Connect with us

እንደ ዜጋ ከምርጫው ሂደትና ውጤት የምንጠብቀው እሴት!!

የመራጮች መዝገብ ለ10 ቀናት ለሕዝብ ክፍት ሊሆን ነው
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

እንደ ዜጋ ከምርጫው ሂደትና ውጤት የምንጠብቀው እሴት!!

እንደ ዜጋ ከምርጫው ሂደትና ውጤት የምንጠብቀው እሴት!!

(ንጉሥ ወዳጅነው ~ ድሬ ቲዩብ)

የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይባሉ ድርጅቶች የመድብለ ፓርቲ ስረአት መሰሶ ናቸው፡፡ የምርጫ ስርአት፣በተለይም የብዝሃ አስተሳሰብ ፀጋ ተደርገውም ነው የሚወሰዱት፡፡ይህ ነባራዊ ሀቅ እኛን በመሰሉ ለጋ የዲሞክራሲ ባላቸው አገሮችም ቢሆን እየወደቀ እየተነሳ መከበርና መቀጠል አለበት ፡፡

ከዚህ አንፃር ዘንድሮ እየተካሄደ ባለው የአገራችን ብሄራዊና ክልላዊ ምርጫ ከቅድመ እስከ ድህረ ሂደቱ ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የሚጠበቁባቸውን ሃላፊነቶች በጥንቃቄ መከተል ግድ ይላቸዋል ፡፡ በምንም መንገድ የህዝብ ህልውና ፣ የአገር ብሄራዊ ጥቅምና የህግ የበላይነትን ለድርድር ሊቀርቡ አይችሉም ፡፡ አይገባም ፡፡ መርሃቸው በመፎካካር መጣፋፋት፣ ሳይሆን ፣ በመወዳዳር ለአንድ አገር መስራት የውዴታ ግዴታቸው ነው ፡፡

ከዚህ በላይ ግን በዘዴና በብልሃት ፣ በመቻቻልና በመግባባት፣ በዴሞክራሲ አግባብና በሰላም የአገሪቱን አጠቃላይ እድገትና ልማት ለማፋጠንና ለማስቀጠል በሚያስችል አግባብ ችግሮችን በሰለጠነ አካሄድ እየፈቱ መሄድ አለባቸው ፡፡ ይህ ሁኔታ ከሞላ ጎደል እስከአሁን ባለው የቅድመ ምርጫ ምእራፍ የከፋ ጉድለት ገጥሞታል ማለት አይቻልም ፡፡

ያለንበት ዘመን አለም የሰለጠነበትና ችግሮች ሁሉ በሰላምና ዲሞክራስያዊ መንገድ የሚፈቱበት ነው ፡፡ኢትዮጵዊያንም ቢሆኑ እውነተኛ የመንግስት ስልጣን የሚገኘው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መሆኑን ለአፍታ መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ዜጎች ይህን ምኞት እውን እያደረጉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲቀባባሉ ደግሞ የፓርቲዎች ዲሞክራስያዊነት ፋይዳው ከፍተኛ ነው ፡፡

ፓርቲዎች በቅድመ ምርጫ ጊዜ አላማቸውንና የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ‹‹በምርጫ ቅስቀሳና በፓርቲዎች ክርክር ላይ አቅርበናል… ህዝቡ እንዲመርጠን ግንዛቤ አስጨብጠናል፡፡›› ካሉና ህዝቡም ‹‹ባገኘሁት ግንዛቤ ላይ ተመስርቼ የሚበጀኝን መርጫለሁ›› ብሎ ድምፁን ከሰጠ በኋላ ምንም አይነት ግርግርና ሁከት ሊፈጥሩ አይገባም ፡፡

የህዝቡ ድምጽ ታዛቢዎች በተገኙበት ከተቆጠረ በኋላ የምርጫ ቦርዱ ውጤቱን እስኪያስታውቅ ድረስ በጥሞናና በማስተዋል አደብ ገዝቶ መጠበቅም  ግዴታቸው  ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ቦርዱ ያሳወቀውንና በይፋ የገለፀውን ውጤት በፀጋ መቀበል የጨዋነትና አገር ወዳድነት ሥነ-ምግባር መገለጫ ነው ፡፡ 

ውጤቱን ተቀብሎ ከዚህ ሁኔታ ተምሮ ለወደፊቱ ምርጫ እንዴት መዘጋጀት እንዳለበት በጥንቃቄ መመርመር እንጂ፣ ውጤቱን ‹‹አልቀበልም›› የማለት ሞራል ለገዥውም ለተፎካካሪ ፓርቲዎችም የተፈቀደ አይደለም ፡፡

እባህሩ ዳርቻ ያሉ ህፃናት ልጆች ባህሩ እየገፋ በሚያመጣላቸው አሸዋ ደስ እያላቸው ሲሰሩ የዋሉትን ቤት በስተመጨረሻ ላይ ደስ እያላቸው አፍርሰው የሚሄዱበት ጨዋታ አላቸው፡፡ ምርጫ ግን የልጆች ጨዋታ አይደለም፡፡ ብዙ እውቀት፣ ጉልበት፣ ገንዘብ፣ ጊዜ… ወጥቶበት ስንትና ስንት መስዋዕትነት ተከፍሎበት የተጠናቀቀ ምርጫ ውጤት እንደአሸዋ ቤት በቀላሉ የሚፈርስ ሊሆን አይችልም፡፡

እስኪ ዘንድሮ በአገራችን  አዲስ የዲሞክራሲ መንፈስ ይጀመር !!  በምርጫው ማንም ያሸንፍ ማን ‹‹ እንኳን ደስ ያለህ!›› የሚል የተፎካካሪዎች አንደበት ይደመጥ ፡፡

በባህላችን መሰረት ትከሻ ለትከሻ ተሳስመው ሲሆን… ሲሆን እርጥብ ሳር… የወይራ ዝንጣፊ ወይም አበባ ሰጥተው… ‹‹የተቃና የሥራ ዘመን ይሁንልህ፣ እኛም በምንችለው ሁሉ ከጐንህ ነን… ይቅናህ!›› ብለው ተመራርቀውና ተዘያይረው ለመሪ (ገዥ) ፓርቲነቱ እውቅና ሰጥተው ሲለያዩ እንመልከት ፡፡ ካለጥርጥር ይሄ የሰላም ወዳዶች ሁሉ ምኞት ነው!!

ሁሉም አሸናፊ መሆን አይችልምና ተሸናፊ ፓርቲዎች ይህን  ቢያደርጉ የኢትዮጵያ ህዝብም በተስፋ ኑሮውን ይቀጥላል ፡፡ በልጆቹ ይደሰታል ፣ በአገሩ ይኮራል፡፡

 ለህዝብ ድምጽ መገዛት… ተሸናፊነትን መቀበል… አሸናፊውን ማክበር ለአጠቃላዩ አገሪቱ ዕድገት ልማትና ሰላም ሲባል ሁኔታዎችን በትዕግስትና በመቻቻል ማለፍ ፣ መግባባትና መስማማት ለህዝብ የሚሰጠው እርካታና በዓለም ፊት የሚያስገኘው ሞገስ በምንም መለኪያ ሊሰፈር ከሚችለው በላይ ነው ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብም የሚጠብቀው ይህንን መሆኑን መዘንጋት አይገባም ፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top