Connect with us

የጥሞና ጊዜው ለዘለዓለም ቢኾን የኢትዮጵያም ህዝብ ባረፈ፤ 

የጥሞና ጊዜው ለዘለዓለም ቢኾን የኢትዮጵያም ህዝብ ባረፈ፤
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የጥሞና ጊዜው ለዘለዓለም ቢኾን የኢትዮጵያም ህዝብ ባረፈ፤ 

የጥሞና ጊዜው ለዘለዓለም ቢኾን የኢትዮጵያም ህዝብ ባረፈ፤ 

(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)

የጥሞና ጊዜ የምትለዋን ሀሳብም ቃልም ወድጃታለሁ፡፡ ምነው እንዲህ ያለው ፓለቲከኛ ነኝ ባዩን አፉን የምታዘጋ ዘመን ዘለዓለም ብትሆን፡፡ የምርጫ ቦርዷ መሪ ስላልተሰዳደባችሁና ስላልተጠላላችሁ አመሰግናለሁ ብለው ያመሰገኗቸው ፖለቲከኞች አሁን እስከ ምርጫው አደብ እንዲገዙ ህግ አስገድዷል፡፡ እኔ ደግሞ የተመኘሁት ምነው ዘለዓለም የምርጫው ዋዜማ በሆነ ብዬ ነው፡፡

መንገድ ሲዘጋብኝ፣ የቸገረው ሁሉ ችግር ፈቺሽ ነኝ ሲለኝ፤ ራሱን ነጻ ሳያወጣ ነጻነቴ በእጁ እንደሆነ ሲነግረኝ፣ በአበል ስስት ሰክሮ አበለጽገሃለሁ ሲለኝ፤ እከሌ ከእከሌ በሌለበት ሁኔታ ፓርቲ የሰከረበት ሰሞን ነበር፡፡ የጥሞናውን ጊዜ እያጣጣምኩ ነው፡፡

የጥሞናው ጊዜ ዘለዓለም ቢሆን የኢትዮጵያ ህዝብ የጥቅሙ እፎይ ይላል፡፡ እኔ አውቅልሃለሁ የሚለው ሁሉ ህግ ይገድበዋል፡፡ መኪና ላይ ሞንታርቦ ጭኖ የሚሰብከው ፖለቲከኛ ሁሉ ዝም የሚልበት ድባብ ለኢትዮጵያ ሁሌም ቢሆን ደስ ይላል፡፡

የምርጫው ዋዜማ ሰላም እስከ ምርጫው እንዲዘልቅ ፖለቲከኞች አደብ ቢገዙልን ሸጋ ነበር፡፡ አንዳንዴ እነሱ ሲሰክሩ አንጎቨራቸው እኛን ያጠፋናል፡፡ ደስታቸውም ሀዘናቸውም መከራ ነው፡፡ ሁሉም ስሜታቸው ግን እኛ ላይ ሲደርስ ሀዘን ነው፡፡

የፖለቲከኞች የምርጫ ዋዜማ መንፈስ ድህረ ምርጫ ዘልቆ ፖለቲካ መገዳደያ ሳይሆን ሳይንስ እንዲሆን እንመኛለን፡፡ በምኞት ከምንቃጠል የምንፈልገውን እውን የሚያደርግልን ፖለቲከኛ እንሻለን፡፡ በየትኛውም ምርጫ ሰላም ፍቅር እና ኢትዮጵያ ቢያሸንፉ ድሉ የኛ ነው፡፡

የጥሞናው ጊዜው ገደብ የለሽ ሆኖ ፖለቲካ እና የፖለቲካ ንግድ ያሰከረው ሁሉ አደብ ቢገዛልን ብዙ እንጠቀማለን፡፡ ብልጽግና በድብቅ ከጥሞና ገዳሙ እንዳይወጣ፤ ጥሞና ላይ ነን ሲባል ሾልኩ ጥሞና የሚጥስ ተፎካካሪም እንዳይኖር እመኛለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከምርጫ ዋዜማም ባሻገር አመቱን ሙሉ ቀኑን ሙሉ ለፖለቲከኞቻችን የጥሞና ጊዜ ቢሆን ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ ጥሞና ራስን ያስገዛል፤ ከሞት ሀሳብም ሆነ ከነውጥ ይመልሳል፡፡ ስለ ሰው ግድ እንዲሰጠን እድልም ይሰጠናል፡፡

ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ጥሞና ጊዜ ገደብ ፈጣሪም ቢጥልልን ምንኛ ደስ ባለን፡፡ ፖለቲከኞቻችን የታሰሩትም ያልታሰሩትም፣ የሚፎካከሩትም ሀገር የሚመሩትም ዝም ቢሉ፤ ብዙ ጥሞና አመታት ቢኖራቸው ሀገር ምንም አትሆንም፡፡ ሀገር ከረሃብ በላይ፣ ሀገር ከድህነት በከፋ፣ ሀገር ከጦርነት በባሰ መልኩ በፖለቲከኞች ምላስ የደማችውና የቆሰለችው ይበልጣል፡፡ እናም እንዲህ ያለው የጥሞና ጊዜ ገደብ የለሽ ሆኖ ቢቀጥል መልካም ነበር፡፡

የእኛ ሀገር ፖለቲከኞች መናገርን የነጻነት መብት ብለው ይሞግቱና ተናግረው ግን የመኖር መብታችንን ይገፉታል፡፡ ፖለቲካ ምኔ ነው የሚል ዜጋ የፈጠሩት ፖለቲከኞቻችን ናቸው፡፡ ዝምታቸው የሚያስፈልገን እንደ ህዝብ በፖለቲካ እንድንነቃ፣ በሀገራችን ባለቤት እንድንሆን፣ እርስ በእርስ እንድንደማመጥ ነው፡፡

እዚህ ሀገር ለፖለቲከኛ ጥሞና ወሳኙ ነገር ይመስለኛል፡፡ ባይኖረን እንኳን ብንበደር ወለዱ አያስፈራም፡፡ ብንለምን እንኳን ከጥሞና በላይ እርዳታ ስለሌለ አያሳፍርም፡፡ ጥሞና ለፖለቲከኞቻችን ማለት ሰላም ለእኛ ለዜጎች ማለት ነው፡፡ ሰላምን የመሰለ ምንም የለም፡፡ ሀገር ሰላም ይሁን፡፡  

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top