Connect with us

ʺእኔስ በተከዜ ቀናሁ፤ እርሱን ብሆን ብዬ ተመኘሁ!”

ʺእኔስ በተከዜ ቀናሁ፤ እርሱን ብሆን ብዬ ተመኘሁ!"
ታርቆ ክንዴ ~አሚኮ

ነፃ ሃሳብ

ʺእኔስ በተከዜ ቀናሁ፤ እርሱን ብሆን ብዬ ተመኘሁ!”

ʺእኔስ በተከዜ ቀናሁ፤ እርሱን ብሆን ብዬ ተመኘሁ!”

የታደለ ወንዝ መከራንም ደስታንም ያይ ዘንድ የተመረጠ፡፡ የትናንቱ ሲያልፍ፣ ዛሬን፣ ዛሬም ትናንት ሲሆን ነገን እያዬ ስንቱን አሳለፈው፡፡ የኢትዮጵያን የፍስሃና የፈተና ዘመናትን አይቷል፡፡ ዘመን በነጎደ ቁጥር እርሱም ሁሉን እየታዘበ ይፈስሳል፡፡

ከታሪክ ባሕር፣ ከጀግኖች ሀገር፣ ከፍቅር መንደር፣ ከጃንተከል ዋርካ ሥር፣ ከአርባ አራቱ አድባር፣ ከመናገሸዋ ከተማ  ሌሊቱን አሳልፌያለሁ፡፡

ጠቢባን የተጠበቡበት፣ ነገሥታት የከተሙበት፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ የታደሙበት፣ እንደአንበሳ ግርማ የሚያስፈሩት፣ ጠላትን እንደ ጭብጥ ጥሬ የሚያፍኑት፣ እንኳን በክንዳቸው በግርማቸው የሚያርዱት ጀግኖች በዙሪያ ገባው የተሰለፉበት ያ ታላቅ ቤተ መንግሥት የትናንትን ታሪክ እየዘከረ፣ ዛሬን በግርማ እየኖረ፣ ነገን በአሻገር እንዲያዩ ልጆቹን በመስመር እያሰመረ በኩራት ቆሟል፡፡ 

በዚያ ቤተ መንግሥት ውስጥ  ዛሬ ላይ ነገሥታቱ የሉም፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ በችሎት አጠገብ አይሰየሙም፣ ወታደሮቹ በቅፅሩ ዙሪያ አይቆሙም፣ የቤተ መንግሥት ነጋሪት አይጎሰሙም፣ ዓለም አጫዋቾች አያጫውቱም፣ ካህናቱ አያዜሙም፣ ከግብር በፊት ጸሎት አያደርሱም፣ ከግብር  በኋላ ሰብሐት አይሉም፣ ንጉሡ ለፍርድ አይሰየሙም፣  የልፍኝ አስከልካዮች፣ የነገሥታቱ አሽከሮች ለአገልግሎት አይፋጠኑም ቢባል ማን ያምናል፡፡

ዓመታት አልፈው ዓመታት ሲተኩ ቤተ መንግሥቱ እስከ ግርማው ቀጥሏል፡፡ ጥላው ከባድ ነው፡፡ የእልፍኝ አስከልካይ፣ የቤተ መንግሥት ጠባቂው፣ የጦር አዛዡ  ጎራዴ እስከ ሰገባው ያለ ይመስላል፡፡ የዙሪያ ገባው ውበት፣ የቤተ መንግሥቱ የዙፋን ክብደት አጄብ ያሰኛል፡፡ ፋሲል ቤተ መንግሥት ውስጥ አሁንም ነገሥታቱ፣ መሳፍንቱ፣ መኳንንቱና፣ ካህናቱ፣ ሠራዊቱ ሁሉም ነገር እንደ ተሟላ ያለ ይመስላል፡፡ ግርማው የእውነት ነበርና ዙፋን ሳይኖር፣ ነጋሪቱ ሳያጓራ፣ የግብር ሰዓት ሳይጠራ አሁንም ከክብሩ ሳይጎድል አለ፡፡

 አዳሩ ጎንደር ላይ የሆነ ሁሉ የቤተ መንግሥቱ ግርማ፣ የአድባራቱ ዜማ፣ የተራራዎቿ ውበት፣ የጃንተከል ሥፋት፣ የሕዝቡ ሰው ወዳድነት፣ እንግዳ አክባሪነት፣  ጀግንነት፣ ሀገር ወዳድነት፣ የተሟላ ኢትዮጵያዊነት ሳያስደንቀው አይቀርም፡፡

ʺእያደር ዝናው ይገናል ስሙ

መሰከረለት ድፍን ዓለሙ ” እንዳለች ከያኒዋ የጎንደር ዝና እያደር ይገናል፡፡ ጎንደር በታዬች ቁጥር አዲስ የምትሆን የማትጠገብ ውብ ሥፍራ፡፡ ሌሊቱ የስልጣን ዘመኑን ለማዕልቱ ሊሰጥ ተቃርቧል፡፡ በየአድባራቱ የካህናት ዜማ ለስለስ እያለ ይሰማል፡፡ አእዋፋት ብርሃንን በዜማቸው እያጀቡ እየተቀበሉት ነው፡፡ 

የብርሃንን መሬት መያዝ ተከትሎ የመጡት መልካም ዜማዎች እያባበሉ ከእንቅልፌ አነቁኝ፡፡ ደስ የሚል ንጋት፤ ጥዑም ዜማ፣ የነብስ ምግብ፡፡ አደራውን የማይበላ አምላክ ከንቅልፍ አንቅቶ፤ ተጨማሪ እድል ሰጥቶ ከአልጋዬ ላይ በሰላም ስላነቃኝ አመስግኘው ተነሰሁ፡፡

ከሙሽረዋ ጎንደር ከተማ ወደ በረሃማው አካባቢ ልወርድ ቀጠሮ ይዧለሁ፡፡ ብርሃን ነጭ ካባውን በምድር ላይ ጥሏል፡፡ ጀንበር ከመስኮቷ እየወጣች ነው፡፡ መፍለቅለቅ ጀምራለች፡፡ በጎንደር ከተማ የነበረኝ ቆይታ ሊጠናቀቅ ነው፡፡ ጎንደርን ተሰናብቻት ወደ በረሃው ጉዞ ጀምሬያለሁ፡፡ በጎንደር ከተማ በጠዋት የሰማሁት ጥዑመ ዜማ እየተከተለኝ ነው፡፡ 

ልብን የሚፈትነው መልካምድር የተለዬ ስሜት ይሰጣል፡፡ አረንጓዴ ካባቸውን በዙሪያቸው ያልተነጠቁት ሰንሰላታማ ተራራዎች በአሻገር ሲታዩ ወኔ ይሰጣሉ፡፡ ተራራዎቹን በግራና በቀኝ እየተመለከቱ የጀግኖችን ምድር አርማጭሆን ሲወርዱ የጸሐይ ኃይል እየበረታ፣ ቅዝቃዜ አቅም እያነሰው ይሄዳል፡፡ አርማጭሆ ጀግና መውለድ ያውቃል፤ በዚያ ምድር የሚወለደው ሁሉ ለጠላት ስጋት፣ ለወገን ኩራት ነው፡፡  ስለ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩ ሠንድቅ መዋደቅ፣ ከጠላት መላቅ ይችሉበታል፡፡

የአርማጭሆ ተራራማ አካባቢዎችን ወርጄያለሁ፡፡ ጉዞዬ ቀጥሏል፡፡ ጀንበር ኃይሏ የበለጠ እየጨመረ ነው፡፡ አረንጓዴ የለበሰው መልካሙ ምድር  ያማልላል፡፡ የአርማጭሆን ከተማዎች እያቆራረጥኩ ወደፊት ገሰገስኩ፡፡

 የጠገዴ ከተማዎችንም እንዲሁ፡፡ ሶሮቃ ደርሻለሁ፡፡ ከሶሮቃ ወንዝ ማዶ የሚገኙት ነዋሪዎች በወያኔ የግፍ አገዛዝ ዘመን አያሌ ሰቆቃዎችን አሳልፈዋል፡፡ ከዓመታት የመከራ ዘመን በኋላ ነጻ ወጥተው ነጻነታቸውን እያጣጣሙ ነው፡፡

የወልቃይት ጠገዴ መሬት ለዓመታት የበቀለበትን መጥፎ አረም ነቅሏልና ደስታ ላይ ነው፡፡ በመንገዱ ግራና ቀኝ ኑሯቸውን የመሠረቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ደስታቸው ልዩ ሆኗል፡፡ ጨልሞ የሚቀር የለምና ቀን ወጥቶ፣ ብርሃን ታይቶ ወልቃይት ጠገዴን ገለጠው፡፡  በወላፈን የሚጋረፈው አየር ቢያስጨንቅም በየመንገዱ የሚገኘው ሰው ነጻነት፣ ደስታና ፍቅር ሁሉንም ያስረሳል፡፡

በረሃውን እያቆራረጥን ዳንሻ ደማቋ ከተማ ደርሰናል፡፡ ዳንሻ ያለፈውን ዘመን የምታካክስ ይመስላል፤ ደስታዋ ቀንና ማታ ነው፡፡  ሙቀቱን ይከላከሉ ዘንድ በየቤቱ በር በተሰደሩት አረንጓዴ ዛፎች ግርጌ ከጸሐይ ተጠልሎ ሳቅና ጨዋታ በዳንሻ ዓለም ነው፡፡

 እርሷን ዓይቶ ማን ያልፋል፡፡ ፍቅር ከሆነ ሕዝብ ጋር ጥቂት የፍቅር ጊዜ ማሳለፍ ይበጃል እንጂ፡፡ ምሳ በዳንሻ እንበላ ዘንድ ወደድን፡፡ ዳንሻ ተገብቶ ምን ታጥቶ ልብን ጥሎ መጫዎት፣ አማርጦ መመገብ ነው እንጂ፤ ምሳችን በዳንሻ ተመገብን፤ ከዳንሻ የፍቅር ባሕር ጥቂት ጨለፍን፡፡ ጉዟችን ሩቅ ነውና ዳንሻን በስስት ዓይተናት ወደ ፊት ገሰገስን፡፡ 

ዳንሻ ሕግ በማስከበር ዘመቻው አያሌ ጀብዱዎች የተፈጸሙባት፤ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የታዩባትና ተፈትነው ያለፉባት ከተማ ናት፡፡ የአሸባሪው ህወሃት ቅስም ተሰብሮ አንገቱን እንደደፋ እንዲጓዝ የተደረገባት ከተማም ናት ዳንሻ፡፡

ዓይኔ ግራና ቀኝ እያማተረ ነው፡፡ መኪናው ቀጥ ባለው የበረሃ መንገድ እንዳሻው ይወነጨፋል፡፡ አይ ወልቃይት ድንቅ ምድር፤ ብዙ የታዬበት፣ ጀግና የተፈጠረበት፣ ኢትዮጵያዊነት ስር የሰደደበት፡፡  ዓልሞ መተኮስ፣ አደባልቆ ማረስ፣ በሰፊ አውድማ ማፈስ መገለጫ የሆነበት፡፡  ጉዟችን ቀጥሏል፡፡ በበረሃው ውስጥ በአስደናቂው ምድር የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ካምፕ አገኘን፡፡ ዘመኑን የዋጁ የጦር መሳሪያዎች፣ እንደ ነብር የፈጠኑ፣ እንደ አንበሳ የጀገኑ ጀግና ወታደሮች በዚያ ካምፕ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ 

በስስት ተመለከትኳቸው፡፡ እውን ከእናንተ በላይ ሀገሩን ማን ይወዳል? ምን አይነት መታደል፣ ምን አይነትስ መመረጥ ይሆን? ስለ ኢትዮጵያ በበረሃ ትኖራላችሁና፣ በእናንተ ኢትዮጵያ ትኮራለችም፣ ትከበራለችም አልኩ በልቤ፡፡ ራስን ሰጥቶ፣ ኑሮውን በበረሃ መስርቶ ስለ ሀገርና ሕዝብ ዘብ ከመቆም በላይ ምንም ስጦታ የለም፡፡

ዓይኔ እንባ እስኪያቀር ድረስ በፍቅር ተመለከትኳቸው፡፡  መኖሪያቸው ከዓይኔ እስኪሰወር ድረስ ዓይኔን ሳላነሳ ጉዟችን ቀጠለ፡፡ ከፊት ለፊታችን የበረሃዋ ሙሽራ ትገኛለች፣ ባዕከር ከተማ፤  ባዕከርን በስስት ቃኝተናት ወደፊት ገሰገስን፡፡ ከመንገዱ በስተግራ በኩል ወደ ምዕራብ ንፍቅ ሲመለከቱ  የምድር መጨረሻ ይመስላል፡፡ 

ኢትዮጵያ የምድር መጨረሻ ናትን፣ ሰማይና ምድርስ ይነካካሉ ወይ? ይላሉ፡፡ ሰማይ ከምድር ላይ የተመረኮዘ ይመስላልና፡፡ ነጭ ወርቅ የሚታፈስበት በረሃ ያስፈራል፡፡ ወበቁ ይጋረፋል፡፡ ጥንቁቁ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ  ግን እንዳሻው ይሆንበታል፡፡ ከበረሃው ጋር ተለማምዷል፤ ከምድሩ ጋር ተዋዷልና፡፡

መኪናዋ እየከነፈች ነው፡፡ በዳርና በዳር በሰልፍ የቆመ የሚመስለው የበረሃ ዛፍ ለመንገዱ ውበት ሰጥቶታል፡፡ በአሻገር አንድ ነገር ተመለከትን፡፡ ቀረብነው፡፡ ከዚያ አስቸጋሪ በረሃ ከመንገዱ አጠገብ ጠላትና ሙቀተን ተቋቁመው የሚኖሩ ወታደሮችን አገኘን፡፡ ተጓዡን እየጠየቁና እየፈተሹ ነው የሚያሳልፉት፡፡ እኛም እንፈተሸ ዘንድ ግድ ነውና ከመኪናችን ወረድን፡፡ ከአጠገብ ዘመናዊ መሳሪያ የሚታይበት የወታደር መኖሪያ ( ካምፕ) አለ፡፡

ወደ መዳረሻችን ከተማ እየተቃረብን ነው፡፡ ከመንገዱ በስተግራ ወደ ደቡብ ምዕራብ ንፍቅ የሚወስድ መንገድ አለ፡፡ ወደ ዬት እንደሚወስድ ጠየኳቸው፡፡ በማይካድራ አድርጎ  ወደ ምድረ ገነት (አብደራፊ)  እንደሚወስድ ነገሩኝ፡፡

 በማይካድራና በአብደራፊ መካከል ወደ ሱዳን የሚያስወጣ ሌላ መንገድ እንዳለና መነሻው ያ መንገድ እንደሆነም ሰምቻለሁ፡፡ ፍተሻችን ጨረስን፡፡ እኒያን ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ተሰነባብተን ወደ መዳረሻችን ከተማ ከነፍን፡፡ ራእውያን  የተሰኘችውን ከተማ  አልፈን ከመዳረሻችን ከተማ ከተመን፡፡

የተከዜዋ ንግሥት፣ የበረሃዋ እመቤት ውቧ ሑመራ፡፡ በአካባቢው ሑመር የሚባል ዛፍ ይበዛል፡፡ በዚያ ዛፍ ጥላ ሥር ለሥር፣ በተከዜ ዳር ከተማ ተመሰረተች፡፡ የዚህች ከተማ ስምም ከዛፉ ተወሰደላት፡፡ ከሑመር ተመሰረተችና ሑመራ ተባለች ይላሉ አበው፡፡ ሑመራ የፍቅር ከተማ፣ የጉዟችን ፍጻሜ ሊሆን ነው፡፡ 

በጎንደር የዘለቀችውን ጀንበር፣ በሑመራ ልናጠልቃት ነው፡፡ ማረፊያችን አዘጋጅተን ሑመራን እንቃኛት ዘንድ ወደድን፡፡

ሑመራን ሲቃኙ ታሪክ አዋቂ መጠየቅ መልካም ነው አንድ ታላቅ ሰው አግኝቻለሁ፡፡  አባ ጋሻው ዓለሙ ይባላሉ፡፡ ሑመራን ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምረው ነው የሚኖሩባት፡፡

 አያሌ ትዝታዎች አሉባቸው፡፡ ትዝታቸው በሑመራ ብቻ የሚወሰን አይደለም አሰብ፣ ምጽዋ፣  አሥመራ፣ ቀይ ባሕርና ኤርትራ ድረስ ይዘልቃል እንጂ፡፡ ከሑመራ ወደ ኤርትራ የሚያሻግረው ድልድይ ሳይሠራ ገና ተከዜን የሚሻገሩት በዋና፣ ካለበለዚያ በእግር ግፊት ነበር፡፡ ተከዜ ታጥቦ ገላን ማንጫ ብቻ አልነበረም፣ የፍቅር፣ የደስታና የኅብረት መግለጫም ነበር እንጂ፡፡ 

አባ ጋሻው ያን ጊዜ ሲያስታውሱት ትዝታ ከንግግራቸው ጎትቶ ወደኋላ ይዟቸው ጭልጥ ይላል፡፡ ʺከሑመራ ሰሊጥ፣ ማሽላና ጥጥ እየተጫነ ወደ አስመራ ይሄዳል፣  እኔም እነግድ ነበር፣ የሑመራን አካባቢ የሚገዙት ራስ ቢትወደድ አዳነ መኮንን ነበሩ፣  ሑመራ ማንም ይኖርበታል፡፡ አስተዳደሩ ጎን በጎንደር ክፍለ ሀገር ነው፡፡ 

ታዲያ ዘመን ያመጣው አሸባሪው ትህነግ መጣና………” ንግግራቸውን አቋርጠው  ወደ ትዝታቸው ተመለሱ፡፡  ያ ከትህነግ በፊት የሚያውቁት ዘመን እየመጣ እየወሰዳቸው ነው፡፡ ከሑመራ ኤርትራ ተሻግረው፣ አስመራ ገብይተው፣ ቀይ ባሕር ዋኝተው፣ ጠጥተው፣ የሚመጡበት ዘመን ውል አለባቸው፡፡ ታዲያ እሳቸው ያልተከዙ ማን ይተክዛል፡፡

ጀግናው ራስ ቢትወደድ አዳነ በአካባቢው ሰው እንዲህ እየተባለ ይገጠምላቸው እንደነበርም ነግረውኛል፡፡  ʺ ቢትወደድ አደነ ዋርካዬ ዋርካዬ

                   ፍሬውን በልቼ ጥላው ማረፊያዬ”

አካባቢው በርካታ የኢትዮጵያ ሁነቶችን አይቷል፡፡ መከራውንም ክፉውንም፡፡ ʺወተትና ማሩ ዝቀሽ ነው፡፡ የዚያኔው የኤርትራ ጠቅላይ ግዛትና የሰሜን በጌ ምድር ጠቅላይ ግዛት ሰው ፍቅሩ ለብቻ ነው በእውነቱ፡፡ ፍቅራችን ግሩም ነው” አሉኝ አባ ጋሻው፡፡ በዚያች ከተማ እንኳንስ ኢትዮጵያዊያን ሌሎች አፍሪካዊያን በፍቅር ነበር የሚኖሩት፡፡ በእርግጥ የዚያ ዘመን የሕዝብ የፍቅር ገመድ ጠንካራ ነበርና ዛሬም ክፉው ዘመን ጨርሶ አላጠፋውም፡፡ 

ቅድመ ህወሃት ሑመራ እንዴት ነበረች?  አባ ጋሻው ከት ብለው ሳቁብኝ፡፡ በእውነቱ ስለ ሑመራ ፍቅር መጠየቅ ከንቱነት ኖሯል፡፡ ʺአይ አንተ ልጄ  ፍቅሩማ፣ ወንድማማች ሆኖ ነው የሚኖር እንጂ፣ ሰው ቢታመም እኔ ሀኪም ቤት ልወስድ እኔ ልውሰድ ነው፣ ሞትም ቢሆን እንደዚያው፣ መጠጥ ቤት የገባኽ እንደሆነ የሚከፍልልህን አታውቀውም፤ እጅ ነስተህ አመስግነህ ነው የምትሄደው፣ የፍቅሩ ነገር ምኑ ተወግቶ ይዘለቃል፡፡ 

ልጄ በፍቅር የተጣመደ፣ የተዋለደ እንኮ ነው” አሁንም ትዝታ ወሰዳቸው፤ በመካከል እሳቸው ብቻ ወደሚያዩት የትዝታ መንገድ ጥለውኝ ነጎዱ፡፡  ደርሰው ይመለሱ ብዬ ዝም አልኳቸው፡፡ 

ያን ዘመን አልፈው ሌላ ዘመን መጥቷል፡፡  አባ ጋሻው የቀደመውን ዘመን መልሰው እያዩ ነው፡፡ ጭራሹን ያብጅልን እንጂ ጥሩ ነው ብለውኛል፡፡ ተከዜን በእግር መሻገር ቀረና ድልድዩ በጃንሆይ በ1960 ዓ.ም ተሠራ አሉኝ፡፡  እጃቸውን ወደ ድልድዩ አቅጣጫ እየጠቆሙ፡፡ የድልድዩ መሠራት ሥራንም ፍቅርንም ጨመረ፡፡ ዘመን ዘመንን እየተካ ሄደ፤ ዘመነ አሸባሪው ህወሃት መጣ፡፡ ኤርትራም ራሷን የቻለች ሀገር ሆነች፡፡ የፍቅር መሻገሪያው ድልድይ ሥራ አቆመ፡፡

በእውነቱ አንድ ጫፉን ሑመራ አንድ ጫፉን ኤርትራ አድርጎ የተጋደመውን ድልድይ አይ ዘንድ ጓጉቻለሁ፡፡ ሑመራ ደርሶ የተከዜን ድልድይ ሳያይ ማን ይመጣና፡፡ ጀንበር ማዘቅዘቅ ጀምራለች፡፡ የጀንበርን መዘቅዘቅ ተከትለው የሑመራ ነዋሪዎች ውኃ ለመቅዳትና ለመዋኘት ወደ ተከዜ ወርደዋል፡፡ አባ ጋሻውን አመስግኛቸው ወደ ተከዜ ወረድኩ፡፡

ወደ ድልድዩ ለመሻገር ከከተማዋ ጫፍ ከድልድዩ አጠገብ የተቀመጡትን የፌዴራል ፖሊሶች መጠየቅ ግድ ነበርና እነርሱን አስፈቅጄ ይሁንታ ሳገኝ ወደ ድልድዩ አቀናሁ፡፡ በአንደኛው ጫፍ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ የኢትዮጵያ ሠንደቅ፣ በሌላኛው ጫፍ ደግሞ የኤርትራ ሠንደቅ ይውለበለባሉ፡፡ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወዲህ ለረጅም ዓመታት በዚያ ድልድይ የሚወጣም የሚገባም አልነበረም፡፡

ከረጅሙ ድልድይ መካከል ቆሜ ተከዜን ተመለከተኩት፡፡ ዘመናትን አሳልፎ ምድርን በሚታዘበው በተከዜ ቀናሁ፤ እርሱን ብሆን ብዬ ተመኘሁ፤ አንተ ታላቅ ወንዝ ሆይ ስንት ዘመናት ሳታቋርጥ ተጓዝክ፣ በዘመናት ጉዞህ መካከል ምን ምን ነገርስ አየህ? ካሳለፍከውና እያሳለፍከው ካለው ዘመን የትኛው ይበልጣል? የቱስ አስገረመህ? እባክህን የኢትዮጵያን ውብ ታሪክ ሳታቋርጥ ንገረኝ? የልቤ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ 

መነሻው ከአቡሆይ ጋራ እንደሆነ የሚነገርለት ተከዜ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ተራራዎች እየተሹለከለከ ወርዶ፣ በረሃማዋ ሱዳንን እያረሰረሰ ይፈስሳል፡፡ ከድልድዩ ወደታች በነጻነት የሚዋኙ፣ ልብስ የሚያጥቡና ውኃ የሚቀዱ ሰዎች ይታያሉ፡፡ ደስታዬ ወደር አልነበረውም፡፡ ጊዜ ደጉ ያመጣል ይወስዳል፡፡ ከሑመራ እስከ ኤርትራ የተዘረጋው ድልድይ ሰው እንዳያሻግር የተከለከለበት ዘመን ታወሰኝ፡፡

አንደኛው ከሑመራ ሌላኛዋ ከኤርትራ ጫፍ ሆነው እንዳይገናኙ የተከለከሉ ስንት ፍቅረኛሞች እንደነበሩ ሳስብ ልቤ አዘነች፡፡ በአሻገር እያዬችው በአሻገር እያያት በእቅፏ ሳታሞቀው በእቅፉ ሳያሞቃት፣ በጆሮዎቿ እያንሾካሾከ ፍቅሩን ሳይነግራት፣ በክንዱ ሳይደግፋት ዓመታት ነጎዱ፡፡

ʺእያለ ድልድዩ መሻገሪያ ሞልቶ

ናፍቆት ጎዳን እንጂ አሻጋሪ ጠፍቶ “

በነጋ በጠባ በአሻገር እየተያዩ ዘመናትን አሳለፉ፡፡ እያየቸው ሸበተ፣ እያያት ሸበተች፡፡ ክፉ ዘመን ከሚወዱት ሰው ጋር ያለያያል፡፡

ʺ እኔ ወዲህ ማዶ አንቺ ወዲያ ማዶ

አንገናኝም ወይ ገደሉ ተንዶ” ከወንዝ ማዶ እያያት እያዜመ፣ እያዬችው እያዜመች፣ ዜማቸው በተከዜ ፈሳሽ ውኃ፣ በአእዋፋት ዝማሬ እየታጀበ በሕሊናቸው ይመላለሳል፡፡ 

ተስፋ የማይቆርጥ ፍቅር፣ መልካም ዘመንን የሚጠብቅ፤ ʺፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፣ ፍቅር አይቀናም፣ ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም፣ የማይገባውን አያደርግም፣     አይበሳጭም፣  በደልን አይቆጥርም፤  ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሣል፣  ሁሉን ያምናል፣  ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣  በሁሉ ይጸናል” እንዳለ በሁሉም ጸንተው ኖሩ፡፡ የልባቸውን መሻት አይቶ እርሱ ረዳቸው፤ መልካም ዘመንም መጣ፡፡ እንደ ቀድሞው ሁሉ በተከዜ ወንዝ በጋራ እየዋኙ ፍቅራቸውን ያጣጥሙ ጀምረዋል፡፡

ከመስኮቷ ልትደበቅ የምትገሰግሰው ጀንበር ውብ ገጽታ ይዛለች፡፡ ለትዝታ  ይሆን ዘንድ ምስሏን አስቀረኋት፡፡ ያለፈውን ዘመን በምናቤ እያንሰላሰልኩ የኤርትራ ሠንደቅ ወደ ተሰቀለበት ጫፍ አዘገምኩ፡፡ ከሠንደቋ አጠገብ ሁለት የኤርትራ ወታደሮች ተቀምጠዋል፡፡ በአሻገር ፈገግታቸው ይጠራል፡፡ እንደ ቀደመው ተመለሱ የለም ዛሬ ላይ፤ ከመቀመጫቸው ተነስተው እጃቸውን ለሰላምታ ዘረጉልኝ፡፡ ፈገግታቸው በፍቅር ይጥላል፡፡ አጻፈውን መለስኩ፡፡  

ደስ የሚል  ድምጸት ባለበት አነጋገር  ʺእንኳን ደህና  መጣህ” አሉኝ፡፡ ምስጋናዬን ገለጽኩ፡፡ ለካስ ፍቅር ድንበር የለውም፣ ጊዜ አይገድበውም፣ ዘመን አይሽረውም፡፡ በፍቅር ዋጋ ስንት እየተተረፈ በጥል ዋጋ ለምን መክሰርን መረጥን? ዳሩ የጥሉ ዘመን አልፎ የፍቅር ዘመን መጥቷል፡፡ የተከዜ ድልድይም  ፍቅር ተርበው የነበሩ አፍቃሪዎችን እያመጣ፣ እየወሰደ ነው፡፡

ማስታወሻ ይሆነኝ ዘንድ ምስሎችን አሰቀረሁ፡፡ ኤርትራዊያን ወታደሮችን ተሰናብቼ በሑመራ ጫፍ የምትውለበለበውን የኢትዮጵያ ሠንደቅ በፍቅር እየተመለከትኩ ተመለስኩ፡፡ ጀንበር እየተፋጠነች ነው፡፡ በዋና የሚታደሱት ነዋሪዎች ግን የመሸባቸው አይመስልም፡፡ በደስታ ይንሳፈፉበታል እንጂ፡፡ 

ʺለተጠማ ወተት የዘመናት ሚዜ

ዳግም እስክመለስ ደህና ሁን ተከዜ” ተሰናብቸው በሑመራ ጎዳናዎች እያዘገምኩ ወደ ማረፊያዬ አቀናሁ፡፡  ተከዜ ያለፈውንና የሚመጣውን እየታዘበ ስለ ሚኖር አስቀናኝ፡፡

(ታርቆ ክንዴ ~አሚኮ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top