ይድረስ ለአዲስአበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የግብር ይውጣ አሰራር ይፈትሹልን?!
ክቡርነትዎ ይህን ማስታወሻ የምንጽፍልዎ በአዲስአበባ ውሃን ፍሳሽ ባለስልጣን የውሃ ፈረቃ አሰራር ፍትሐዊነት ጋር በተያያ ከባድ ቅሬታ ስላደረብን እንደሚፈቱልን በመተማመን ነው፡፡ ምናልባትም የባለስልጣኑ ማኔጅመንት ጉዳዩን በቀናነት አይቶ በራሱ ተነሳሽነት አሰራሩን በመፈተሸ ፈጣን የእርምት እርምጃ እንደሚወስድም በመተማመን ነው፡፡
ክቡርነትዎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲስአበባ የመጠጥ ውሃ እጥረት እየተባባሰ መምጣቱ የሚታይና እየኖርን ያለነው እውነት ነው፡፡ በመሀል አዲስአበባ ሳይቀር ውሃ በተከታታይ ከሳምንቱ ቀናት ከግማሽ በላይ ወይንም ለሶስትና ለአራት ቀናት መጥፋት ተለምዷል፡፡ ክቡርነትዎ ሳይቀር እንደማንኛውም ነዋሪ የውሃ ችግሩን እየኖሩት እንደሚያውቁት ሰሞኑን ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ መናገርዎን እናስታውሳለን፡፡
አሁን ጥያቄያችን ለምን ውሃ ይጠፋል የሚል አይደለም፡፡ ነገርግን ውሃና ፍሳሽ ከዚህ ቀደም እንደሚደርገው የፈረቃ አሰራሩን በግልጽ ማድረግ ለምን አቃተው የሚል ነው፡፡ እንደሚታወቀው አምናም ካቻምናም ተመሳሳይ ችግር ባጋጠመበት ወቅት ባለስልጣኑ የፈረቃ አሰራሩን ግልጽ በማድረጉ የከተማው ነዋሪ መቼ ውሃ እንደሚጠፋ፣ መቼ እንደሚመጣ ያውቃል፡፡
ውሃን በቁጠባ ስለሚጠቀም ለተጨማሪ ወጪ የሚዳረግበት ሁኔታ የለም፡፡ የዘንድሮ የተገላቢጦሽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አሰራሩ ነዋሪዎች ለከባድ ምሬት የዳረገ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ በአሁን ሰዓት አንድ 25 ሊትር የሚይዝ ውሃ ፈልጎ አስቀድቶ ለማምጣት ለቀን ሙያተኞች በበርሜል 20 ብር እና ከዚያ በላይ ያስከፍላል፡፡ ይህ ነዋሪው በመንግስት ላይ እንዲያማርር በር ከፍቷል፡፡ ኑሮውንም አክብዶበታል፡፡
አብነት ላንሳ ፤በአራት ኪሎ መሀል ከተማ አካባቢ በሚገኝ ኮንደሚኒየም እኖራለሁ፡፡ ውሃ ሰሞኑን ከማክሰኞ ጀምሮ ጠፍቶ ከረመና ዛሬ ንጋት ላይ አንድ ሰዓት ላልሞላ ጊዜ ብቅ ብሎ እንደገና ጠፍቷል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ለሶስት ተከታታይ ቀናት ውሃ ጠፍቶ አንድ ሰዓት ላልሞላ ጊዜ ለቅቆ እንደገና ማጥፋት ምን ይሉታል? ምን ኣይነትስ ፍትሐዊነት ነው? እንዲህ አይነቱ ስራ መደጋገሙ አሳስቦናል፡፡ ጥቂት የባለስልጣኑ ሰዎች አጋጣሚውን ሽፋን በማድረግ ሳቦታጅ እየሰሩ ይሆን የሚል ጥርጣሬንም ያሳደረብን መሆኑንም መሸሸግ አልፈልግም፡፡
ዋናው ነገር ባለስልጣኑ አሰራሩን ግልጽና ፍትሐዊ እንዲያደርግልን ነው፡፡ ግልጽ ሲባል የፈረቃ ፕሮግራሙን ለሕዝብ እንዲያሳውቅ ነው፡፡ ከመቼ እስከ መቼ ውሃ እንደማይኖር፣ መቼ እንደሚኖር በግልጽ አሳውቆ በዚህ መሰረት ስራውን ማከናወን አለበት፡፡ አለበለዚያ እንደፈለገ ማጥፋት፣ በፈለገ ጊዜ መልቀቅ የሚያሳየው የህዝብ አገልጋይነትን ሳይሆን ዳተኝነትና ምን ታመጣላችሁ አይነት የጥጋብ ምልክትን ነው፡፡
ክቡርነትዎ፤ የከተማዋን ችግር (የውሃ እጥረትን ጨምሮ) ለመፍታት ሌት ተቀን የሚያደርጉትን ጥረት በአንክሮና በአድናቆት ከሚከታተሉ የከተማዋ ነዋሪዎች አንዱ ነኝ፡፡ ነገርግን የፈረቃ የውሃ ስርጭቱ በግልጽነት፣ በፍትሐዊነት አሰራር ማጀብ እንደሚቻል የራሱ የባለስልጣኑ የዚህ ቀደም ተሞክሮ ምስክር ነውና ባለስልጣኑ አሰራሩን እንዲፈትሽና እንዲያስተካክል መመሪያ እንዲሰጡልን በአክብሮት እጠይቅዎታለኹ፡፡
(እሱባለው ካሳ – አራት ኪሎ)