ከደብረ ሲና እስከ ራሳ፤ ያወደሟትና ያወደመቻቸው ሸዋሮቢት፡፡
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
የታለች እኔ የማውቃት ሸዋ ሮቢት? እነኛ እንደ አየር ንብረቷ የሚሞቁት ብዙ ነገሮቿ ፈዝዘዋል፡፡ ሰው የማይጠፋባቸው ሆቴሎቿ ተዘርፈው፣ ተሰብረው ዝም ብለዋል፡፡ ሸዋ ሮቢት የትናንቷን ስደርስ አላገኘኋትም፡፡
እዚህ የሀገር ልጅ ድንቅ ገድል ጽፏል፡፡ እየዘረፈ የመጣ ወራሪ ምኞቱ መክኖ የቀረበት ቦታ ደርሻለሁ፡፡ እዚህ መከላከያው ስለፋኖው አውርቶ አይጠግብም፤ ፋኖው መከላከያው ሀገር ለመታደግ የጣረውን ጥረት ያደንቃል፡፡ እዚህ ፋኖና መከላከያ አቤት ራሳ ብለው የብርቱ ይፋቴዎችን ጀግንነት እኩል ይመሰክራሉ፡፡
ፊልም ቢሆን ምራቅ ያስውጣል፣ ግን ደግሞ ከዚያ በላይ እውነት ነው፡፡ ሸዋ ሮቢት በግጦሽ ሳቢያ ድንበርተኛ ህዝቦች እርስ በእርስ ተጋጩ ሲባል ሰምታችሁ ይሆናል? እነሱ ናቸው ናቸው ዛሬ ሀገሬ ኢትዮጵያ ብለው አብረው የቆሙት፣
ይፋቴና አፋር ተማምሎ ገባ፡፡ ከሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ጎን ቆመ፡፡ ፋኖው እየተወረወረ ጠላት አፉ የከተታትን ሸዋሮቢት አስተፉት፡፡ ግን የሆነው ያሳዝናል፡፡ በዓይኔ ያየሁት ነው፡፡
የንግድ ተቋማቷ ወድመዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በተከፈቱት ሁለት ሆቴሎች እንኳን ብርጭቆ መጠየቅ ቅንጦት ነው፡፡
የሸዋ ሮቢትን ቀይ መስቀል ያየ የዚህች ምድር ወራሪ እንዲህ ያደርጋል ብሎ ለማመን ይከብደዋል፡፡ ቀይ መስቀል የትም አለ፤ ምልክቱ የደሃ ነው፡፡ ምልክቱ የሰው ልጅ ነው፡፡ በዓለም በከፉ ግጭቶች መካከል እንኳን ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ በሰላም ለማለፍ፣ በሰላም ለመርዳት እድል አላቸው፡፡
እዚህ ያየሁት ልብ ይነካል፡፡ ከሆነው አጋጣሚ ጋር ሲገናኝ ደግሞ ህመሙ ይብሳል፡፡ ቀይ መስቀሉ በር ላይ ቆመናል፡፡ ውስጡ አይተን ነው የወጣነው፡፡ መዳኒቶቹን ዘርግፈው፣ መደርደሪያውን ሰብረው ሰው ከሞት የሚታደጉ ውድ መድሃኒቶችን አድቅቀው ከጥቅም ውጪ አድርገውታል፡፡ ሸዋ ሮቢት ያለው የግል ፋርማሲ ሁሉ ተዘርፏል፡፡ አስም እያጣደፋት መተንፈስ ያቃታት ነፍሰ ጡር የመጨረሻ እድሏን ልትሞክር ቀይ መስቀሉ በራፍ ደረሰች፡፡ ላቧ ግንቧሯን አጥቦታል፡፡ የወደመውን የቀይ መስቀል መድሃኒት ቤት ስታይ ተስፋ ቆርጣ ቁጭ አለች፡፡ መልካሙ ነገር ከወደመውና ከተበተነው መድሃኒት ውስጥ እሷን የሚታደግ ጥቂት መድሃኒት ከወደቀበት ተለቅሞ ተሰጣት፡፡ አቤት ፊቷ ላይ የነበረ ደስታ፣ እንዲህ የየፊታችንን ደስታ ለማጥፋት ነበር ያሰቡት፡፡
ቤቶች ተዘርፈዋል፡፡ ሱቆች የሉም፡፡ ሸዋ ሮቢት ጎዳናዎቿ ላይ ነበረኝ የምትለውን ሀብት ወይ ጭነውታል፣ ወይ እዚያው ዘርግፈው አውድመውታል፡፡ የሆቴሎቿን መጠጦች ጠጥተው ሰባብረውታል፡፡ የጎዳናዎቿን ደማቅ መንፈስ በጥፋታቸው አደብዝዘውታል፡፡ በመጨረሻም ቀምሰው ወጡ ብሎ ደረቱን የሚነፋ ነዋሪ መዲና አድርገዋታል፡፡
ሸዋሮቢት የመጣነው ለፋኖው ለራሳዎቹና በህልውና ዘመቻው ሚና ለነበራቸው ወገኖቻችን በሜላት ዳዊት መሪነት በነጋዜጠኛ የኋላሸት ዘሪሁንና በሀገር ወዳዱ ነብዩ ሲራክ አስተባባሪነት ወገን አድርሱ ያለንን ደጀን ድጋፍ ከጓደኞቻችን ጋር በጋራ ሆነን ለማድረስ ነው፡፡ በርቱ ለማለት ሳይሆን እናመሰግናለን ለማለት ቢባል ይቀላል፡፡ ያለ በርቱ ባይ ድል ያስመዘገቡ ጀግኖች ቀዬ ደርሰናልና፤ ገና ብዙ ነገር እነግራችኋለሁ፡፡