ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ፤ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች አጠቃላይ የዕቅድ ግምገማ ስብሰባን እያስተናገደ ነው
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድና ስልጠናዊ ግምገማ እያካሄደ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲዎች ዕቅዳቸውን ከማቅረባቸው በፊት በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ ጨምሮ ከ 25 ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ እግዶች የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።
በመቀጠል የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሰብስባቸው የመጡ እንግዶችን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ መድረኩን ከፍተዋል። ወደ መድረኩም ንግግር እንዲያደርጉ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበን ወደ መድረክ ጋብዟቸዋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ሀብታሙ(ዶ/ር ) በዩኒቨርስቲው የተገኙ ፕሬዝዳንቶችና እንግዶችን ወደ ሰላም አምባሳደር ወደ ሆነች ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እየሰሩ ስላላቸው ስራዎችና በቀጣይ ስለሚሰሩ ስራዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ትኩረት ሰጥቶ ካከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል ብዝሃነትን ያከበሩ ተማሪ ተኮር ስራዎችን እነዲሁም ለሴቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለና በአጭር ጊዜ ስኬታማ የሆነ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በተለይ የመግቢያ በር፣ የግቢ አስፓልት መንገድና በውስጥ የሚሰሩ የተለያዩ የግንባታ ስራዎችን ለስብሰባቸው ታዳሚ እንግዶች አብራርተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ሐሙስ ዕለትም በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ አምስት መቶ ሺህ የሚጠጋ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ለማከናወን ያቀዳቸውን ዋና ዋና ተግባራት አብራርተዋል። በዚህም መሰረት ዩኒቨርሲቲው በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በተቀናጀ ከተማ ልማት፣በታዳሽ ሃይልና አረንጓዴ ቱሪዝም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ዶ/ር ሀብታሙ ተናግረዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩለቸው ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲና ዶክተር ሀብታሙ በቅርቡ ላገኙት ሽልማት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ አያይዘውም ይህ ሽልማት የመጣው በትጋት ስለተሰራ የተገኘ መሆኑን በመጥቀስ አበረታተዋል፡፡
ስብሰባው እንደቀጠለ ሲሆን በቀጣይም ዩኒቨርሲቲዎች የ2014 ዕቅዶቻቸውን በቅደም ተከተል የሚያቀርቡ እንደሚሆን የደረሰን ዜና ጠቁሟል፡፡
ፎቶ፡- ዶ/ር ሙሉ ነጋ፣ ዶ/ር ሀብታሙ አበበ እና የስብሰባው ተሳታፊዎች በከፊል