Connect with us

የአፍሪካ ቀንድ ፡ ”የአሜሪካ  ትዝ አለኝ የጥንቱ …” አዲስ ዘፈኗ ይሆንʔ

የአፍሪካ ቀንድ ፡ ”የአሜሪካ ትዝ አለኝ የጥንቱ …” አዲስ ዘፈኗ ይሆንʔ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የአፍሪካ ቀንድ ፡ ”የአሜሪካ  ትዝ አለኝ የጥንቱ …” አዲስ ዘፈኗ ይሆንʔ

የአፍሪካ ቀንድ ፡ ”የአሜሪካ  ትዝ አለኝ የጥንቱ …” አዲስ ዘፈኗ ይሆንʔ

( እስክንድር ከበደ ~ ድሬቲዩብ)

በአንድ ወቅት የደቡብ ኮሪያ ወጣቶችን ልኡካን ወደ አዲስ አበባ መጥተው ነበር፡፡ የጦር ኒሻን ደረታቸው ላይ የተደረደሩ አዛውንቶች በእድሜ ብዛት ደክመው ይታያሉ፡፡ ይህ ክስተት የአንድ ቀን የዜና ውልብታ ከመሆን የዘለለ ትርጉም አልነበረውም -ለእኛ ፡፡ ለደቡብ ኮሪያ ወጣቶች ግን ዛሬ በሀገራቸው በጀግንነቱ ስለሚወሳ የአንዲት አፍሪካዊት ጦር አስደማሚ ታሪክ እየሰሙ አድገዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ ወጣቶቹ የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾችን ጉልበቶች ይስማሉ፡፡ በዛ ምሽት የቴሌቪዥን ምሽት ዜና እንደዋዛ ብልጭ ብሎ አለፈ፡፡ ከኮሪያ ድረስ አዲስ አበባ የመጡት ልጆች ዓለምም ሆነች ሀገራቸውም የረሳቻቸውን አዛውንት አባት ጦር አባላት አስታውሰው የመጡት በምክንያት ነበር፡፡

የኮሪያ ጦርነት እ.ኤ.አ ከሰኔ 15 ቀን 1950 እስከ ሐምሌ 27 ቀን 1953 አመተ ምህረት የተካሄደ ነበር፡፡ ጦርነቱ በሰሜን ኮሪያ በኩል ሶቬየት ህብረትና ቻይና የደገፉት ሲሆን፤ በደቡብ ኮሪያ ወገን ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተለይ በአሜሪካ ዋና አጋዥነት የተካሄደ ጦርነት ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ሩቅ ምስራቅ የኮርያ ልሳነምድር ወታደሮቿን በመላክ እጅግ የሚያኮራ ተግባር መፈጸሟ ይታወቃል::

በኮርያ ጦርነት የተሳተፈው የቃኘው ሻለቃ 238 ጊዜ ተዋግቶ ሁሉንም አሸንፎ ነበር::የኢትዮጵያ ሰራዊት ከክቡር ዘበኛ ክፍለጦር የተውጣጣ ሲሆን ፤121 ወታደሮች ቢሞቱበትም አንድም እሬሳ ጠላት እጅ አልወደቀበትም::ከ20 በላይ ሀገራት በተሳተፉበት የኮርያ ጦርነት የምርኮ ልውውጥ ሲደረግ አንዲት ሀገር ግን አንድም ወታደር አልተማረከባትም ::

በኮርያ ጦርነት አንድም ወታደር ያልተማረከባት ኢትዮጰያ ብቻ ነበረች ::ይህ በአሜሪካ መራሹ ጦር ተደናቂ አድርጓታል::ለዛም ነበር አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ እ.ኤ..አ በ1953 በአስመራ የሚገኘውን ግዙፍ ወታደራዊ ሰፈሯን ቃኛው ስቴሽን የሚል ስሜ የሰጠችው ::

ቃኛው ሻለቃ እንደ አውሮፖውያን አቆጣጠር ከ1950 እስከ 1953 በተካሄደው የሁለቱ ኮሪያዎች ጦርነት የዘመተው የኢትዮጰያ ጦር መጠሪያ ነበር:: አሜሪካ ቃኘው ስቴሽን በቀድሞ ኢትዮጰያ በአሁኗ ኤርትራ በአስመራ የሚገኝ ግዙፍ ወታደራዊ የመገናኛ ጣቢያ ሠፈር ገንብታ ነበር:: የጦር ሠፈሩ ቀደም ሲል የጣሊያን የባህር ኃይል ሬዲዮ ጣቢያ ማለትም ሬዲዮ ማሪና (Radio Marina) በመባል ይጠራ የነበረ ተቋም ነው:: 

የጣሊያን ኃይሎች እ.ኤ.አ. በ1941 መሸነፋቸውን ተከትሎ፣ የአሜሪካ ጦር በ1943 ዳግም በማደስ ጣቢያውን ይጠቀምበት ጀመረ:: ቃኘው ጣቢያ እ.ኤ.አ. እስከ ሚያዚያ 28 ቀን1977 ድረስ በአሜሪካ ጦር ቁጥጥር ሥር ነበር::

ቃኘው ስቴሽን የቀዝቃዛው ጦርነት የመስሚያ ጣቢያ(Cold War Listening Station) ሆኖ አገልግሏል:: የቀዝቃዛው ጦርነት መረጃ መሰብሰቢያ ዲሾች አሥር ኪሎ ሜትር ስኩዌር ላይ ያረፈ አንቴና የተገጠመለት ግዙፍ ጣቢያ እንደነበር ይነገራል:: ይህ ግዙፍ ወታደራዊ የኮሙዩኒኬሽን ግንኙነት ጣቢያ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በምሥራቅ አፍሪካ ወሳኝ ወታደራዊ ሠፈር ነበር:: እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ አምስት ሺሕ አሜሪካ ዜጎች ይኖሩበት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ::

እ.ኤ.አ. በ1971 እየተካሄደ በነበረው ጦርነት በከረንና በምፅዋ የሚገኙት ማዕከላቱ ለአጭር ጊዜ ተዘግተው ነበር:: የአሜሪካ ጦር በቃኘው ስቴሽን የሚገኙ ወታደሮችና ባለሙያዎች ለማቆየት በዓመት 12 ሚሊዮን ዶላር ያወጣ ነበር::

እ.ኤ.አ. በ1941 የሩዝቬልት አስተዳደር ለኢትዮጵያ ወታደራዊ ድጋፍ ፕሮግራም እንደሚያስፈልጋት ይፋ አድርጎ ነበር:: በወቅቱ ብሪታኒያ በጣሊያን ተይዞ የቆየውን ሬዲዮ ማሪና ተብሎ የሚጠራውን የኮሙዩኒኬሽን ምድብ ለማደስና ለማዘመን ብዙ ወጪ አውጥታበት ነበር::አሜሪካ ይህንን የጦር ሠፈር ለመገንባት 77 ሚሊዮን ዶላር እንዳወጣችበት ይነገራል:፡

እ.ኤ.አ በ1953 የጦር ሠፈሩ በይፋ ስሙ ቃኘው ስቴሽን ተብሎ እንዲጠራ ተደረገ:: ጣቢያው  አቅርቦቱን በአውሮፕላኖች  የሚያገኘው ከሳዑዲ ዓረቢያ ዳህራን ምድብ ነበር:: ከምግብ ሸቀጣሸቀጦች  እስከ ዘመናዊ  የውትድርና የስለላ መሳሪያዎችን  በመርከብ በምጽዋ በኩል ይገባለት  ነበር፡፡እ.ኤ.አ. ዓርብ መስከረም 12 ቀን1975 የኤርትራ ነፃነት ግንባር የአሜሪካ የጦር ሠፈር በመግባት ሁለት አሜሪካውያንን ጨምሮ 12 ሰዎችን አፍኖ መውሰዱ ይነገራል:: 

በኋላ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተፈጠረ የርዕዮተ ዓለምና ልዩ ልዩ ምክንያቶች አሜሪካ እ.ኤ.አ 1977 የጦር ሠፈሩን ለቃ ወጥታለች:: የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰላም ማስከበር መልካም ዝናና የጀግንነት ታሪክ ከኮሪያ ጦርነት ይጀምራል፡፡ ይህ ታሪክ ከተጠና ምርጥ ፊልም ይወጣዋል፡፡ፈረንሳይ ሰፈር መዳረሻ ላይ በሚገኝ ማዞሪያ የሚታየው የኢትዮጵያና የደቡብ ኮሪያ የወዳጅነት ምልክት ይህንኑ ውለታ ለማስታወስ ነው፡፡

አሜሪካ  ከቃኛው ሻለቃ ከወጣች በኋላ እ.ኤ.አ በ2001  አመተ ምህረት የመስከረም 11  የሽብር  ጥቃትን ተከትሎ ፤በአፍሪካ ቀንድ  የአፍሪካ ቀንድ ጥምር ግብረሀይል በሚል  አሜሪካ  እ.ኤ.አ በ2002 ከጂቡቲ መንግስት  የቀድሞ  የፈረንሳይ  ወታደራዊ ካምፕ የነበረውን  ካምፕ ሌሞኒይርን  በሊዝ ተከራይታ አፍሪካ ቀንድ ገባች፡፡ አሜሪካ  እ.ኤ.አ በ2015   አመተ ምህረት  ለ20  አመታት  ውሏን ያደሰች ሲሆን፤ በጂቡቲ  ለሚገኘው  የጦር ሰፈር  ኪራይ  በየአመቱ 70 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማምታለች፡፡

የኤርትራው ቃኛው ሻለቃ ስቴሽን 14 ስኩዬር ኪሎሜትር ይዛ የነበረችው አሜሪካ፤ በትንሿ ጂቡቲ 2 ስኩዬር ኪሎሜትሮች የሚሸፍነውን የጦር ምድብ ለሚቀጥሉት ሁለት አስርት አመታት በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ለማደስ  ወጥን ይዛለች፡፡  ጂቡቲ የሩሲያም ወታደራዊ ምድብ ለመክፈት ፍላጎት እንዳላት የጠየቀች ሲሆን፤ የጂቡቲው አልተቀበለችም ፡፡ ለፈረንሳይና ለጃፓን የፈቀደችው ጂቡቲ ፤ የአሜሪካ አጋሮች ስለሆኑ መሆኑ ይነገራል፡፡ በቅርቡ ለቻይና መፈቀዱ ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ ወደ ውጥረት እየወሰደ ይመስላል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከ1990 እስከ ሰኔ 1992 ዓመተምህረት ድረስ ያካሄዱት ደምአፋሳሽ ጦርነት ከማብቃቱ አንድ ወር በፊት የአሜሪካ ጡረተኛ የስለላና የወታደራዊ ጠበብቶችን ወደ ቀድሞ የጦር ሰፈሯ “ራዲዮ ማሪያ” ወይም “ቃኘው ሻለቃ” ጣቢያ ልካ፤ጡረተኞቹ የየዘርፉ ልሂቃን “ሪዩኒየን” በሚል ደግሰው ሲዝናኑ የሚያሳይ አጭር  ቪዲዮ እ.ኤ.አ ሜይ 23፣2000 ለቀው ነበር፡፡ 

በአሜሪካ መንግሥት በኩልም ይህ ስትራቴጂክ የጦር ሰፈር አሁንም ተፈላጊነቱ  እንዳለ ይመስላል፡፡ በወቅቱ ዝግጅቱ ላይ የኢትዮጵያና ኤርትራ ባንዲራዎች  መሐል የአሜሪካ ባንዲራ ጠረጴዛ ላይ ደርድረው ይታያሉ፡፡ እነርሱ በደረሱ በጥቂት ሳምንታት የኢትዮጵያና የኤርትራ  ጦርነት በአፋጣኝ እንደቆመ ተሰማ፡፡ የአሜሪካ ወታደራዊና የጸጥታ ጠበብት የሁለቱ ሀገራት ጦርነት ፈጥኖ መቆም እንዳለበት መንግሥታቸውን  ሳያማክሩ አልቀረም፡፡

በዚህ መድረክ አዛውንቶቹ የስለላና የጦር ጠበብት ከ“ቃኘው ሻለቃ”  ወጡ እንጂ  “ቃኘው ሻለቃ” ከውስጣቸው አለመውጣቱ  የሚያሳይ ምልክቶች አሉ፡፡ የአሜሪካ  የአፍሪካ ቀንድ  ልዩ ልኡክ መመደቧ  ከምትዘረዝራቸው ምክንያቶች ባሻገር ማየት ያስፈልጋል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ  የሁለተኛው  ቀዝቃዛ ጦርነት አውደ ግንባር  እየሆነ ለመምጣቱ ምልክቶች እየታዩ ናቸው፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top