ሀገር አፍራሹ ጭፍራ-ጭፍራ ላይ ዋጋውን አግኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች ኢትዮጵያን እየታደጉ ነው!
(ስናፍቅሽ አዲስ ~ ድሬቲዩብ)
ምን እንደሚፈልግ እንኳን ሌላው ራሱ የማያውቀው ወራሪ በየደረሰበት ግፍ እየፈጸመ፤ ሆዳም ቀጥሮ ሀገር እያፈረሰ፣ የድል ጫፍ ነኝ ባለ ማግስት ሀገር በጋራ ሆ ብሎ ታሪክ ቀይሯል፡፡ ግፉን በመደበቅ የምዕራብ ሚዲያ ተባባሪው ቢሆኑም የራሱን ግፍ እያጋለጠ ነውሩ ይበልጥ ሀገር ወዳዱን አጠንክሮታል፡፡
በአፋር ቆርጦ የጅቡቲን መንገድ እዘጋለሁ በሚል ቅዠት የስንቱን ደሃ ልጅ ነፍስ በበርሃ ከገበረ በኋላ ታሪክ ሰራሁባቸው ያላቸውን ኮረብቶች ታሪክ ተሰርቶበት ለቋል፡፡ በየሜዳው ረግፎ ጭፍራን ለባለቤቱ አስረክቧል፡፡
ጭፍራው ጭፍራን የለቀቀው ከባድ ድል ተመቶ ነው፡፡ አልቆና ረግፎ ምክንያት አልባ በሆነ ትእቢት የደሃ ልጅ አስጨርሶ ድራማውን በመቀየር ደግሞ አክሱም አክሱም ማለት ጀምሯል፡፡ በአክሱም የሆነ የለም፤ የሆነው በገባበት ሸዋ፣ በአወደመበት ወሎ፣ በተመካበት አፋር ግንባር ነው፡፡
ምዕራባውያኑ መስሏቸው ከጎኑ ቆሙ፡፡ እሱ ግን የሀገሩን ጀግኖች እያወቀ ድል የማያደርገውን ጦርነት ሆ ብሎ ገባበት፡፡ ይሄ ጦርነት ውስኪ እየጨለጡ በትግል ዘፈኖች ከሰው እንለያለን እኛ ብቻ ጀግና እንደማለት ቀላል አይደለም፡፡ ይሄ ጦርነት ለሃምሳ ሰዎች ፍላጎት ሚሊዮኖች ለእርድ የቀረቡበት ቁማር ነው፡፡
አንዴ ብልጽግና ሌላ ጊዜ የአማራ አሌቲ ሲያልፍ ደግሞ አብይ አህመድ እየተባለ ከግብጽና ከሱዳን አልፎም ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ቃል ኪዳን በማሰር ሲዖል ድረስ እወርዳለሁ ያለው ሃይል ያለበት ሆኖ አንድ ትውልድ ሲዖል አውርዷል፡፡
የኢትዮጵያ ልጆች እየተዋጉ ያሉት ምክንያታዊ ጦርነትን ነው፡፡ ዘር ላይ ዝተው ሲዖል ገብተን ሂሳብ እናወራርድ በማለት ሆ ብለው የከተቱ አይደሉም፤ ቅጥረኛ የባንዳ ልጆች ተልከው ሀገር እንዳያጠፉ አፍሪካን የታደጉበት ዘመቻ ነው፡፡ ሀቅ ያለው ዘመቻ ስለሆነ ትግሉም ውጤቱም ያኮራል፡፡
እዚያ ማዶ ትግሉም ውጤቱም ነውር በሆነ ጦርነት ህጻናት ልጆችን ለቅመው እሳት ከተው ጨለማ ሊያበሩ ይፈልጋሉ፡፡ ዛሬም በጥላቻ የሰከረ መንፈስ ይዘው በሀሰት የድል ዜማ የደረሱበትን ውጤት ብቻ በማድረግ ገብቶ ስለማይወጣው ሃይላቸው ሳይጨነቁ ሰው እንደ ቅጠል እያረገፉ ነው፡፡
ነገ የትግራይ ህዝብ ይጠይቃል፡፡ ያ ጥያቄ ሊቀርብ ጫፍ ላይ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ትግራይን ለመታደግ አፋርን ወርሮ እንደ ቅጠል መርገፍና መስጂድና ገዳም ዘርፎ ማቃጠል እውነትና ሀቁ የት ጋር እንደሆነ ሲረዳ የሰጠውን ልጅ መልሶ መቀበል ሳይችል ሲቀር የጦርነቱ መልክ ይቀየራል፡፡ ያ ሊሆን ጥቂት ቀርቶታል፡፡ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፡፡