ሠላምን የሚወዱ፤ የሚያሸንፉትን ጦርነት የሚጠየፉ፤ ሀገር ሰሪ፤ የአፍሪካ ኩራት፤ እንኳን ተወለዱ!
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
ዛሬ የንጉሠ ነገሥታችን የዳግማዊ ምኒልክ ልደት ነው፡፡ ንጉሥ ሆይ እንኳን ተወለዱ ብለናል፡፡ ጦርነትን ቢያሸንፉት እንኳን ደም አይፍሰስ ብለው የሚማጠኑ ሠላም ወዳዱ ንጉሣችን ሀገር ሰርተዋል፡፡ ለአፍሪቃ ምልክት የምትሆን ሀገር ሰርተዋል፡፡ ሥልጣኔን ከዘመናቸው ቀድመው ከሀገራቸው አስተዋውቀዋል፡፡
ዛሬ ሁለት ልደት ነው፡፡ የንግሥታችን የእቴጌይቱም ልደት ነው፡፡ ጣይቱ በደብረ ታቦር ምኒልክ በአንጎለላ የተወለዱበት፡፡ ምኒልክ ዛሬም ንጉሥ ነው እንዳለው ከያኒው፤ አሁንም አፍሪቃ ስለ ክብራቸው ክብር ይሰጣል፡፡ ዛሬም የጥቁርን ታሪክ የሚያጠኑ የዓለም ሊቃውንት ከቀለማቸው የተናቀውን ቀለም ክብር ይፈልጉታል፡፡ እሳቸው እምዬ ናቸው፡፡
ዘመን አልፏል፡፡ ታሪክ ግን ከወርቃማው ስፍራ አላወረዳቸውም፡፡ በህዝቦች መካከል ጥላቻን አንግሰው መኖር የፈለጉ ፖለቲከኞች ዛሬን ከመስራት ይልቅ ትናንትን ለማውራት ምክንያት አድርገው በጥላቻ ያጠፉት ስማቸው ይበልጡኑ በየቀኑ ከፍ ባለ ክብር ስማቸው ገኖ ይኖራል፡፡
ምኒልክ ዛሬ ያላሳካነውን የፌዴራሊዝም ሥርዓት እውን ያደረጉ፣ በኩሩ ነገሥታት ታጅበው ንጉሠ ነገሥት ለመባል የበቁ፣ ሀገር ሰርተው፣ የዓለምን ጥቁር ያኮሩ፤ ሀገር ከወራሪ አድነው ስማቸው በድል አድራጊነት የሚነሳ ንጉሥ ናቸው፡፡
ደግሞ ይቅር ባይ፤ ጦርነት ገጥመው ድል ያደረጉትን እንኳን እግዚሐር አተረፈህ የሚሉ፤ ለሰልፉና ለጦርነቱ ሳያንሱ ደም አይፍሰስ ብለው የሚለማመጡ፤ ሰላምን ከሁሉ የሚያስቀድሙ፤ ህዝባቸውን በአዋጅ አስቀይሜህ አላውቅም ብለው በእርግጠኝነት የሚናገሩ፡፡ እናም ዛሬ የእሳቸው ልደት ነው፡፡
በየዓመቱ ይህንን ቀን ፈረሰኛ ኦሮሞዎች በጉግስ ያከብሩታል፡፡ ይሄንን ማየት የሚሻ ፊታውራሪ ገበየሁ ቀዬ ብቅ ይበል፡፡ እምዬ ናቸዋ፤ ከባልቻ ጋር ሆነው ሀገር የሰሩ፤ ከአባ መላ ጋር ሆነው ትልቅ ድል እውን ያደረጉ፡፡ ስመ መልካም፡፡ እምዬ፤
ዛሬ የእሳቸውም የባለቤታቸውም ልደት ነው፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ልደትም ነው፡፡ ንግሥቲቱ መለኛ ናቸው፡፡ ከንጉሠ ነገሥቱ ድንቅ ስኬት ጀርባ ያለ ብርቱ መካሪ፤ ደግሞም ጦረኛ፡፡ ደግሞም ዲፕሎማት፣ ሥራ ፈጣሪም ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሆቴል ኢንዱስትሪ መሥራች፡፡ እቴጌይቱ፤ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ፡፡ የጁዋ፣ ጎጃሜይቷ፣ ስሜነኛዋ፣ በጌምድሯ፣ ኢትዮጵያዋ፤ አፍሪቃይቱ፤ ሰማይ የተሰቀለችው፡፡ ጠሐይቱ፡፡ ጣይቱ፡፡
ዛሬ የታላቁ የጦር ገበሬ የምኒልክ ዘመን ሰው፤ የፊታውራሪ ገበየሁ ጎራው ልደትም ነው፡፡ አንጎለላ መልካሟ ምድር እልፍ ፍሬ ያፈራችበት፤ ሀገር የወለደችበት፤ የሀገር እትብት የቀበረችበት ቀን፡፡ የጀግኖቻችን ልደት ዝም ብሎ ቀን አይደለም፡፡ ሀገር ተወልዶበታል፡፡ የሀገር ልደት ነው፡፡ ሀገር ይኮራበታል፡፡ ሀገር ክብርና ዝና የወለደችው እንዲህ ያሉ ለሀገርም ለአህጉርም የሚሆኑት ስለተወዱበት ነው፡፡ መልካም ልደት ለሀገር ሰሪዎቻችን፡፡