50 ቢሊዮን ብር የወጣበት የአዋሽ – ኮምቦልቻ የባቡር ፕሮጀክት በኤሌክትሪክ ችግር አገልግሎት መስጠት አልቻለም
የካቲት 2007 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የኮምቦልቻ – አዋሽ – ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተገነባ ነው:: በምዕራፍ አንድ ከአዋሽ – ኮምቦልቻ የ270 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን 99 ነጥብ ሰባት በመቶም ተጠናቋል:: የሚቀሩት ስራዎች የሙከራና የርክክብ ተግባራት ብቻ ናቸው:: እነዚህ ስራዎች ያልተጠናቀቁትም በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማጣት ብቻ ነው ይላሉ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ዘርፍ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሻሎም አሹሮ ::
የባቡር ፕሮጀክቱ 390 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይሸፍናል:: ከኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ ያለው የምዕራፍ ሁለት ግንባታ ደግሞ ስራው 73 በመቶ ተጠናቋል:: ይህ ፕሮጀክት በ2012 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ገልፀዋል::
በወቅቱ ምንዛሬ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ (አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር) የተበጀተለት የባቡር ፕሮጀክቱ ዋነኛ ተቋራጭ ፈረንሳዊያን ሲሆኑ በንዑስ ተቋራጭነት ደግሞ የቱርኩ “ያፒ መርከዚ ኮንስትራክሽን” ድርጅት ተዋውሎ ስራው እየተከናወነ ይገኛል:: ፖርቱጋላዊያንና ፈረንሳዊያን የስራ ተቋራጮች ደግሞ አማካሪዎች ናቸው:: 25 በመቶ የሚሆኑት ሙያተኞች ቱርካዊያንና ጥቂት ፊሊፒንሳዊያን ሲሆኑ በፕሮጀክቱ ግንባታ 75 በመቶ በኢትዮጵያውያን የሰው ኃይል የተሸፈነ ነው::
ሐዲዱ አንድ ነጥብ 43 ሜትር ስፋት ያለውና ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ነው:: 10 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ 12 ዋሻዎች፣ ሰባት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው 65 ድልድዮች፣ 827 የውሃ ማፋሰሻዎች፣ ስምንት የኃይል ማስተላለፊያዎችና 10 የባቡር ንዑስ ጣቢያዎች ግንባታቸው ተጠናቀዋል::
በኮምቦልቻ ከተማ አካባቢ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ፕሮጀክት አካል የሆነ የባቡር ጥገና ማዕከልም በዘመናዊ መልኩ ተገንብቷል :: በማእከሉ ጥራታቸው የዘመኑ መሳሪያዎች ተተክለዋል:: የሙያተኞች ልምድም በአውሮፓውያን የተቃኘ ሲሆን የታጠቀው ቴክኖሎጂውም ዓለም በአሁኑ ወቅት የደረሰበት በመሆኑ ለኢትዮጵያውያን የዘርፉ ሙያተኞች ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያደርግ አቶ ተክለብርሃን አበበ የኮምቦልቻ – አዋሽ – ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የባቡሮች ጥገና ማዕከል ምክትል ኃላፊ ገልፀዋል::
ከሙያና ቴክኒክ ኮሌጆችም ይሁን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰለጠኑ ኢትዮጵያውያን በፕሮጀክቱ ሙያቸውን በተግባር የሚፈትኑበት አጋጣሚ እንደሚሆን አቶ ተክለብርሃን ገልፀዋል::
የባቡር ጥገና ማዕከሉ ለባቡር ጥገና አገልግሎት የሚውሉ መለዋወጫዎችን ማምረት የሚችል ዘመናዊ የጥገና ማዕከልም ነው:: ማዕከሉ ስምንት ባቡሮችን በአንድ ጊዜ መጠገን ይችላል:: የጥገና ሂደቱ ኮምፒዩተራይዝድ ነው:: ዘመናዊ የመፈተሻ መሳሪያዎች የተገጠሙለት የጥገና ማዕከሉ ቀላልም ይሁን ከባድ የባቡር ብልሽቶችን በፍጥነት ለመጠገን የሚያስችል አቅም አለው::
በኢትዮጵያ ትልቅና ዘመናዊ የሆነው የኮምቦልቻ የባቡር ጥገና ማዕከል ከዚህ በፊት ለባቡሮች ጥገና የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ከማስቻሉም ባሻገር በፕሮጀክቱ የሚንቀሳቀሱ ባቡሮች በብልሽት ምክንያት አገልግሎት መስጠት እንዳያቋርጡ ለማድረግ ሚናው የጐላ ነው:: ፕሮጀክቱ ስራ ሲጀምር የሚቀበለው በርካታ የሰው ኃይልም ሌላኛው ከፕሮጀክቱ የሚጠበቅ በረከት ነው::
የባቡር ጥገና ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለርክክብና ለሙከራ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል ይላሉ ኢንጅነር ሻሎም አሹሮ ::
የባቡሮችን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች መቆጣጠሪያ ማዕከልም በኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ እየተገነባ ነው:: የማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ 20 የዕቃ መጫኛና ስድስት የህዝብ ማመላለሻ ባቡሮች ይኖሩታል::
አንድ የሰው ማጓጓዣ ባቡር በአንድ ጊዜ 720 ሰዎችን የሚያጓጉዝ ሲሆን አጠቃላይ ባቡሮቹ በቀን አራት ሺህ 320 ሰዎችን ማጓጓዝ ይችላሉ:: አንዱ የዕቃ ማመላለሻ ባቡር ደግሞ አንድ ሺህ 350 ቶን የመሸከም አቅም ያለው ሲሆን ሰላሳ ተጐታች ፉርጐዎች ይኖሩታል:: አንዱ የዕቃ ማመላለሻ ባቡር 30 የጭነት መኪኖች ከነተሳቢያቸው የሚጭኑትን ጭነት ያክል በአንድ ጊዜ የመሽከም አቅም ይኖረዋል::
የባቡር ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ – ጅቡቲ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ጋር የሚገናኝ ሲሆን ወደ ጅቡቲ ለመድረስ የሚወስደውን ጊዜ በግማሽ የሚቀንስም ይሆናል:: ፕሮጀክቱ ለኮምቦልቻ ከተማ፣ ለዞኑ፣ ለክልላችንና በአጠቃላይም ለሀገር ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው::
የአማራ ክልል ከዚህ ፕሮጀክት በእጅጉ ተጠቃሚ ይሆናል:: ለአብነትም፦ እንደ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር እና መሰል ግብርናውን የሚደግፉ ቁሳቁሶች በፍጥነትና አርሶ አደሩ በሚፈልጋቸው ጊዜ እንዲቀርቡለት የፕሮጀክቱ ሚና የጐላ ነው::
ኮምቦልቻ ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርክና ደረቅ ወደብ መኖሩ ብቻ ሳይሆን አካባቢው የንግድ ማእከል ከመሆኑ ጋር ተያያዞ የባቡር ፕሮጀክቱን ጠቀሜታ በእጅጉ ከፍ ያደረገዋል::
ወይዘሮ አምሳል መሀመድ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ ናቸው:: የባቡር ፕሮጀክቱ ለከተማዋ ወጣቶች ከፈጠረው የስራ ዕድል በተጨማሪ ለከተማዋና ለህብረተሰቡ ዕድገት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ገልጸውልናል:: ለፕሮጀክቱ ሲባል ከመሬታቸው የተነሱ አባዎራዎችና ልጆቻቸው የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውም ሆነ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ መደረጉም ሌላው የፕሮጀክቱ ጠቀሜታ መሆኑን ወይዘሮ አምሳል ገልጸውልናል::
አቶ አሊ ሰኢድ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ የባቡር ፕሮጀክቱ ለኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎችና በተለይም ለልማቱ መሬታቸውን የለቀቁ የህብረተሰብ ክፍሎች በርካታ ጸጋዎችን ይዞ እንደመጣ እማኝነታቸውን ሰጥተውናል:: ፕሮጀክቱ በአፋጣኝ ስራ መጀመር እንዳለበት የገለጹልን አቶ አሊ የባቡሮች መቆጣጠሪያ ጣቢያውም ሆነ የባቡር ጥገና ማዕከሉ ወደ ስራ ሲገቡ የልማት ተነሺዎችን ብቻ ሳይሆን በርካታ የከተማውን እንዲሁም የክልሉን ስራ ፈላጊ ወጣቶች ወደ ስራ የሚያስገባ በመሆኑ የፕሮጀክቱን ስራ መጀመር በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል::
የባቡር ፕሮጀክቱ ካለበት አካባቢ የሚሰበሰብ የግብርና ምርትን ወደ ውጭ ለመላክም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ነው የፕሮጀክቱ የዘርፍ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሻሎም የገለፁት::
ፕሮጀክቱ ባለባቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ የስርቆት አዝማሚያዎች እየታዩ ነው ይላሉ ኢንጅነር ሻሎም:: በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተገዙ የፕሮጀክቱን ዕቃዎች ወደሥራ ባለመግባታቸው በአንዳንድ ግለሰቦች እየተሰረቁና ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑንም ኢንጀነር ሻሎም ጠቁመዋል:: ስለሆነም መሳሪያዎች አገልግሎት መስጠት ካልቻሉ እና ሙከራ ካልተደረገባቸው የመበላሸት እድላቸው የሰፋ እንደሚሆንም ነው ኢንጅነሩ የገለጹት::
በፕሮጀክቱ ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ወቅት “ካሳ አንሶናል!” በሚሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ምክንያት የስራ መጓተቶችም አጋጥመዋል:: ኮርፖሬሽኑ በጥናት ላይ ተመስርቶም ሁሉንም የካሳ ክፍያ የፈፀመ ቢሆንም አንዳንድ ወረዳዎች ላይ ስራዎች እንዲጓተቱ ተደርጓል:: ችግሩን ለመቅረፍ ከክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ ጋር ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ኢንጂነር ሻሎም ተናግረዋል ::
ፕሮጀክቱ የልማት ተነሺዎችን የሚከታተል ቡድን አቋቁሞ ለተነሺዎቹ በፕሮጀክቱ ውስጥ ቅድሚያ የስራ ዕድል በመስጠት፣ በካሳ ክፍያው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ስልጠና በመስጠትና በመሳሰሉት ጥቅማ ጥቅሞች የልማት ተነሺዎቹ ተጠቃሚ እንጂ ተጐጂ እንዳይሆኑ መስራቱንም ነው ኢንጅነር ሻሎም የገለፁት::
ከፕሮጀክቱ በቂ የሆነ የዕውቀት ሽግግር የተደረገበት መሆኑን የሚገልፁት ኢንጅነር ሻሎም በቀጣይ ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ሙያተኞች በራሳቸው አቅም በተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሰሩበት ዕድል እንደተፈጠረላቸው ገልፀውልናል::
በምዕራፍ አንድ የተጠናቀቀው ፕሮጀክት (ከአዋሽ – ኮምቦልቻ) ርክክብ ተደርጐ ወደ ሙከራ ትግበራ እንዳይገባ እንቅፋት የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በፌደራል መንግሥት በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጠቶት ችግሩ በአፋጣኝ መፈታት እንዳለበት የዘርፍ ስራ እስኪያጁ ኢንጂነር ሻሎም ገልፀዋል:: ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ከተቋራጩ ጋር የነበረው መልካም ግንኙነት በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ መዘግየት ምክንያት ሊበላሽ እንደሚችልም ኢንጅነሩ ስጋታቸውን ገልፀውልናል::
አቶ ሞገስ መኮንን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት /ኮርፖሬሽን/ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ናቸው:: የኮምቦልቻ – አዋሽ – ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የሚያስፈልገው የኃይል አቅርቦት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እንዲያቀርብላቸው ፍላጐት አላቸው ብለውናል:: ይሁንና ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቱ የሚፈልገውን ኃይል የማቅረብ እንጂ የ “ሰብስቴሽን” ስራውም ይሁን የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው የፕሮጀክቱ እንደሆነ ተናግረዋል::
የባቡር ፕሮጀክቱ ተጀምሮ ከ40 በመቶ በላይ ሳይገነባ በ2009 ዓ.ም ፕሮጀክቱ የሚፈልገውን ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በራሱ ወጭ እንደሚሽፍን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እንደገለጸ ያስታወቁት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ሞገስ ከአሰራር ውጭ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን ወጭ ተቋማቸው እንደማይሽፍን ጭምር ገልፀውልናል::
የኃይል ችግር ሳይሆን የኃይል መሰረተ ልማቶች አለመዘርጋታቸው ለባቡር ፕሮጀክቱ ፈተና እንደሚሆኑ ያመኑት አቶ ሞገስ የባቡር ኘሮጀክቱ ለራሱ ብቻ የሚጠቀመውን የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት ዝርጋታ ወጭ መሸፈን የሚችልበትን አማራጮች ይዞ ሲቀርብ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የራሱን ተግባራት ለማከናወን ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ገልጸውልናል::
የኮምቦልቻ፣ አዋሽ፣ ሃራ ገበያ የምድር ባቡር ፕሮጀክት የዘርፍ አስኪያጅ ኢንጂነር ሻሎም አሹሮ በበኩላቸው ከዚህ በፊት የነበረው ተሞክሮ ሲታይ ለአብነትም ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ያለውን የባቡር መስመር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ያሟላው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን መሆኑን ገልፀው ይሄኛው ፕሮጀክት በውጭ የግል ባለሀብቶች በመያዙ ብቻ የአሰራር ለውጥ መኖር እንደሌለበት ጠቁመዋል::
ምድር ባቡር እና ኢትዮ – ኤሌክትሪክ ሁለቱም የመንግስት ተቋማት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ጣት ከመጠቋቆምና ከመገፋፋት ይልቅ የባቡር ፕሮጀክቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል መስራት እንደሚጠበቅባቸው ኢንጀነር ሻሎም አሳስበዋል::
“የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያለበትን የፋይናንስ እጥረት እኛም እንረዳዋለን” ያሉት ኢንጅነር ሻሎም በዚህ ችግር ላይ የተለያዩ የመንግስት ተቋማትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ተሳትፎን በማጉላት ለምድር ባቡር ፕሮጀክቱ ወሰኖችን አስጠብቆ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ እንጂ መገፋፋቱ ጥቅም እንደማያስገኝ ነው የገለፁልን::
ይህ ትልቅ ፕሮጀክት የክልላችን ብሎም የሀገራችንን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ ሚናው የላቀ ነው:: ይሁንና ፕሮጀክቱ አጋጥሞኛል የሚለው የኃይል አቅርቦት ችግር በአፋጣኝ ካልተፈታ ከፕሮጀክቱ የሚጠበቀው አገልግሎት “ላም አለኝ በሰማይ፤ ወተቷንም አላይ!” ዓይነት እንዳይሆን ያሰጋል:: መፍትሔው ኢንጅነር ሻሎም እንዳሉት ተናብቦ በመስራት የፕሮጀክቱን ጠቃሚነት በተግባር ማረጋገጥ ብቻ ነው::
(ምንጭ:- በኩር ጋዜጣ)