Connect with us

“አቃተን” ማለትም እኮ ይቻላል !!!

"አቃተን" ማለትም እኮ ይቻላል !!!
Photo: Facebook

ጥበብና ባህል

“አቃተን” ማለትም እኮ ይቻላል !!!

“አቃተን” ማለትም እኮ ይቻላል !!!
(ዮሐንስ መኮንን)

የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ የእንግሊዝኛ መጽሐፋችን ላይ ያለ ስለ ቀበሮ ቤተሰብ የሚተርክ አንድ ታሪክ ትዝ ይለኛል። በታሪኩ የተራቡ የቀበሮ ልጆች በመንገድ ሲያልፉ ግምብ ላይ ተንዠርግጎ ያዩትን የበሰለ ወይን ዘለላ እናታቸውን እንድታወርድላቸው ያስቸግሯታል።

እናትዬውም ወይኑን ስታየው እውነትም አበሳሰሉ ለዓይን የሚያስጎመጅ ምራቅም የሚያስውጥ መሆኑን አስተዋለች። “ችግር የለውም። አውርጄው እንበላዋለን” ብላ ቃል በመግባት ወይኑን ለማውረድ መዝለል ጀመረች። ምንም ያህል ብትዘል ግንቡንም ብትቧጥጥ የሚያስጎመጀው ብስል ወይን ርቆ ከተሰቀለበት ግንብ ማውረድ ሳይቻላት በመቅረቱ አንጀቷ እያረረ ልጆቿን እንዲህ አለቻቸው። “ግንቡ ጫፍ ወጥቼ ወይኑን ቀምሼው ነበር። ወይኑ ያልበሰለ ከመሆኑም በላይ መራራ ስለሆነ ይቅርባችሁ”

ይህንን በልጅነቴ ያነበብኩትን ታሪክ ያስታወሰኝ ሰሞኑን ወንድሜ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ ጠርዘኛ ጎሰኞች የሚያዘንቡበት የአሉባልታ ውርጅብኝ ነው። የተራ ግለሰቦችን አጉራ ዘለል ስድብ እና ውግዘት ቸል ብሎ ማለፍ ይገባል። እስካሁን የሆነውም እንዲሁ ነበር። አሁን አሁን ግን በመቶ ሺህ የሚቆጠር ተከታይ ባላቸው ገጸ ጦማሮቻቸው (ፌስ ቡክ) እና የቴሌቪዠን ቻናሎቻቸው ሳይቀር በርብርብ የተቀናጀ የአሉባልታ ዘመቻ ሲከፍቱበት አልፎ ተርፍፎ ሠልፍ ሲያደራጁበት ከኋላ ያለውን ገፊ ምክንያት መመርመር ይገባል እላለሁ።

እስከማውቀው ድረስ ዳኒ የጠቅላይ ሚንስትሩ የማኀበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሆኖ የተሾመው በተለመደው የካድሬ ሰንሰለት ባሳየው ታዛዥነት፣ በደጅ ጥናት ወይንም ከነባር የፖለቲካ ሥልጣን በጡረታ በመገለል አይደለም። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው “የእናንተ አገዛ ያስፈልገናል። ‘ኑ ኢትዮጵያን እናዋልዳት’ ብለህ እንደጻፍከው ሀገሪቱን በጋራ እናሻግራት” ብለው ጋብዘውት ነው። እንዲያውም መጀመሪያ አካባቢ በሳምንት ሦስት ቀናትን ብቻ በቤተ መንግሥት እየተገኘ የማማከር ሥራዎቹን ያከናውን የነበረ ሲሆን ሥራው እየበዛ ሲመጣ ግን ሙሉ ጊዜውን ለሀገሩ በመስጠት ያለእረፍት በማገልገል ላይ እንደሚገኝ እኔው እራሴ የቅርብ ምስክሩ ነኝ።

አልፎ አልፎ ምሳ ለመብላት ስንገናኝ “ዳኒ የሀገራችን ፖለቲካ በጥላቻ፣ በመበላላት እና በሴራ የተተበተበ ነው። ጽንፈኞች የሚያዘንቡብህ የተቃውሞ ውርጅበኝ ከምትታገስ ለምን አይቀርብህም?” ስንለው ቅጭም ባለ ፊት “ትልቅ ዋጋ ያላቸው በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ንብረቶች እንዳይበላሹ ፊውዝ ይገጠምላቸዋል። ፊውዙ ስለራሱ ጥቅም እና ምቾት ሳይጨነቅ ራሱን አቃጥሎም ቢሆን ከፍ ያለ ዋጋ ያለውን ንብረት ያድናል። በምድርም በሰማይም እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ያላትን ኢትዮጵያን ለማዳን ዜጎች በሚችሉት ሁሉ ሊረባረቡ የሚገባበት ወቅት ላይ ወደኋላ ማፈግፈግ አይገባም” ይለናል።

በእርግጥ ዳንኤል በአንገቱ ላይ ያንጠለጠላት (PM Advisor) የምትለው መታወቂያ ለበርካታ ተቃዋሚዎቹ ርቃ የተሰቀለች የምታስጎመጅ ብስል የወይን ዘለላ ናት። ምንም ያህል ቢዘሉ የማይደርሱባት ስትሆንባቸው እንደቀበሮዋ ለመንጋ ተከታዮቻቸው “ዳንኤል አልበሰለም” የሚል ቀረርቶ በየሚዲያዎቻቸው ይደሰኩራሉ።

ዳንኤል በፈቃደኝነት የተቀበለው ሀገርን የማማከር ሥራ በግል ብቃቱ የተቀበለው ኃላፊነት አንጂ ከቤተ ክህነት ወይንም በፓርቲ ውክልና “ተመድቦ” አይደለም። እርሱን ስታብጠለጥሉ የምትውሉ ሰዎች ከእርሱ የተሻለ የማሰብ ብቃት እንዳላችሁ በአደባባይ አስመስክሩና ቦታውን ተረከቡት። አከተመ። በተረፈ ከዚህ ቀደም እራሱ ዳንኤል የጻፋትን “አትውረድ” የምትል ዝነኛ ጽሑፉን ፈልጋችሁ አንድታነቧት የምጋብዛችሁ በምክንያት ነው። እርሱ ከደረሰበት ከፍታ እንኳንስ ሊወርድላችሁ እናንተም ከ “ሰውነት” እንዳትወርዱ ይመክራቸኋልና!

በግሌ በእርግጠኝነት የምመሠክረው አንድ ነገር ቢኖር ዳንኤል ለቤተመንግሥቱ ያስፈልገው ይሆናል እንጂ ቤተመንግሥቱ ለዳንኤል ፈጽሞ አያስፈልገውም። ተቃዋሚዎቹ ዘልላችሁ ዘላችሁ እርሱ የደረሰበት ከፍታ ላይ መድረስ ካልሆነላችሁም በሀሰተኛ ውነጀላ ማሩን ከማምረር ወተቱንም ከማጥቆር “አቃተን” ማለትም እኮ ይቻላል ! እኛም እንረዳችኋለን!

Click to comment

More in ጥበብና ባህል

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top