ጽዮን ማርያም በዛሬው ቀን!!
(ጥበቡ በለጠ)
ትዝ አለችኝ። አመታዊ ክብረ በአሏ። ደግሞ ግራ ይገባኛል። እውነት ወያኔ ከዚያ አካባቢ የወጣ ነው? አገር እያፈረሰ የሚደሰት ሐይል ዕውን ከዚያ የወጣ ነው? ግራ ግብት ይላል። ምን አይነት ምክንያት ይሰጠው ይሆን? ከሰይጣን በላይ የሆነ ድርጊቱን ሳስብ ዕውን ከዚያ አካባቢ የወጣ ነው? ለመሆኑ ቀሳውስቱ የት ናቸው? የሐይማኖት መሪዎቹ የት ገቡ? እንዴት እንዲህ አይነት ፀረ ሰዎች ተፈጠሩ? ማን ነው ክፋት ያስተማራቸው? ጽዮን ሆይ ለኢትዮጵያ ሰላምን አምጭላት።
ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ልግባ። ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪኰች ሀገር እንደሆነች ተደጋግሞ ተደጋግሞ የተነገረ ሀቅ ነው። ኢትዮጵያ ራሷን ለውጭው ዓለም ለማስተዋወቅ ብዙም ጥረት ባታደርግም፤ ነገር ግን ከቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች መካከል አንዷ ሆናለች። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ማለትም /ዩኔስኮ/ የዓለም አስደናቂ ቅርሶች በማለት የመዘገባቸው የቱሪዝም መስዕቦች ከ20 ልቀዋል። እነዚህም ዘጠኝ ቋሚ ቅርሶች ሲሆኑ 12 ደግሞ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፎች ናቸው። እነዚህን ጥንታዊ የብራና ፅሁፎች ዶክመንተሪ ቅርስ /documentary Heritages/ በሚል መዝገብ ውስጥ አስቀምጧቸዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ለማስተዋወቅ በርትታ ብትሰራ ደግሞ እጅግ ብዙ አስገራሚ ነገሮችን ማስመዝገብ ትችላለች። ግን በዚያ ዘርፍ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ያን ያህል ጐልቶ አይታይም።
ኢትዮጵያ አሉኝ ከምትላቸው እጅግ አስገራሚ ቅርሶች መካከል የእምነት መገለጫ የሆነው ጽላተ-ሙሴ አንዱ ነው። ይህ ፅላት ከሦስት ሺ ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ ሲነገር ቆይቷል። በርካታ የእምነትና የታሪክ ተመራማሪዎችም አያሌ ማስረጃዎችን እየጠቀሱ ፅላቱ በኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን አረጋግጠዋል።
ይሁን እንጂ ይሄ በክርስትናው ዓለም ውስጥ ያሉ የዓለም ህዝቦች ሁሉ መገለጫ የሆነውን ፅላት በተመለከተ ልዩ ልዩ ፊልም ሰሪዎች፣ የልቦለድና የቴአትር ፀሐፊዎች፣ አርኪዮሎጂስቶችና ተመራማሪዎች የተለያዩ ኀሳቦችን ሲሰጡ ኖረዋል። አሁንም ይመራመራሉ።
አንዳንዱ ደግሞ ጽላተ-ሙሴን መሠረት አድርጐ ልብ ወለድ ሁሉ ይፅፋል። የፈረደባቸው ደግሞ በየሀገሩ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ እያደረጉ አንዴ አገኘነው ሲሉ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የተመራመሩበት ሁሉ ሀሰት ነው ተብለው ውድቅ የተደረገባቸው ጊዜያት ነጉደዋል።
በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ደግሞ ይህን ፅላት ከኢትዮጵያ እንወስደዋለን ብለው የውጭ ሀገር ሰዎች የተለያዩ ደባዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል። ነገር ግን ኢትዮጵያዊያኖች ለሀገራቸውና ለሃይማኖታቸው ባላቸው ቀናኢነት ማንም ድርሽ እንዳይል እያደረጉ በጀግንነት ቆይተዋል። በሀገሪቱ ውስጥ በተነሱ ታላላቅ ጦርነቶችም መካከል ፅላቱ አደጋ ውስጥ እንዳይገባ ብዙ ርብርብ ተደርጐ ቆይቷል።
በአንድ ወቅት ደግሞ Ron Wyatt የተባለ አሜሪካዊ አርኪዮሎጂስት ፅላተ-ሙሴን በእስራኤል ጐሎጐታ ውስጥ ቆፍሬ አገኘሁ ብሎ ተናገረ። ፊልምም ተሰራለት። በተለይ እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም የተቀረፀው የዚህ አርኪዮሎጂስት ግኝት በወቅቱ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። ይሄ ነገር እውነት ይሆን ብለው ብዙዎች መጠየቅ ጀምረው ነበር። እውን ጽላተ-ሙሴ ጐሎጐታ ውስጥ ተቆፍሮ ተገኝቷል?
ጉዳዩ ብዙ አነጋጋሪ ነገሮችን የያዘ ነው። አርኪዮሎጂስቱ Ron Wyatt ለማሳመኛ እንዲመቸው ብሎ ሌሎች በርካታ ጉዳዮችንም እያያዘ ተናገረ። በፊልም እያስደገፈ ፅላቱን አግኝቸዋለሁ አለ። ከፅላቱ ጋርም የተለያዩ የእስራኤል ቅርሶችን አገኘሁ እያለ ብዙ ተናገረ። ሚዲያዎችም ጉዳዩን እየተቀባበሉት አራገቡት። ነገር ግን በመጨሻም የRon Wyatt የአርኪዮሎጂ ግኝት ከፅላቱ ጋር ተያያዥነት እንደሌለው ተነገረ። ይሁን እንጂ ይህ አሜሪካዊ የሰራው ስራ ውዥንብር ፈጥሮ ማለፉ የማይታበል ሀቅ ነው።
ግርሃም ሀንኩክን ጨምሮ በርካታ ተመራማሪዎችና ፀሐፊዎች ደግሞ መፅሐፍ ከማሳተም አልፈው በፅላተ-ሙሴ ላይ ዶክመንተሪ ፊለሞችን ሰርተዋል። ግርሃም ሀንኩክ The Sign & the Seal በተሰኘው ታዋቂ መፅሐፉ ፅላተ-ሙሴን በዓለም ላይ መፈለጉን ይናገራል። ብዙ ሀገራት ፈልጓል፣ ተመራምሯል። የአርኪዮሎጂ ውጤቶችን የታሪክ ሰነዶችን አገላብጧል። በመጨረሻም ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ኢትዮጵያ ውስጥ ምርምር አደረገ። ወደ አክሱም ፅዮን ማርያም ገደም ሄደ። ቀሳውስቱን አገኛቸው። አወራቸው። ጽላቱ አክሱም ውስጥ ፅዮን ማርያም ቤተ-ክርስትያን ቅፅር ግቢ ውስጥ ባለች ልዩ ህንፃ ውስጥ እንዳለች አስረዱት። ልየው አላቸው። ለማንም እንደማይታይና እጅግ ጥብቅ በሆነ ጥበቃ ላለፉት ሦስት ሺ ዓመታት መኖሩን ነገሩት።
ግርሃም ሀንኩክ የኢትዮጵያን የታሪክ ሠነዶች አየ። ፅላቱ እንዴት ከእየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ መጣ ብሎ ታሪክ ፈተሸ። ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚኖሩት ቤተ-እስራኤላውያን ታሪክም አወቀ። ፅላቱ ከነርሱ ጋር እንደመጣም አመነ። እናም በመጨረሻ ላይ ግርሃም ሀንኩክ ፅላተ-ሙሴን በኢትዮጵያ ውስጥ አገኘሁት ብሎ ፃፈ። ዶክመንተሪ ፊልምም ተሰራለት። በዓለም ላይ እጅግ ከተሸጡ መፃህፍት አንዱ ይኸው The sign & the seal የተሰኘው የግርሃም ሀንኩክ መፅሐፍ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያንም በከፍተኛ ሁኔታ ያስተዋወቀ ነው።
ግርሃም ሀንኩክ በሌሎች ኢትዮጵያውያን በተመለከቱ ዶክመንተሪ ፊልሞች ላይም ማብራሪያ የሚሰጥ ሰው ነው። በዚሁ በፅላተ-ሙሴ ላይ በተሰራ The lost ark of the covenant በተሰኘ ፊልም ላይ ፅላቱ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ተናግሯል። ከዚህም ባለፈ በልዩ ልዩ ታላላቅ ጉባኤዎች ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ይናገራል። Earth Keeper በተሰኘ ዶክመንተሪ ፊልምም የኢትዮጵያ ጉዳይ ይጠቀሳል።
የፅላተ-ሙሴን ታሪክ በተመለከተ አያሌ ፊልሞች ተሰርተዋል። በመሠራትም ላይ ናቸው። አንዳንዶቹ አጨቃጫቂ መረጃዎችን ይዘዋል። አብዛኛዎቹ መረጃዎችና ዶክመንተሪ ፊልሞች ኢትዮጵያ ሚስጢራዊት ሀገር መሆኗን ገልፀው፤ ፅላቱም በዚህችው አገር ውስጥ እንደሚገኝ መስክረዋል። እነዚህ ፊልሞች በጣም ደስ የሚሉ እና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው ናቸው።
ጣና ቂርቆስ ላይ፣ ዝዋይ ሐይቅ ላይ፣ አክሱም ላይ የተሰሩ እጅግ የሚገርሙ ዶክመንተሪ ፊልሞች አሉ። ሁሉም አንድ የሚያደርጋቸው ደግሞ ፅላተ-ሙሴን ፍለጋ ነው። ሌሎች ፊልሞች ደግሞ አሉ። አለምን እየዞሩ መጥተው ኢትዮጵያን ማሳረጊያቸው ያደረጉ። እነዚህን አስገራሚ ፊልሞችን አልፎ አልፎ እያነሳሳሁ አወጋችኋለሁ። የኢትዮጵያ አስተዋዋቂዎች ናቸውና።
ጽዮን ማርያም ከናንተ ጋር ትሁን።