የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ወደ ባንክ ሂሳብ ገቢ ማድረግ የሚያስችል ኤቲኤም (ATM) ማሽን ሥራ ላይ አዋለ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ገቢ ማድረግና የውጭ ምንዛሬ መመንዘር የሚያስችል የኤቲኤም (ATM) ማሽን በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ።
ይህ አዲስ የATM ማሽን ቀደም ሲል አገልግሎት ላይ ከዋለው የገንዘብ መክፈያ የATM ማሽን ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ገንዘብ ገቢ ማድረግና የውጭ ምንዛሬ መመንዘር የሚያስችል በመሆኑ ደንበኞች ገንዘብ ወደ ሂሳባቸው ገቢ ማድረግ እና የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚችሉበት ነው።
ይህ አገልግሎት ለመጀመርያ ጊዜ ስራ ላይ ያዋለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዲሱ ATM ማሽን በአሁኑ ሰዐት በሙከራ ደረጃ በባንኩ ፍንፍኔ ቅርንጫፍ ላይ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ይህ ማሽን ባንኩ አገልግሎት የመስጠት ሥራውን ከማቃለሉ በተጨማሪ በተለይ ባንኮች ክፍት በማይሆኑበት ዕለታት ደንበኞች የእለተ እለት ስራቸውን ለማቀላጠፍ እንዲችሉ ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።
በአሁኑ ወቅት ባንኩ ካሉት ከ22 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች፣ 30 በመቶ የሚሆኑት የዲጅታል የክፍያ አማራጮችን የሚጠቀሙ ሲሆን፣ ይህ አዲስ ATM ማሽን የዲጅታል የክፍያ አማራጭ ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥርን እደሚያሳድግ ይታመናል፡፡
በሙከራ ደረጃ አገልግት መስጠት የጀመረው አዲሱ ATM ማሽን በዋናነት የሚሰጣቸው አገልግሎቶች፤ደንበኞች ካርዱን ወደ ማሽኑ በማስገባትና የሚስጥር ቁጥሩን በመጠቀም፤
ገንዘብ ማስገባት
ገንዘብ ማውጣት
ቼክ ወደ ሂሳብ አካውንት ማስገባት
ማሽኑ የኢትዮጵያ ባለ 5፣ 10፣ 50፣ እና የ100 ብር ኖቶችን በቀላሉ ለይቶ ይቀበላል፤
ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ለይቶ ማስወገድ ይችላል፤
—
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፍ በሻሸመኔ ከተማ ከፈተ
ቅርንጫፉ የሸርዓ መርህን መሠረት አድርጎ አገልግሎቱን እንደሚሰጥ በምረቃ ሥነ-ስርዐቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዘዳንትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባጫ ጊና በምረቃ ሥነ-ስርዐቱ ላይ እንዳሉት “የአል ኢማን ቅርንጫፍ” በሻሸመኔ ከተማ መከፈት፣ ወለድን በመፍራት ከባንክ ርቆ ለቆየው የከተማዋና አካባቢው ህብረተሰብ የባንክ አገልግሎትን በተሟላ ሁኔታ እንዲያገኝ የሚያስችል ነው፡፡
በቀጣይም ባንኩ የሸርዓ መርህን ተከትለው አገልግሎት የሚሰጡ ሌሎች ቅርንጫፎችን በሻሸመኔ ከተማና አካባቢው እንደሚከፍት አቶ ባጫ ገልፀዋል፡፡
የሻሸመኔ ከተማ የእስልምና ጉዳዮች የመጂልስ ኃላፊ ሼህ ማህመድ አቡቴ ጎበና በበኩላቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “የአል ኢማን ቅርንጫፍ” ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርጎ መከፈቱ ወለድን በመፍራት ብቻ ከባንክ ርቆ የቆየውን የህብረተሰብ ክፍል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልፀው፤ ለባንኩም ምስጋናቸውን አበርክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሸርዓ አማካሪ ሰብሳቢ ዶ/ር ጀኢላን ከድር በበኩላቸው ባንኩ በባለፉት አመታት ከ1500 በላይ ቅርንጫፎቹ አማካኝነት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን በመስኮት ደረጃ ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው ይህም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን እንዲያገኙና የቁጠባ ባህላቸው እንዲዳብር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ሰአት እየከፈታቸው የሚገኙ ቅርንጫፎችም የሸርዓ ህግን የተከተሉና ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ በመሆኑ ህብረተሰቡ ወደ ቅርንጫፎቹ በመሄድ አገልግሎቱን እንዲጠቀም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ አደም ማህመድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአካባቢው ህብረተሰብ የባንክ አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረገ ያለው ጥረት ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው በእለቱ “የአል ኢማን ቅርንጫፍ” በከተማዋ መከፈትም ተደራሽነቱ የተሟላ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በሻሸመኔ ከተማ “የአል ኢማን ቅርንጫፍ” የምረቃ መርሃ ግብር ላይ የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ፣ የባንኩ ከወለድ ነፃ የሸርዓ አማካሪ ሰብሳቢና አባላት፣ የአርሲ ዞንና የሻሸመኔ ከተማ የስራ ሃላፊዎች፣ የባንኩ ደንበኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡
(ምንጭ:- ኢትዮ ንግድ ባንክ)