ዩኔስኮ ለስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ልማት የሚውል 74 ሺህ የአሜሪካ ዶላር መመደቡን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። ዓለም አቀፉ የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለባለሙያዎች ስልጠና እና ለቁሳቁስ ማሟያ የሚሆን 74 ሺህ የአሜሪካን ዶላር መመደቡን የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ባለፈው ዓመት ብሔራዊ ፓርኩ የእሳት ቃጠሎ ከደረሰበት የፓርኩ አካል መካከል 65 በመቶው ሳር ስለነበር በፍጥነት ማገገሙም ታውቋል፡፡ በተለይም ሳር በል ለሆኑ የፓርኩ እንስሳት ምቹ የሳር መኖ መውጣቱን ነው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው የተናገሩት፡፡
የደረሰው የእሳት ቃጠሎ የከፋ የሚባል አሉታዊ ተጽዕኖ አላሳደረም፡፡ ድርጊቱ ባልታወቀ መንገድ የተፈጸመ እና ሳይንሳዊ መንገዱን ያልተከተለ መሆኑ እንጂ ቃጠሎ በሳይንሳዊ መልኩ እንደሚመከርም ተናግረዋል፡፡
ተፈጥሮ የነበረው ችግር ዳግም እንዳይፈጠር የሕዝቡን የመልካም አስተዳድር ችግሮች አስቀድሞ ለመፍታት፣ ማኅበረሰቡን በልማት እና በአካባቢጥበቃ ለማሳተፍ፣ የአካባቢውን የፀጥታ አካላት ከፓርኩ ስካውቶች ጋር በማገናኘት በየቀጠናው ጥብቅ የቁጥጥር ሥራ ለማከናወን በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡ ችግሩ በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸውን ቦታና ጊዜ በመለዬትም 24 ሰዓት ጠበቅ ያለ ቁጥጥር እንዲደረግ ይሠራል ብለዋል አቶ አበባው፡፡
ዓለም አቀፉ የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ብሔራዊ ፓርኩን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማልማት እና ለመንከባከብ የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡ ዩኔስኮ ለባለሙያዎች ስልጠና እና ለቁሳቁስ ማሟያ የሚሆን 74 ሺህ የአሜሪካን ዶላር መድቧል ነው ያሉት፡፡
ባለሙያዎች የእሳት አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ውጤታማ የመቆጣጠር ሥራ ማከናወን የሚያስችል ስልጠና በኬንያ መውሰዳቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የሰለጠኑት ባለሙያዎችም እስከ ሕዳር 20/2012 ዓ.ም ድረስ በሀገሪቱ ከሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች ለተውጣጡ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና በደባርቅ ከተማ እንደሚሰጡ ተመላቷል፡፡ በፓርኩ አዋሳኝ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶችም ስልጠናውን ይወስዳሉ ተብሏል፡፡
በተያያዘ ዜና በብሔራዊ ፓርኩ 38 ሺህ የሚጠጉ የተለያዩ ሀገር በቀል ችግኞች በክረምቱ ተተክለዋል፤ 25 ሺህ ሄክታር የፓርኩ መሬትም በችግኞች ተሸፍኗል፡፡
በችግኝ ተከላ ዘመቻውም የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ጨምሮ የክልል እና የፌደራል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና ሌሎችም አካላት ተሳትፈውበታል፡፡ ችግኞቹ እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑንም አቶ አበባው ነግረውናል፡፡
የአካባቢውን ወጣቶች በማሰማራትም የማረም እና የመኮትኮት ተግባራት እየተከናወነ ነው፡፡ እንደአብመድ የተተከለው ችግኝ የጽድቀት መጠን እንዲጨምር ከዘርፉ ባለሙያ ጋር ለመሥራት መታሰቡንም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡
ምንጭ:- ኢፕድ