ኢትዮጵያውያን ነን፤ ቋንቋችን አንድ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊም ከአፍጥር እስከ ኢድ በዓለም ፊት!!
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬቲዩብ)
ዓለም ምክንያት ይፈልጋል፡፡ አንድ ነን እያልነው ብዙ ቦታ ሊያደርገን ይመኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ እኛን የሚመስል ብዙ ቦታ ከፋፋይ የአብራክ ክፋይ ጭምር ይልክብናል፡፡ ሊጥሉን የሚላኩት በሁሉም ቀጠና፣ እምነትና ብሔር አሉ፡፡ አንድ ላይ የምንቆመው ግን መቶ ሚሊዮን ነን፡፡ በድፍን ኢትዮጵያ፣ በሁሉም እምነትና በሁሉም ማንነት ያለን፡፡
ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ አባቶቻችንን ታውቋቸዋላችሁ፡፡ ጥቂት የሚሸነገሉ እልፍ አእላፍ እንቢኝ ብለው አብረው የሚቆም ምድር የተፈጠርን ነን፡፡ ቋንቋችን እንዲህ ነው፡፡ አንድ ዓይነት፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊም ከጎናችሁ እንዲቆም ቃዥታችሁ ይሆናል፡፡ ከኢትዮጵያ ይሄን ይሄን ብሔር ነጥለን እናራቁታታለን ብላችሁ ተመኝታችሁ ይሆናል፡፡ ግን አይሆንም፡፡ አደባባይ ላይ በቋንቋችሁ የሚሞግቷችሁ ጥቂቶች ብቻ አባቶቻቸውን የሚመስሉ ኩሩ ሙስሊሞች ከመሰሏችሁ ተሳስታችኋል፡፡ ብዙ ሚሊዮኖች እንዲህ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የእኔ ናት የሚሉ፡፡
ብዙ ቁጥር ያለው ሙስሊም ጎዳና ወጥቶ ሲያፈጥር ተመልክታችኋል፡፡ እናንተ ዘንድ አደባባይ ከወጣው የሚበልጥ ቁጥር ያለው፡፡ ይሄ ማዕበል በደማቅ የጎዳና ላይ አፍጥር ሥርዓቱ ለዓለም እንዲህ ያሉ መልእክቶችን ተናግሯል፡፡ ግድቡ የኔ ነው፡፡
በየቦታው የምንገደለው፣ የምንሰደደው፣ የምንበላው በጥቂት ቁጥራቸው ቁጥር በማይገባ የኢትዮጵያ ጠላቶች ተልእኮ ማስፈጽም ተግባር ነው፡፡ ዛሬም ግን ከኢትዮጵያውያን ልብ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማውጣት አይቻልም፡፡
ታቦት ይዘን ብንወጣ ሀገሬ የኔ ናት የምንል ነው፡፡ ለአፍጥር ጎዳና ብናደምቅም ሀገሬ የኔ ናት ባይ ነን፡፡ ዝምታችን የአባቶቻችን ትህትና ነው፡፡ ዝምታችን ሀገራችሁ የእናንተ አይደለም ሊሉን ለሚፈልጉ የአዎንታ ምላሽ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዓለምን ከአፍጥር እስከ ኢድ በሚገባው ቋንቋ ያናግሩታል፡፡ በብሔርና በእምነት ብዙ ጎራ ሊያደርጉን የሚሹ ከታሪካዊቷ ሀገር ታሪካዊ መልእክት ይደርሳቸዋል፡፡ ጥቂት ወንድሞቻችን በቋንቋቸው ሲነግሯቸው የኖሩትን ሚሊዮኖች በአደባባዮች ደግመው ያረጋግጡላቸዋል፡፡
አባቶቻችን አብረው የሞቱላትን ሀገር አብረን እየሰራናት እንደሆነ ዓለም ዳግም በኢድ አፍጥር እንደተረዳው በኢድ ሶላድ በቅጡ ይገባዋል፡፡ እኛ አንድ ነን፡፡ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ ቅጥረኛ ጠላቶቻችን ይልቁንስ አንድ ከሆኑት መቶ ሚሊዮን ወገኖቻችሁ ጋር ቁሙ፡፡ ምሰሶው ይነቃነቃል እንጂ አይወድቅምና፡፡