ሰው በሚታረድበት ሀገር የአህያ እርድ፤
ክምር እህል በሚቃጠልበት ደግሞ የአንጀታችሁ መቃጠል አያሳስባችሁ!
(ስናፍቅሽ አዲስ~ ድሬቲዩብ)
ሰሞኑን በፖለቲካው አንጀቴ ተቃጠለ የሚለውን ሰው እያየን ነው፤ ከእኛ አንጀት መቃጠል በላይ ለአንጀታችን መቃጠልም ቢሆን በጣም የሚያስፈልገን እህል በተከመረበት የሚቃጠልበት ክፉ ጠብ ላይ ደርሰናል፡፡
እውነት ለመናገር ሁሉንም ጉዳይ ፖለቲካ ማድረግ ያከስረናል፡፡ እንዲህ ያለውን ረብ የለሽ ጉዳይ ከፖለቲካ ባሻገር ብንመለከተው መልካም ነው፡፡ አለቃ ገብረ ሃና ናቸው እዚያም ቤት እሳት አለ ያሉት፤
ሰዎች በዚህ ደረጃ አእምሯቸው ታውኮ የሚፈጽሙትን ተግባር ፖለቲካ አድርገንው ካረፍን ኪሰራው ይጨምራል እንጂ አይቀንስም፡፡ ሀገር ተርቦ የትኛው ፖለቲከኛ ጠግቦ ሊያምሰን ነው፡፡ እንደ በጥባጭነት ጥጋብ የለም ለመጥገብም ደግሞ እህል መኖር አለበት፤ እራሱን ለማስራብ ያበደ አረመኔ የፈጸመውን ሁሉ ከፍ ያለ ስምና ማዕረግ ከሰጠነው ችግሩን አንፈታውም፡፡
አጀንዳዎቻችን ፍሬ አልባ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር እየታረደ አህያ እርድና ቄራ ላይ እንነታረካለን፡፡ ሰው በታረደባት፣ ገበሬ በየሜዳው በሚወድቅባት ሀገር ቅድስና ፍለጋ የአህያ ደም አይፍሰስ ማለት መዘባበት ነው፡፡
ሁሉ ከሰከረ መንግስትም ቢሆን አብሮ ይሰክራልና አንዳንዴ ስካር የፈጠራቸው አረመኔ ድርጊቶችን በስካር አይን መመልከቱ ለማንም አይጠቅምም የሃምሳ ሰው ሞትን ብንነግድበት ሃምሳ ህይወት አንመልስም ይልቁንም መቶና ሁለት መቶ እንጨምራለን፡፡
በወለጋ እየሆነ ያለው የታወቀ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የኦሮሚያ ብልጽግናን ለማዋረድ አማራውን መርጦ መግደል የሚል መርህ ያለው ጨካኝ እድሉን እየሞከረ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት እጁ እንዳለበት አድርጎ ማንጫጫት ያስተዛዝባል እንጂ ውጤት አያመጣም፡፡ የኦሮሚያ ልዩ ሃይልም እኮ በአሁን ሰዓት ለሀገር ጥሪ ምላሽ ሰጥቶ ግንባር አለ፡፡
ወቅቱ ፈተና የበዛበት ነው፡፡ አማራ እንኳን ወለጋ ጎንደር ከተማ ውስጥ እየታፈነ እንደሆነ ለማወቅ ሌላ ምርምር አይፈልግም፡፡ መፍትሔውስ እየሆነ ያለውን ለመመከት በሁሉም አቅጣጫ እጅ ለእጅ መያያዙ እንጂ በየምክንያቱ አትንካኝ መባባሉ አይደለም፡፡
የወለጋዋ ሞት መቀሌ የተጸነሰች ናት፡፡ ይሄ ምስጢር አይደለም በአደባባይ ሀገርም ዓለምም እየሰማ የተነገረ በመግለጫ ያታወጀ የህብረት ስምምነት ውጤት ነው፡፡ ጠላቶቻችን ሳያንሱ እርስ በእርስ መጓተቱና መጠላላቱ የትም የማያደርስ ነው፡፡
አሁን በኢትዮጵያ እኮ ማንም ከማንም ጋር ተቃራኒ የሚቆምበበት ምዕራፍ አይደለም፡፡ ችግሩና መከራው አይሏል፡፡ በጣም አሰቃቂ በሆነ አብሮነትንና መደማመጥን በሚፍልግ ምዕራፍ ላይ ነን፡፡
ቃልም ተግባርም ጥሩ የሚሆነው ውጤት ሲያመጣ እንጂ እሳቱ ይበልጥ ለማንደድማ የለኮሱት ይበቃሉ፤ እነሱን መተውና አለመታገል ብቻውን በቂ ነው፡፡ ግን በእያንዳንዱ የሰከረ ፖለቲካ ሳቢያ ብዙ ነፍስ እና የንጹሃን ህይወት እንደ ቀልድ እየወደቀ ነው፡፡ እነሱን የማይታደግ ቀረርቶ፣ መግለጫ፣ ኩርፊያ፣ ከመንግስትም ይመጣ ካኮረፈ ተቃዋሚ ትርጉም የለውም፡፡
ነውራችንን አለማዘመኑ ይሻለናል ምክንያቱም እንዲህ ያለው ተግባር ፖለቲካ አይደለም፡፡ መታመም ስለሆነ ተገቢውን ህክምና ተገቢውን በአንድነት መታገልና እስከመጨረሻው ለመዳን መሞከር እንጂ ዘናጭ ስምና ከፍ ያለ ክብር እየሰጠን ትንሹን መከራ ይበዛ ዘንድ እራሳችኑ ስልት አንንደፍለት፡፡