በሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ የተደቀነውን አደጋ የመመከት ኃላፊነት በዋነኛነት የፌደራል መንግሥቱ ነው!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም
አንኳር
• የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በይዞታው ስር የነበሩ ቦታዎችን ለቆ ከወጣ በኋላ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያስተዋልነው እንቅስቃሴ ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣነው መግለጫ በቢሆንስ (Scenario) ትንተናችን ውስጥ ከሁሉም የተሻለ የመከሰት ዕድል አለው ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (Scenario) እውን እየሆነ እንደሆነ የሚያመላክት ነው።
• የፌደራል መንግሥት ሕወሃት ግጭቱን ለመቀጠል የወሰዳቸውን እርምጃዎች በግንባር ቀደምነት አመራር እየሰጠ ለማክሸፍ ከመሞከር ይልቅ ግጭቱን በክልሎች መካከል ያለ ግጭት እስኪመስል የወሰደው ግልፅ ያልሆነ አቋም እጅግ አስደንጋጭ ሆኖ አግኝተነዋል።
• በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የፀጥታ አስከባሪዎች ሕወሃት የደቀነው አደጋን ለማክሸፍ እያደረጉ ያሉትን መረባረብ በከፍተኛ አክብሮት እናደንቃለን።
ሕወሃት የደቀነው አደጋ በሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ እንጂ በአንድ ወይንም በጥቂት ክልሎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልሆነ በመረዳት አደጋውን ለመከላከል የሚወሰደው እርምጃ አንድ ወጥ የዕዝ ሰንሰለት ኖሮት በፌደራል መንግሥት እና በኢፌደሪ መከላከያ ሠራዊት አመራር ሰጪነት ብቻ መወሰድ አለበት።
• በትግራይ ክልል ያለውን ችግር አሁን ከፊታችን ሕወሃት ከደቀነው አደጋ እንፃር ብቻ በማየት ሕወሃትን ማሸነፍን ብቻ ዓላማ ያደረገ የአጭር ጊዜ ስልት ይዞ ከመንቀሳቀስ ባለፈ በዘላቂነት ክልሉ ወደተረጋጋ ሰላም እና ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ሊመለሱ የሚችሉበት እንዲሁም ግጭቱ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተቋጭቶ የሀገር ህልውና እና አንድነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻልበት ስልት የአካባቢውን ተወላጆች በማሳተፍ ተነድፎ ተግባራዊ መደረግ አለበት።
• አሁን ያለው ግጭት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች የምትገኙ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ልሂቃን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የምታስፈልጉበት ወቅት ላይ መሆናችሁን ተረድታችሁ የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት መወጣት ይገባቹኻል።
• የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደርሳቸው የሚደረገው ጥረት አሁን ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ በክልሉ ለሚኖሩ ዜጎች እንዲዳረስ የሚያደርገውን ጥረት በግልፅ እንዲያሳውቅ፤ እንዲሁም በዚህ ተግባር የሚሳተፉ የሰብዓዊ ድርጅቶች በግልፅነት እንዲንቀሳቀሱ ተገቢው ክትትል መደረግ ይኖርበታል።
• ሕወሃትን ደግፋቹኻል በሚል በጅምላ የሚወሰዱ እርምጃዎች ባስቸኳይ እንዲቆሙ እና እስካሁንም በዚህ መልኩ የተወሰዱ እርምጃዎች አፋጣኝ ማጣራት ተደርጎ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም አሁን ያለውን ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የግል ጥቅም ለማግኘት ዜጎች ላይ እንግልት የሚፈፅሙ የመንግሥት እና የፀጥታ ሠራተኞች ላይ አስፈላጊው ማጣራት በአስቸኳይ ተደርጎ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤