Connect with us

የእንስሳት ለህጻናት ርህራሄ

የእንስሳት ለህጻናት ርህራሄ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የእንስሳት ለህጻናት ርህራሄ

የእንስሳት ለህጻናት ርህራሄ

(ኘሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ)

ልብ ብላችሁ ከሆነ እንስሳት የእንስሳትንም ሆነ የ ሰውን ህጻናት አይበሉም። በእራሴም ውሾች  ሆነ በዱር እንስሳት ፊልም እንዳየሁት የአደገ እንስሳ የራሱንም ሆነ የሌላ እንስሳ ህጻንን በፍጹም አይጎዳም። እንዳውም ፍቅሩን ለመግለጽ ህጻኑን ይልሳል። ትልቋ እንስሳ ሴት ከሆነች ደግሞ ያልወለደችውን ህጻን ታጠባለች።

የዱር እንስሶች የሰውን ልጅ ህጻኖችን ካገኙ እንኳን ህጻንነታቸውን ተገንዝበው  አይበሉአቸውም። በሚችሉት ሁሉ ይረዷቸዋል እንጂ። ጨካኝ እናቶች ጨቅላዎቻቸውን ገስጋሽ ባቡር  ሀዲድ ላይ፣ ኩሬ ውስጥ ወይም ቁሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ ሲጥሉ እንስሳት ሲያድኗቸው አስተውለናል።  ሰው ነኝ ባዩ አረመኔ ግን አቅም የለሽ ህጻናትን በሳንጃ ይወጋል። ሳይሰቀጥጠው ያርዳልም።

ውሾች ሲጣሉ ተሸናፊው ውሻ መሸነፉን ለመግለጽ በጀርባው ሲተኛ አሸናፊው ውሻ ለስላሳ ሆዱን አይዘነጥለውም። ራርቶለት ይተወዋል። ሰብአዊ ፍጡር ነኝ የሚለው ባለሁለት እግር አውሬ ግን ያሸነፈውን እና የገደለውን አምሳያውን ፍጡር መግደሉ ሳያንሰው ዐይኑን ጎልጉሎ አውጥቶ ሥጋውን ይቆራርጣል።

ከሰው ልጅ ይልቅ በባህሪው እና በጸባዩ እንስሳ ከላቀ እንግዲህ ሰው ክቡር ነው የምንለው ለምንድነው? ሰው ሁሉ እኩል ነው ለማለትስ እንዴት እንችላለን? በትምህርት በባህል እና በስነምግባር ካልተገራና ካልታሸ የስው ልጅ ጥሬ  ጭራቅ ነው።

በህጻናትም ላይ ሆነ በድኩማን ላይ ሰው ከእንስሳት አንሶና ዘቅጦ የጭካኔ ሥራ ሲፈጽም በሁለት እግሩ ቆሞ ስለሄደ ብቻ ሰው ተብሎ ከተከበረ ዶሮም በሁለት እግሩ ስለሚሄድ እንደሰው መከበር ይገባዋል።

ሰውን ክቡር የሚያደርገው ሲያጠፋ የሚወቅሰው ኅሊና  ሲኖረው፣ ለሰው ልጅ ህይወት እና ነፍስ ዋጋ ሲሰጥ እና ሰብአዊ ርህራሄ ሲኖረው ነው። እነዚህ መልካም እሴቶች ከሌሉት ግን ከእንስሳ ያነሰ በመሆኑ በድኩማን ላይ ጥቃት ሊያደርስ በማይችልበት ስፍራ መገታት ይኖርበታል። በእዚህ ዓለም ላይ የመኖር መብቱ ቢገፈፍም አያስደንቅም። እሱ እንዲኖር ከተፈቀደለት ሌሎች እንዳይኖሩ ሊያደርግ ይችላልና።

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top