ʺሀገርህን ከወደድካት ወታደር ሁንላት” …
በአንድ አዋጅ መሰባሰብ፣ በአንድ ልብ ማሰብ፣ በራስ ትጥቅ፣ በራስ ስንቅ ስለ ሀገር መዋደቅ፤ ኢትዮጵያዊያን ሀገር ተነካች ሲባል ልጆቻቸውን በቤት፣ ከብቶቻቸውን በበረት እንደዘጉ ስለ ሀገር ይዘምታሉ፡፡ ስለ ክብር ይሞታሉ፣ ስለ ነጻነት አትንኩን እያሉ ይፋለማሉ፡፡ ድንበር አልፈው አይነኩም፤ ድንበር አሻግረው አያስነኩም፤ የሀገር ፍቅር ገመዳቸው፣ ኢትዮጵያዊነታቸው፣ አንድነታቸውና አይደፈሬነታቸው ሁልጊዜም ያስደምማል፡፡
ጠላት በአራቱም ንፍቅ ቢመጣ በአራቱም እየዘመቱ፣ ሁሉንም እየመቱ፣ ሁሉንም እየረቱ ይመልሳሉ፡፡ ዳር ድንበሯንም ያስከብራሉ፤ ገና ቀደም ባለው ጊዜ ታንክና ብሬን ባልተጫነበት፣ የዘመነ መሳሪያ ባልነበረበት፣ መገናኛ ራዲዬ ባልተገጠመበት፣ በሰማይ የሚበር፣ በምድር የሚሽከረከር መዋጊያ ባልታሰበበት ዘመን ኢትዮጵያዊያን በጋሻ መክተው፣ በጦር ወግተው ጠላታቸውን መልሰዋል፡፡ ለዚያም ነው ʺአይ ያለ ችግር ያለ መከራ፤ ጥይት ቢያልቅበት አለው በከራ” ተብሎ የተገጠመላቸው፡፡
በቀደመው ዘመን ኢትዮጵያውያን ስለሀገር ፍቅር ካላቸው ከፍ ያለ ስሜት የተነሳ ሀገር ተነካች ሲባል የጦር መሪውን ʺእባክዎን አብረን እንዝመት” እያሉ ዘምተዋል፡፡ ለጦርነት ይማፀናሉ፤ ሞተው ሀገር ለማስከበር መዝመትን ይለምናሉ፤ የጦርነት አዋጅ ከተነገረማ ደስታው ወደር የለውም፤ ስንቃቸውን ቋጥረው፣ ሳንጃቸውን ስለው፣ በባዶ እግራቸው ኑ ወደ ተባሉበት ሥፍራ ይዘምታሉ፡፡
የሀገራቸው ፍቅር ምን ይደንቅ፣ የጀግነታቸው ልክ ምን ይልቅ አጀብ ነው፡፡ ሳይከፈላቸው ዋጋ ይከፍላሉ፤ ሕይወት ሰጥተው እውነትና ነጻነት ለማቆዬት ይፋለማሉ፡፡ እውነት፣ ጀግንነት፣ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት አላቸውና ሁሉንም ያሸንፋሉ፡፡ የሀገሬው ገበሬ በሰላም ጊዜ አራሽ፣ በከፋ ጊዜም ተኳሽ ነው፡፡ እርሶ ያበላል፣ ተኩሶ ሀገርና ድንበር ያስከበራል፣
ʺበግራው አራሽ በቀኙ ተኳሽ፣ ገፍቶ የመጣን ጠላትን መላሽ” የሚባልላቸውም ለዚህ ነው፡፡
አንድርዜይ ባርትኒስኪ እና ዮአና ማንቴል ኒችኮ የተባሉ የታሪክ አጥኚዎችን ዓለማየሁ አበበ የኢትዮጵያ ታሪክ; ብለው በተረጎሙት መጻሕፍ የታሪክ አጥኚዎቹ ስለ ኢትዮጵያ እንዲህ ብለዋል፡፡ ʺኢትዮጵያ እጅግ አስደናቂና ልዩ ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡
ለብዙ ምዕተ ዓመታት በአፈ ታሪካዊ ብሂሎች ታጅባ የኖረችው ኢትዮጵያ ምንጊዜም የተመራማሪዎችን ቀልብ ስታማልል ትኖራለች፡፡ ገና ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአውሮፓ ዝናዋ ይታወቅ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ አያሌ ምዕተ ዓመታት ከተቆጠረ በኋላ የጨለማው ዘመን ተገፍፎ የሀገሪቱ ትክክለኛ ገጽታና እውነተኛ ታሪኳ ሲታይ በወሬ ሲነገር ከኖረው የላቀ ሆኖ ተገኘ፡፡
ስዝንዝር በማያላውሰው የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ተራሮች ውስጥ የምትገኘዋ ኢትዮጵያ ብዙ ምዕተ ዓመት ባስቆጠረው የነጻ መንግሥትነት ታሪኳ ውስጥ አንድ ልዩ ስልጣኔ ፈጥራለች፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ በዓለም በየትም ሀገር የማይገኘው የጽሑፍ ጥበቧ ለዚህ አንድ ምስክር ነው፡፡ የነጻ መንግሥትነት ፖለቲካዊ ታሪኳ ከሀገራዊ ትውፊት መሠረት በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡
ሠፊውና ደማቁ ፖለቲካዊ ታሪኳ አንድ ወጥ የሆነው ጥንታዊ ስልጣኔዋ በአፍሪካ ውስጥ አምሳያ የሌለው ውስጣዊ አደረጃጀቷና እንደዚሁም በዓለም ውስጥ ከማንኛውም ሀገር ለበለጠ ዘመን ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገር መሆኗ ኢትዮጵያን ያለ ጥርጥር አስደናቂ ከሆኑ ሀገሮች አንዷ እንድትሆን አድርጓታል፡፡” በሳል መሪ፣ ብልህ ተመሪ፣ ጀግና የጦር መሪ ስለ ነበራት ነው ኢትዮጵያ ከፍ ያለች ሀገር የሆነችው፡፡
ዘመን ዘመንን እየተካ ሄደና ኢትዮጵያ ዘመናዊ ወታደር አቋቋመች፤ ወታደሩም በካምፕ የሚኖር፣ ደሞዝ የሚከፈለው ሆነ፡፡ ያም ሆኖ ግን የጨነቀ ዘመን ሲመጣ በሰላም ጊዜ የሚያርሱትን አርሶ አደሮች መጥራቱ አይቀርም፤ ለሀገር ከወታደር በላይ ራሱን የሚሰጥ ያለ አይመስልም፣ ሌላውም ባለሙያ ለሀገሩ ጠቃሚ ቢሆንም እውቀቱንና ጉልበቱን ከሚሰጣት ሕይወቱን የሚሰጣት ይልቃል፡፡
በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ጠላቶች መልካቸውንና ግብራቸውን እየቀያየሩ አልተኙም፡፡ የኢትዮጵያን ጠላቶች ለመጠበቅ ደግሞ የሰለጠነ ወታደር ያስፈልጋታል፡፡ ኢትዮጵያም ለመከበር ስትል ወታድር ሆነው ልጆቿ እንዲጠብቋት ስትጣራ ትታያለች፡፡
በቀደመው ዘመን ሀገሩን እያሰበ፣ አርበኛ ሆኖ ጠላቱን ለመመለስ እያለመ ከልጅነት ጀምሮ ወታደር መሆንን ይለማመዳል፤ ዘመቻ ይማራል፡፡ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ወታደር እንዲሆኑ የምትጠራቸው ልጆቿ የሚሄዱት ጥቂቶች ናቸው፡፡ የበረሃው ወታደር መስዋእትነትን ይፈልጋልና፡፡
የበረሃው ወታደር ይጠብቃታል፤ ሀገርህን ከወደድካት ወታደር ሁንላት፤ ወታደር ስትሆን ድንበር ትጠብቃለህ፣ ክብር ታስጠብቃለህ፣ ታሪክ ሠርተህ ታሪክ ታስቀጥላለህ፤ ስምህንም በታሪክ መዝገብ ላይ ጎላ አድርገህ ትፅፋለህ፡፡
ከ1982 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመሆን አገልግለዋል፡፡ በውትድርና ሕይወታቸው ኢትዮጵያን ዞረዋል፡፡ በጎረቤት ሀገራትም ግዳጅ ተወጥተዋል፡፡ ስለ ሀገራቸው ያላቸው ፍቅር የአንድ ወጣት እድሜ በሚሆነው የወትድርና ሕይወት አሳይተዋል፡፡ ኮሎኔል ደሴ ሞላ ይባላሉ፡፡
ወታደር ታዛዥ፣ ለመለዮው እና ለሀገሩ ክብር የሚሰጥ፣ የሀገሩን ዳር ድንበር ለመጠበቅ ሕይወቱን ለመስጠት የተዘጋጄ ነው ይላሉ፡፡ ሀገር ካለ ወታደር መኖር አትችልም፤ ወታደር ለሀገር አለኝታና ዋልታ ነውም ብለውኛል፡፡ ሕዝብ በሰላም እንዲኖር ግዴታ ወታደር መኖር አለበት፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ ኢትዮጵያን መሠረት ያደረገ ውትድርና ወይም ዘመቻ ስለነበር ኢትዮጵያዊያን ለውትድርናው ትልቅ ፍቅር ነበራቸው፡፡ በተለይም ከደርግ መውደቅ በኋላ የተቀበለው ሥርዓት ወታደሩን የገነባበት መንገድ ከሀገር ይልቅ ለተለዬ ዓላማ ማድረግ ወጣቱ ለውትድርና ፍቅር እንዳይኖረው አድርጓል፡፡ በወታደራዊ ተቋሙ የአያያዝ ችግር መኖር፣ የአንድ ብሔር የበላይነት መኖርና የገዢዎችን ዓላማ ማስፈጸሚያ የማድረግ ችግሮች እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡
ግን አሉ ኮሎኔል ደሴ ውትድርና እንቅፋቶች ያጋጥሙታል፤ እንቅፋቶቹን እያለፈ መሄድ መቻል ነው፡፡ ችግሮች ፍቅሩን ሊቀንሰው አይገባም፡፡ አሁን ላይ የወታደራዊ አደረጃጄት ማሻሻያ መደረጉንና የቀድሞ ችግሮች መፈታተቸውንም ነግረውኛል፡፡ ወጣቶች ወታደር ሆነው ሀገራቸውን እየጠበቁ ጀብዱ ከመፈፀም ባለፈ የሥራ ዕድል መፍጠሪያና ራስን ማሳደጊያ መሆኑንም ነግረውኛል ኮሎኔል ደሴ፡፡
በተቋሙ ውስጥ የተለያዩ የትምህርት እድሎች ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡ እናት አባቶቻችን በጦር፣ በጎራዴ ነው ጠላትን የመለሱት ያሉት ኮሎኔል ደሴ ከሁሉም በፊት ሀገር የሚለውን በማስቀደም ወታደር መሆን አለባቸው ነው ያሉት፡፡
የኃይል ሚዛን እንዲስተካከል፣ ሀገር እንድትቀጥል ወጣቶች ወታደር መሆን ይባቸዋልም ብለዋል፡፡ ሀገሬን እወዳለሁ የሚሉ ወላጆች ልጆቻቸውን መርቀው ወታደር እንዲሆኑ መሸኘት እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት፡፡
የአማራ ሕዝብ ከነብሱ አብልጦ ኢትዮጵያን ይወዳታል፤ ይህን ፍቅሩን የበለጠ ከፍ ለማድረግ ደግሞ ወታደር ሆኖ ሀገሩን ሊጠብቅ ይገባልም ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ለሀገሩ ያለውን ከፍ ያለ አስተዋፅዖ ለማስቀጠልና ኢትዮጵያን ለመጠበቅ በወታደር ውስጥ የሚጠበቅበትን ማድረግ እንደሚገባውም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገሩን የሚወድ ወታደር እንዲኖራት ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆ ከልጅነት ጀምሮ መሰጠት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ከፍ ያለ ሥራ መሠራት እንዳለበትና ውትድርና ዋስትና መሆኑ መታወቅ እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡
ውትድርና ለሀገር፣ ለፍቅር፣ ለክብር፣ ለእንድነት፣ ለጽናትና ለኢትዮጵያዊነት መሰጠት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፈተናዎች የታለፉት ሀገሬን በሚሉ ወታደሮች ነው፡፡ አሁንም ፈተናዎችን ለማለፍ እንደ ቀደሙት መሆን ይገባል፡፡ ለሚወዱት የሚነፍጉት የለምና ለሚወዷት ሀገር ያለን መስጠት ነው፡፡
#አሚኮ (በታርቆ ክንዴ)