Connect with us

የብሮክራሲዉን ድክመቶች መቅረፍ ቀዳሚው  የመንግስት ኃላፊነት !!

የብሮክራሲዉን ድክመቶች መቅረፍ ቀዳሚው የመንግስት ኃላፊነት !!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የብሮክራሲዉን ድክመቶች መቅረፍ ቀዳሚው  የመንግስት ኃላፊነት !!

የብሮክራሲዉን ድክመቶች መቅረፍ ቀዳሚው  የመንግስት ኃላፊነት !!

(ንጉሥ ወዳጅነው – ድሬ ቲዩብ )

 ዲሞክራሲንና ፍትሃዊነትን ለህዝብ ለማጎናፀፍና ብልፅግናን በአገር ላይ ለማረጋጋጥ   ቢሮክራሲዉንና የመንግስት አሰራርን  ማጠናከር ወሳኝና ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት ፡፡ በተለይ መዋቅርን ተጠቅሞ ከሚካሄድ ዘረፋና ንጥቂያ ህዝብን መታደግ ለነገ መባል የለበትም ፡፡ ከቅርብ አመታት ወዲህ  አገራችን አጋጥሟት ለነበረው ህዝብ በመንግስት ላይ የመከፋት ዝንባሌ፣ ተስፋ ቆራጭነትና አልፎ ተርፎም የእርስበርስ ግጭት ፣ አንዱ መንስኤ ይህው ችግር እንደነበር መዘንጋትም  አይገባም ፡፡

 ከለውጡ በፊት መንግስታዊ ስርዓት ዉስጥ ያቆጠቆጠዉ ጥገኛ ሁሉ እየተቧደነ  ህዝቡ በአደባባይ እሲከጮህ  ድረስ  ብዝበዛና ምዝበራ ዉስጥ መዘፈቁ፣  ብዙሃኑን የሚያስቆጣ ነበር የሆነው  ፡፡  ስለሆነም እንደ ሀገር የተለወጠ የፖለቲካ ስነምህዳር ተፈጥሯል ከተባለ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝብ በድምፁ እንደመረጠው መንግስት  ከዚያ ከንቱ ምዕራፍ ለመወጣት  በርትቶ መንቀሳቀስ ግድ ይላል ፡፡ ይህን እሳቤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ (ዶ/ር) ም በፓርላማው ማጠቃላይ ንግግራቸው ላይ  በግልፅ ተናግረዋል  ፡፡ ግን ብርቱ ተከታዮች ያስፈልጋሉ!! 

 አሁን አገራችን ይነስም የብዛም ለዉጥ ጀምራለች ፡፡ የሀሳብ ነፃነት፣ የመምረጥና መመረጥ ፣የመደራጀትና  በነፃነት  ሰርቶ የመብላት እድል እየተፈጠረ ነዉ ፡፡ ምንም እንኳን የከረመዉ አንጎበር ያባባሰዉ ግጭት፣ የዜጎች መፈናቀልና ሞት ፣ የህወሀት የለኮሰው ጦርነት ጉዳት ማስከተሉ ባይካድም፣ቢያንስ በከፋ የሀብት ብክነትና የከረፋ ሙስና ውስጥ ያለ ተቋም ወይም የስራ ሃላፊ አገር እየመራ ነዉ የሚል ቅዠት ዉስጥ የሚያስገባ መረጃ  የለም ፡፡

 ነገር ግን አሁንም ቢሆን እራስ ወዳድነትና ጠባብነት ፣ በሙስና መደራደርና በአቋራጭ ለመበልፀግ መወራጨት እየተንቀለቀለ  መሆኑ አይካድም ፡፡ ውስን የህዝብ  ሀብትን  የማድፋፋት ቀዳዳ( ለአብንት መሬት ) ሙሉ በሙሉ ተወግዷል ለማለት ጥንቃቄና ጊዜ ያስፈልጋል ፡፡ ገና ብርቱ ትግልና የማሻሻያ እርምጃ መወሰድ  ያለበት ጉዳይም ነዉ ፡፡ ካለማቅማማት !! 

 በመሰረቱ   በሶስት አስርት ዓመታት ዉስጥ የህዝብ ቁጥሩ በእጥፍ አድጎ  መቶ አስር ሚሊዮን ደርሶ ይቅርና ፣ የትም ቢሆን  ሰው ሲበዛ መሬት ይጠባል  ፡፡ የሀብት አገልግሎትና አቅርቦትም ያንሳል ፡፡ በዚህ ላይ ስግብግብነትና አልጠግብ ባይነት ሲበረታ  ሽሚያ፣ ንጥቂያና የሌላውን ድርሻ መፈለግ  ይገነግናል ፡፡ ይህን ልጎም የለሽ ፍላጎት የሚገታ የቁጥጥርና የግምገም ብቻ ሳይሆን ህግ የማስከበር ስራአት ከሌለ ችግሩ ሊባባስ ይችላል ፡፡ ስለሆነም መንግስት ቢሮክራሲውን ገለባብጦ በመፈተሸ ቅድሚያ ውስጡን ማጥራት ይጠበቅበታል  ፡፡

 ኢትዮጵያውያን ምንም እንኳን በሃይማኖቶቻችንና በባህሎቻችን ፈሪኃ ፈጣሪና ሞራላዊነት ያለን ብንሆንም ፣ በተለይ በከተሞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያቆጠቆጠ የመጣው በአቋራጭ የመክበርና ሕግና ሥርዓትን በገንዘብ የመጠምዘዝ ድርጊት ፈር እንዳያስትን መገታት አለበት ፡፡ ለውጥን የዋጃ፣ አገር ወዳድነትና ብርቱ ተነሳሽነት የሚታይበት ፐብሊክ ሰርቪስ መገንባት የሚያስፈልገውም ለዚሁ ነው ፡፡  

 በየትኛውምና በምንም መንገድ ስልጣንን ላልተገባ ጥቅምና ተራን ጠብቆ ለመዝረፍ ለማዋል  የሚያስበዉ የቆየ አመለካካት በትግል በተገኘው ለውጥ መታረም አለበት፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላን …››  እየዘመሩ ያውም በህዝብ መሬት፣የጋራ ሀብትና ንብረት ላይ ወንጀል መፈፀም ቢያንስ ከህወሀት/ኢህአዴግ  ውድቀት በሆላ ትምሀርት ሊወሰድበት ግድ ነው ፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት ብቻ ሳይሆን ህዝቡም የነቃ ትግል ማድረግ ይኖርበታል ፡፡ 

በአጠቃላይ የቢሮክራሲ ብልሽትና የሙስና ወንጀል ጎጂነት ላይ የምንስማማውን ያህል በጋራ መታገሉ ላይ ካልበረታን ለነገው ትውልድ የተሻለች አገር ልናስተላልፍ አንችልም፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ በላቀ ሞራልና ሥነ ምግባር፣ በታታሪነትና ትጋት እንዲሁም በፀረ ሌብነትና በፀረ ሙስና ባህል ውስጥ ሆነን ቤታችንን እንሥራ ፡፡ ትዉልድም እንታደግ ፣ አገራችንንምእንገንባ  ነዉ መባል ያለበት ፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top