ኦነግ ከምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘቱ ደስታውን ገለፀ። (መግለጫው እነሆ)
*****
የደስታ መግለጫ
(ኦነግ – ኅዳር 5, 2012 ዓ.ም.)
የተከበርክ ሰፊዉ የኦሮሞ ሕዝብ
የተከበራችሁ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች
ሁሉም የትግል አጋሮቻችንና ሰላም-ወዳድ የዓለም ማህበረሰቦች
ከሁሉም በላይ ደግሞ የተወደዳችሁ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ
እንኳን ደስ ኣላችሁ ! እንኳን ደስ ኣለን !
በዛሬዋ ዕለት (ኅዳር 5, 2012 ዓ.ም.) ድርጅታችን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህጋዊ ሰዉነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ማግኘቱን በከፍተኛ ደስታ እናበስራለን።
ከተመሠረተ 46 ዓመታትን ያስቆጠረዉ ድርጅታችን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሰፊዉ የኦሮሞ ሕዝብ ነፃነቱን ለመጎናጸፍ የሚያካሄደዉን ፍትሃዊ ትግል በመምራት ትግሉ ታላላቅና አንጸባራቂ ድሎችን እንዲያስመዘግብ ከማስቻሉም በተጨማሪ በዚህች ሀገር ፖለቲካ ዉስጥ ጉልህ ኣዎንታዊ ለዉጦች እንድከሰቱ በማድረጉ ሂደት ዉስጥም ወሳኝ አስተዋጽዖ ኣበርክቷል። በ1991/92 እ.ኤ.አ. (በቻርተሩ ወቅት) በኢትዮጵያ ህብረብሔራዊ ፌዴራልዝም ስርዓት (Multinational Federation System) ግንባታ መሠረት በመጣሉ ሂደት ዉስጥ ኦነግ የተጫወተዉ ወሳኝ ሚና ለዚህ ህያዉ ምስክር ነዉ።
ሆኖም ግን፣ በጭቆናና ብዝበዛ፣ እንዲሁም በአንድ ወገን የበላይነት ላይ የተመሠረተዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ስርዓት ኦነግ ከሚታገልለት ፍትሃዊና ሕዝባዊ የፖለቲካ ዓላማ በተቃራኒ በመሆኑ ሁለቱ የማይጣጣሙ ሆኖ እስከ ዛሬ ቆየን። ከዚህ የተነሳም ኦነግ በዚህች ሀገር የፖለቲካ ሂደት ዉስጥ በሰላማዊ መንገድ ተንቀሳቅሶ ዓላማዉን እንዳያራምድ ከመደረጉም ኣልፎ እንደ ፀረ-ሰላምና የሀገር ጠላት በመፈረጅ ያለ ስሙ ስም ተለጥፎበት እንደ ጠላት ስዘመትበት ኖረ። ይህ እጅግ የተሳሳተ የፖለቲካ አካሄድ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮናሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ዋናዉ ምንጭ በመሆን ሕዝቦቻችንን ከፍተኛ የህይወትና የንብረት መስዋዕትነት ከማስከፈሉም በላይ መሠረታዊ የሰላም ስጋትና የዕድገታችን ጠንቅ ሆኖ ዓመታትን ኣስቆጠረ።
ዛሬ ያ አሳዛኝ ሁኔታ በሕዝቦቻችን መራራ ትግልና ከባድ መስዋዕትነት (በሚፈለገዉ ደረጃም ባይሆን) ተቀይሮ ለዚህ ደረጃ መብቃታችን የህዝቦቻችን የዓመታት ትግልና መስዋዕትነት ዉጤት ነዉ። ትልቅ ተስፋም ያሳድርብናል። ይህንን ዕድል በመጠቀም እስከዛሬም መፍትሄ ላላገኙ ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ በልበ-ሙሉነትና በቆራጥነት የሚንሰራ መሆናችንንም እናሳዉቃለን።
በዚህ አጋጣሚ ለዚህች ሀገር የዴሞክራሲ ግንባታ እየተደረገ ባለዉ ጥረት ዉስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እያበረከተ ያለዉ ወሳኝ አስተዋጽዖም ልመሰገንና ልበረታታ የሚገባዉ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን።
በመጨረሻም፣ የሕዝቦችን ነፃነት፣ ዴሞክራሲያዊነትንና እኩልነትን በማረጋገጥ በሀገራችንና በቀጠናችን ዘላቂ ሰላምና የጋራ ዕድገትን ለማስገኘት የሕዝቦችን ፍላጎትና ዘላቂ ጥቅም እንድሁም ሀቅን መሠረት አድርገን አብረን እንድንሰራ ለሚመለከታቸዉ ሁሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ከዚሁ ጋር በማያያዝ ይህ የኦነግ ባንዴራና ኣርማ ህጋዊ የድርጅታችን (ኦነግ) ባንዴራና ኣርማ መሆናቸዉ ታዉቆ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን በህጉ መሠረት ነፃ ሆኖ የሚገለገሉበት መሆኑን እናስገነዝባለን። በተጨማሪም፣ ለማስመሰል ይህን ባንዴራና ኣርማ ይዞ በመንቀሳቀስ ለእኩይ ዓላማ በመጠቀም የድርጅታችንን እና የሕዝባችንን ስም ለማጉደፍ፣ እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚሞክሩ ካሉ ሕዝቡ በንቃት ተከታትሎ እንዲያጋልጣቸዉ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።
ድል ለሰፊዉ ሕዝብ !
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር
ኅዳር 5, 2012 ዓ.ም.