Connect with us

 ጉራማይሌ ዜና—ዥንጉርጉር ስሜት

ጉራማይሌ ዜና---ዥንጉርጉር ስሜት
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

 ጉራማይሌ ዜና—ዥንጉርጉር ስሜት

 ጉራማይሌ ዜና—ዥንጉርጉር ስሜት

(ጌታሁን ሄራሞ)

  እውነት ነው፣ ሀገራችን በብዙ አቅጣጫ በአያሌ ተግዳሮቶች እየተፈተነች ያለችበት ወቅት ነው፣ በዚህ ወቅት እያንዳንዷን ስህተት በአደባባይ እየነቀሱ አንድነታችንን የሚፈታተን አቋም ከመያዝ ይልቅ ለሀገር ደህንነት አጀንዳ ቅድሚያ ሰጥቶ መንቀሳቀስ ግዴታችን ነው። 

ሆኖም ይህን ውሳኔ የሚፈታተኑ ተግባራት በተለይም “መንግስታዊ” ተብለው በሚጠሩ ሚዲያዎች ጭምር ከዜና አቀራረብ ረገድ ሲከወን እያስተዋልን ነው። ለምሣሌ ከአንድ ቀን በፊት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አንባቢውን በጥያቄዎች ወጥሮና አጭቆ የሚሸኝ ዜና በገፁ ላይ ለጥፎ አስነብቧል። የዜናው ርዕስ፦ “አሸባሪው ህወሓት ዳሎልን ለመቆጣጠር ያደረገው ሙከራ በአፋር ክልል ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ ከሽፏል” የሚል ነው።

በዚሁ ዜና ብዙም ሳይቆይ በሁለተኛው ዐ/ነገር ላይ “የሽብር ቡድኑ በበርሃሌ ወረዳ በርካቶችን ገድሏል፣ አቁስሏል፣ ከቤት ንብረታቸው፣ አፈናቅሏል፣ ቅርሶችንም አውድሟል፡፡” የሚልና አንባቢው ተገኝቷል የተባለውን ድል በቅጡ ሳያጣጥመው ሐዘን ውስጥ እንዲዘፈቅ የሚያደርግ ሌላ መርዶ ይነገረዋል። በተለይም “በርካቶችን ገድሏል” የሚለውን ሐረግ አስምሩልኝ። ይህም ብቻ አይደለም፣ ተገኝቷል በተባለውም ድል ብቸኛው ተሳታፊ የአፋር ልዩ ኃይል እንደሆነ እና ይህም የአፋር ልዩ ኃይል በትጥቅ አደረጃጀት አኳያ ከሕወሓት ልዩ ኃይል ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የማይባል “አነስተኛ መሳሪያ” እንደሆነም ፋና ብሮድካስትንግ ዘግቦልናል። ይህን ዜና ያነበበ ወይም ያዳመጠ ታዳሚ በአዕምሮው እነዚህ ጥያቄዎች ባይፈጠሩ ይገርመኛል፦ 

  1. አንዳንድ ብዥታ የሚፈጥሩ ዜናዎች ዜጎች ከሙያቸው ውጪ የሆኑ ጥያቄዎችን እንዲጠይቁ እያስገደዳቸው ይገኛል። ለምሣሌ ያህል የውትድርና ሳይንስ አነስተኛ መሳሪያ የታጠቀ የወገን ጦር እስከ አፍ ጢሙ ዘመናዊ መሳሪያን ከታጠቀ የጠላት ጦር ጋር መፋለምን የቱን ያህል ይደግፋል? አሁን አሁን ፋናም በአደባባይ እንደነገረን “በአነስተኛ መሳሪያ” መፋለም እንደ መርህ እየተቆጠረ ያለ ይመስላል። ከጦርነቱ በፊት የወታደራዊ መረጃና ደህንነትም ይሁን የብሔራዊ ደህንነት አካላት በየግንባሩ ሕወሓት ልዩ ኃይልን ያስታጠቀችው ትጥቅ ምን እንደሆነ አነፍንፈው አይደርሱም ማለት ነው? የሚገርመው ፋና ብሮድካስትንግ በዜናው ላይ የሕወሓት ተዋጊ የታጠቀውን መሳሪያ ያሞካሸው “ከባድ መሳሪያ” በማለት ነው።
  2. ሌላው ግራ የሚያጋባው ሕወሓት “በበርሃሌ ወረዳ በርካቶችን ገድሏል…” ተብሎ የተዘገበው ነው። ይህ የሕወሓትን ወንጀል አመላክቶ የፈፀመችውን ግፍ ለዓለም መንግስታት ለማሳወቅ ሲባል የተለቀቀ ዘገባ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አገላለፁ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚፈጥረው አሉታዊ ስሜት ለምን ከግምት አልገባም? ለምሣሌ በበርሃሌ ወረዳ በርካቶች የተገደሉት ፣ የቆሰሉትና የተፈናቀሉት ፋና በሰጠን ፍንጭ መሠረት የሕወሓት ተዋጊ የመሳሪያ ብልጫ ኖሮት ነው? በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች በዜጎቻችን ላይ  በሕወሓት በሚፈፀሙበት ወቅት የጥቃት አድራሾቹን ለማሳነስ ሲባል ጥቅም ላይ የምትውል “ሰርጎ-ገቦች” የምትባል ጣምራ ቃል አለች። 

በእኔ ምልከታ ዋናውን ትኩረት መሳብ ያለበት ጥቃቱ የተፈፀመው በሰርጎ-ገቦች ወይም በማካይነዝድ ጦር መሆን አለመሆኑ ሳይሆን የደረሰው የጥቃቱ መጠን መሰለኝ…ፋና የነገረን “በርካቶች ተገድለዋል” የሚለው!!! እናም ዜጎች ስለ ድሉ ሲነገራቸው በድሉ የሚፈነጥዙትን ያህል ስለ ሽንፋቱ ዜናው ሲነገራቸው “ለምንና እንዴት?”  ብለው በሚጠይቁበት ወቅት “ይህ የሠራዊቱ ድርሻ ነውና አርፋችሁ ዝም ብላችሁ ተቀመጡ” ሊባሉ ዘንድ አይገባም። ዜናው የተሰናዳው ለዜጎች መሰለኝ። የሰው ልጅ ደግሞ ከሰማውና ካዳመጠው ነገር ላይ ተንደርድሮ ብዥታን በፈጠረበት ጉዳይ ላይ ጥያቄን መጠየቁ ተፈጥሮአዊ ነው። 

 

  1. ከላይ እንዳስቀመጥኩት ድል እንደተገኘ በተነገረው ግንባር ጦርነቱ የተካሄደው በአፋር ልዩ ኃይል ብቻ ነው። ማለትም መከላከያ ጦርነቱ ላይ እንደተሳተፈ ዜናው ላይ አልተነገረንም። ባለፈው አንድ የአማራ ክልል ባለሥልጣን ከሕወሓት አዋጊ ጋር ያደረገው የስልክ ልውውጥ ነው ተብሎ የተለቀቀው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ የሕወሓት አዋጊው መረጃውን አሳልፎ የሰጠውን ሰው በተደጋጋሚ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ነበሩ። 

የመጀመሪያው በዚያ መስመር  የመከላከያ ሠራዊት ይኑር ወይ አይኑር ሲያጣራ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ስለ ትጥቁም ዓይነት አጥብቆ ሲጠይቀው ነበር። ይህ የሚያመለክተው ወያኔ ጥቃቱን ከመሰንዘሯ በፊት ስስ ጎኖችን በደንብ እንደሚታጠናቸው ነው። ይህ የውትድርና ሳይንስ “ሀሁ” መሰለኝ።  በተለይም ወያኔ ልዩ ኃይልን ለብቻው መፋለም ቀደሚ ምርጫዋ እንደሆነ ይታወቃል። ምናልባትም ፋና ብሮድካስትንግ ኮርፖሬሽን በበርሃሌ ግንባር “በርካታዎች እንደተገደሉ” የነገረን ዜና ሕወሓት ስስ ጎን መሆኑን አጥንታ የፈፀመችው ጥቃት ይሆን? 

 ስለዚህም መንግስትም ይሁን የመንግስት ሚዲያዎች በሕዝቡ ዘንድ ብዥታንና ስጋትን የሚረጩ መረጃዎችን ከመልቀቅ መቆጠብ አለባቸው። አደናጋሪ መረጃዎችን ከሰጡ በኋላም ሕዝቡ ያለ ሙያው ዳራ በግምቶች ተሞልቶ በሴራ ትንተና ውስጥ ከገባም አትፍረዱበት። ቢያንስ ሕዝቡ ያለ ፍላጎቱና ምርጫው በሴራ ትንተናው ውስጥ እንዲገባ በማድረጉ ሂደት የናንተም አስተዋፅኦ አለበት። ጉራማይሌ መረጃዎችና ዜናዎች ታዳሚው ዘንድ ሲደርሱ ዥንጉርጉርና ባለብዙ መልክ ስሜት መፍጠራቸው ልደንቀን ዘንድ አይገባም። 

ሰናይ ሰኞና ሳምንት ለኢትዮጵያ!!!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top