል ወይስ ፍቅር ምኞትን ያስከትላል? ብንባልም ቁርጥ ያለ መልስ ሊኖረን አይችል ይሆናል። ደግሞም ያዳግታል፤ ነገር ግን ግሪካዊው ፈላስፋ አርስቶትል ከሁሉም በፊት ቅንነት ይቀድማል ይላል። እንደ ሲግመንድ ፍሮይድ አባባል ከሆነ ደግሞ ፆታዊ ምኞት ፆታዊ ፍቅርን ያስከትላል ይላል፡፡ ሌሎቹም ሌላ ይላሉ። የጥያቄው ተመሳሳይ ምላሽ ማጣት አንድ ነገር እንድንጠረጥር ያደርገናል። እሱም ፍቅር ተወጥኖ በተግባር ሲፈፀም የተለያየ እውን የመሆኛ መንገድ እንዳለው። በወሲብ የተጀመረ ፍቅር እድሜው አጭር ሲሆን፤ ፍቅር ሲቀድም ግን የተሻለ መረጋጋት የሚታይበት መሰረት የያዘና ፍሬያማ አንድነት ይኖረዋል።
ጉዳዩን በጥልቀት የተመለከቱ የስነልቦናና የስነ-አእምሮ ምሁራን ያረጋገጡት ብዙውን ጊዜ የፆታ ፍቅርና ፍትዎት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ነው። ታዋቂው የስነ አእምሮ ምሁር ቴዎዶር ሪክ “መስማማት የነገሮችን ምንነት እንደሚለውጠው ልብ ማለት ያሻል” ሲል ይጀምራል። “የፍሮይድ ተከታይ የስነ-ልቦና ባለሙያዎች (Psychoanalysts) ከፍቅር ውጪ ወሲብ ሊኖር እንደሚችል ማመናቸው አጠራጣሪ ነገር አይደለ፤ ወሲብ ብቻ። ነገር ግን በኃይል ገርስሰው የማያልፉት እውነት ደግሞ ከወሲብ ውጪ ፍቅር መኖሩን ነው።” አሁንም ሌላኛው የስነ አእምሮ ምሁርና የ The art of loving መጽሐፍ ደራሲ ኤሪክ ፍሮም እንዲህ በማለት ማስጠንቀቂያ ብጤ ጣል ያደርጋል፡፡
“አፍቅሮተ-ፍትዎት እውን ሲሆን ከንፁህ ፍቅር የማይለይ አደናጋሪ ስሜት አብሮት ይከሰታል …ነገር ግን አፍቅሮተ-ፍትዎት የተለየ ግምትና ቦታ የሚሰጠው ከፍቅር ይልቅ ለወሲብ ፍላጎት በመሆኑ ይለያል። አፍቅሮተ-ፍትዎት የመተሳሰብ ፍቅር አብሮት ከሌለ በስተቀር ቅጥ ያጣ የመቅበጥ ግንኙነትና የማይዘልቅ ጊዜአዊ ይሆናል።”…
ብዙ ታላላቅ ባለቅኔዎች ይሄንን አመለካከት ይደግፋሉ። ከረጅም ዓመታት በፊት የስነ-አእምሮ ምሁራኑን አቋም በቅኔዎቻቸው ውስጥ አካትተው ተስተውለዋል። በእነዚህ ቅኔዎች ውስጥ የስነ-አእምሮ ሳይንሳዊ ግኝቶች ሙሉ በሙሉ ባይካተቱም ሰዋዊ ፍቅርን ቀድመው በመረዳት ጥቂት ነገር ብለዋል ።
ባለቅኔው ሚልተን “Paradise Lost” የተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ እንደሚለው ፍቅር የጥልቅ ስሜት ማመላከቻ ነው። ባለቅኔውና ፀሐፌ ተውኔቱ ሼክስፒር ደግሞ ፍቅር ፅናትን ማመላከቻ ነው ይላል። ከሁሉም በላይ ፍቅር በተፈቃሪዎች መዋሃድ ይገለፃል ብሎ የሚያምነው ደግሞ ባለቅኔው ጆን ዶን ነው።
አንድ ነባር የግሪክ አፈታሪክ እንደሚለው ቀደም ሲል የሰው ልጅ ግማሽ ወንድ፣ ግማሽ ሴት የሆነ እርስ በእርሱ ቅልቅል ፍጥረት ነበር። አንድ ቀዥባራ አማልክት እንደ አክርማ ለሁለት ሰነጠቀው እንጂ። በመሆኑም ግማሹ ወንድ የተቀረው ሴት ሆነ። ለምንጊዜውም ተለያየ እነዚህ የሰው ግማሾች (ወንድና ሴት) ዘወትር ዳግም ለመዋሃድ እንደሞከሩ ነው። ዘመናዊዎቹ የስነ-ልቦና ሊቆች ይሄንኑ አፈታሪክ ትንሽ ለውጥ አድርገው ይደግሙታል። “የሰው ልጅ ስውር ፍላጎቱ እራሱን ተነጥሎ ከመቅረት መታደግ ነው። ከብቸኝነት እስር ቤት ሰብሮ መውጣት”
አዲስ ዘመን ጥር 1/2012