የተገፋን ህዝቦች መሪ ስለሆንክ፤ “ሆ” ብለህ ትመለሳለህ፤ “ሆ” ብለህ በድል!
(ሄኖክ ስዩም ~ለድሬቲዮብ)
ይሄ ምኞት የነጻነት ተምሳሌት ከመሆን ውጪ ዓለምን አንዳች በደል ባልበደለች ደሃ ሀገር ላይ የሆነ ነው፡፡ እናፍርስ ያሉትም አፍርሱ ያሉትም በመኖሯ ቢጠቀሙ እንጂ አይጎዱም ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ተገፍተናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ታርደናል፡፡ ኢትዮጵያውያን መከራ እንዲጫንብን ሴራ ተሰርቶብናል፡፡
በአፋር ሲያርዱን ምዕራባውያን ዓይናቸውን ጨፍነው ነበር፤ በጭና ሲገድሉን፣ በማይካዳር ቤት አቅልመው በደም ሲያቀልሙን አይተው እንዳላየ ሆነዋል፡፡ መሪ አልባ ሀገር አልባ ክብር አልባ ሊያደርጉን ተቀናጅተው አሲረዋል፡፡
ከተራ ሜዳሊያቸው የሺህ አመቷ ኢትዮጵያ እንደምትበልጥብን አልገመቱም፤ ስልጣኔያቸው ስልጡን ህዝብ ሀሳቡ ምን እንደሆነ እንኳን መረዳት አይችልም፡፡ ከፍትፍቱ ፊቱ በሚል ህዝብ ላይ ፍትፍትን መደለያ አድርጎ ሁሉን እንዳልነበረ ማድረግ አይቻልም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነቱን በግንባር እመራለሁ ሲሉ እዋጋለሁ ብሎ መንደር ከሚያወድመው ሽፍታ በላይ የመረረው የምዕራቡ ዓለም ነው፡፡ በኖቤሉ ሊሳለቅ ሞከር፡፡ ያ ኖቤል የአባ ገዳ ምርቃትን ያህል ቦታ እንደሌለው እንኳን አያውቅም፡፡ የኢትዮጵያ እናቶችን ጸሎት ያህል ስፍራ አግኝቶ በተደጋጋሚ እንዳልተኮራበት አልሰሙም፡፡
ሰብሉን ታጭዶ፣ ቢርመው የማያርደው ጥማዱ ተበልቶ፣ ሚስቱ ልጆቹ ፊት ተደፍራ ዓለም አላየም አልሰማም፡፡ የምዕራባውያን ፖለቲካ ቆሻሻ ነው፡፡ በሰለጠኑ ከተሞች የሚኖሩ ኋላ ቀር ቁማርተኞች እንደሆኑ በታሪክ ፊት ዳግም ማንነታቸውን አሳይተዋል፡፡
ጠቅላዩ የተገፋ ህዝብ መሪ ናቸው፡፡ አራት ኪሎን ለመታደግ ሳይሆን በኢትዮጵያ የተሴረውን ቁማር ለመበጠስ ግንባር እወርዳለሁ ብለዋል፡፡ በፈረሶቻችን አንታመንም፣ በሠራዊታችን ብዛት አንመካም፤ ይሄ ሁሉ ከፍትህ የመጣ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ለምን ሆነ ከሚል እዚህ የደረሰ ነው፡፡ የተገፋን ህዝቦች ነን፡፡
እረፍት በሌለው ስካር የሉዓላዊ ሀገር ውስጥ ጉዳይ ነው ብለው ለማሰብ በሚከብድ ሁኔታ በማያጋባቸው እንኳን አፍጋን ተጠራርተው እንዳልገቡ፣ በማያጋባቸው እንኳን ሃያላኑን ስልጡን ሀገራት ጭምር አብረው ቆመው እንዳላፈረሱ፣ አፍሪቃን እንዳላባሉ ሰው በሀገሩ የሆነውን ለመኮነን በሳምንት አስር ቀን እየተሰበሰቡ ሲያደቡብን ሰንብተዋል፡፡
የፌዴራሊዝማችን ጠበቃ የረሃባችን ተሟጋች መስለው ቆመዋል፡፡ ሊቢያን ለማፍረስ፣ ኢራቅን ለማውደም፣ ስንት ንጹህ ሙስሊም ለመፍጀት፣ ጥቁር ለማሸማቀቅ እጃቸውን የከተቱ የኖቤል ተሸላሚዎች አጀንዳ ባልሆኑበት ሚዲያ ሀገሩን የሚያድን መሪ ለማሸማቀቅ ሞክረዋል፡፡ ሽርጥ ለብሰው መዋጋት እስኪቀራቸው የቻሉት አድርገዋል፡፡
ግን የተገፋን ህዝቦች ነን፡፡ ጠቅላያችን የተገፉ ህዝቦች መሪ ነው፡፡ ግንባር ገብቷል፡፡ ነገ አፍሪቃ የሚያሞግሰውን የሉዓላዊነት መርህ የግንባር ስጋ ሆኖ ተጋፍጧል፡፡ በድል ይመለሳል፡፡ ሆ ብሎ በድል ይመለሳል፡፡
ያኔ ከአሸነፈ ሀገር ጋር መቆም መላው የሆነ ዓለም ደግሞ ሌላ ሽልማት ታቅፎ ይመጣል፡፡ አባቶቻችን ታላቅ ሀገር የሸለሙን ህዝቦች ነን፡፡ ሽልማታችንን ለሽልማታችሁ ብለን አናስነካም፡፡ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፡፡