የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግምገማ
– ከላይ ወደታች ወይስ ከታች ወደላይ?
– ይብሰል ወይስ እንደጋመ ይቀጥል?
(ጋዜጠኛ ውድነህ ዘነበ)
ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች የከተማውን ቁልፍ በተረከቡ ማግስት በመሬት ዘርፍ ጠንከር ያለ ግምገማ ማካሄድ ፈልገው ነበር። ነገር ግን ግምገማው በከፍተኛ አመራሩ ተጀምሮ (ከላይ) – ከላይ ከላይ ከላይ ..ተካሄደና የጤሰውን ያህል ሳይነድና ፣ ብዙም ዱላ ሳያሳርፍ ከሽፏል።
በወቅቱ የተስተዋለው ችግር ኃላፊዎች ለተመደቡበት ተቋም ብቁ ያለመሆን፣ ተቋማት ህልውና ኖሯቸው በህግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ባግባቡ እንዳይወጡ ሽባ መደረጋቸው፤ ለብልሹ አሰራር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ኋላ ላይ በግልጽ ተስተውሏል።
ባለፈው አመት ግምገማ በተለይ ከመሬት ጋር ተያይዞ ሌብነት አለ ይሉ የነበሩ አመራሮች ብቅ ቢሉም፣በወቅቱ ቁንጮ የነበሩ አመራሮች “ሀሜት” በሚል እንዲታለፍ አድርገዋል ፣ ሌብነት አለ ያሉትንም በዘዴ ዞር እንዲሉ መደረጋቸው ሲነገር ቆይቷል።
ከቀድሞው ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አንፃር ሲታይ አዴ አዳነች ለአልሚው ማህበረሰብ መሬት ሰተዋል ማለት አይቻልም። በጨረታም ቢሆን መሬት ሳይቀርብ አዲሱ የበጀት አመት ጠብቷል።
በነገራችን ላይ የሊዝ አዋጁ ህዳር 2004 ከወጣ ጊዜ ጀምሮ መሬት በግልፅ መንገድ እየተሠጠ ነው ማለት አይቻልም ። አዋጁ የፀደቀ ሰሞን በየወሩ መሬት ለጨረታ ይቀርባል ተብሎም ነበር። ነገር ግን መሬት ለጨረታ የቀረበበትን ጊዜ ወደ ኋላ ብንመለከት ትከሻችን ይቀጫል። አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች በምደባ ይሰጣል የተባለውም አከራካሪ ብቻ ሳይሆን አድሏዊም ነበር።
የማይካደው ሃቅ በስልጣን ላይ ያለው ካቢኔ ቀደም ሲል ለተወሰነላቸው አልሚዎች መሬት ከንክኪ ነፃ አድርጎ ለአልሚው ማስረከብ ይጠበቅበት ነበር።የመሬት አገልግሎት ዘርፍ ላይም መልካም አስተዳደር ማስፈን ይኖርበት ነበር። የተንሰራፋውን የመሬት ወረራ ማስታገስም ነበረበት። ቢያንስ እንኳ አገልግሎት ፈላጊውን ነዋሪ ከዕንግልት መታደግ ነበረበት። ይህ ሳይሆን ግን አመታት ተቆጥረዋል።
ሠሞኑን በመሬት ዘርፍ በተካሄዱ የግምገማ ማስጀመርያ መድረኮች፣ በመሬት ተቋማት በተጀመሩ ግምገማዎች ከተላለፉ መመርያዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ግምገማው መሬት የረገጠ እንዲሆን፣ ጥፋተኛ የተባሉ አካላት ላይ ጣት እንዲቀሰር ይፈለጋል።እጅ መንሻ የሚጠይቁ ተለይተው ይቅረቡም ተብሏል።
ከዚህ አንፃር በቡድን በቡድን በተሠጠ ቅርፅ ግምገማዎች የተጀመሩ ሲሆን በግምገማው የሰው ስም እየተነሳ ነው። ለሚሰጡት አገልግሎት ብር አምጡ፣ እጃችሁን እያወዛወዛችሁ በእግራችሁ አትምጡ!! ይላሉ ፤ ብለዋልም የተባሉ ሹሞች እየተብጠለጠሉ ነው። በቡድን ግምገማ ችግር መኖሩን ያነሳ ገምጋሚ በጠቅላይ ግምገማ ወቅት ስም መጥራት ይኖርበታል። አለበለዚያ ሃሜተኛ ተብሎ ዱላው እራሱ ላይ ያርፍበታል።
ይህ እንግዲህ ከታች ወደላይ በሚካሄድ ግምገማ የተገኘና የሚገኝ ውጤት ነው። የኢህአዴግ አልጋ ወረሽ በሆነው ብልፅግና ፓርቲ ቋንቋ ግምገማው ግለቱን ጠብቆ ይቀጥል ወይስ ይብሰል የሚል መወያያ አጭሯል። ይብሰል ማለት የደህንነት መረጃዎች ጭምር አጋዥ ሆነው ምቱ ይክረር ወይ? እንደማለት ነው።
ይህ ካልሆነ ደግሞ በሂስ እና ግለሂስ አወጫጭኙ ይቀጥል ወይ? የሚል ትርጉምም አለው። እንደሚታመነው ከላይ ወደታች የሚካሄድ ግምገማ ዋዘኞች በተውኔታቸው እንዳሉት – ከላይ ወደ ታች የሚጣል ትኩስ ድንች ነው። ብዙም ለውጥ ሲያመጣ አልታየም። አይጥ በባላ ዳዋ ተመታ እንዲሉ ዱላው አቅም በሌላቸው ላይ አርፎ አንደ ውሸት ጥይት ጮሆ ብቻ ይቀራል።
የማይቀረው እና አመላካቾች የታዩበት ነጥብ ግን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ጠንከር ያለ ግምገማ እንዲካሄድ በፅኑ መፈለጋቸው ነው።ቀጣዩ አመት የመሬት ዘርፍ ከሙስና የፀዳ፣መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ፣ አድሏዊነትን ያስወገደ እና ህገወጥነት ጥጉን የሚይዝበት እንዲሆን ቀጠዩን አምስት አመት የከተማውን ቁልፍ ይዘው ይቆያሉ ተብለው የሚጠበቁት የወ/ሮ አዳነች ፍላጎት መሆኑን መረጃዎች እያመለከቱ ነው።ያልታወቀው ነጥብ በግምገማው ግኝት መሠረት የቀድሞ ኃላፊዎች ተጠያቂ ይሆኑ ይሆንን? የሚለው ጉዳይ ነው።
እንደተለመደው አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ን የረገጠ ከንቲባ ሁሉ እንደሚያደርገው ፣ በቀጣዩ ዓመት አዴ አዳነችም በመሬት ዘርፍ ሪፎርም ለማድረግ መወጠናቸውን ከውስጥ የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
የመሬት ዘርፍ መዋቅር እና ሪፎርም ማብቂያ ማጣት ግን እጅግ አታካች ነው። ስለ ካዳስተር መሠማት ከጀመርን እንኳ ልጆች ተወልደው ጎረመሱ እኮ – ምናለ ብልፅግና ተወዳጇን አዲስ አበባ ከተማ በአብዛኛው በባለሙያ፣በጥቂቱ ደግሞ በፖለቲከኛ እንድትመራ ቢያደርግ ?