Connect with us

የሀኪሞችን ስራ አጥነት ማስቀረት ባይቻል መቅረፍ ይቻላል!

የሀኪሞችን ስራ አጥነት ማስቀረት ባይቻል መቅረፍ ይቻላል!
ዶ/ር ያሬድ አግደው

ነፃ ሃሳብ

የሀኪሞችን ስራ አጥነት ማስቀረት ባይቻል መቅረፍ ይቻላል!

የሀኪሞችን ስራ አጥነት ማስቀረት ባይቻል መቅረፍ ይቻላል!

(ዶ/ር ያሬድ አግደው)

ወደ ሆስፒታላችን ከሚመጡ ባለጉዳዮች አንዳንዶቹ ስራ አጥ ሀኪሞች ናቸው። ትናንት ሁለት ሀኪሞች ወደ ቢሮዬ ዘልቀው ነፃ አገልግሎት መስጠት እንደሚፈልጉ ገለፁልኝ። ትልቅ ውሳኔ ነው። በተለይ በኮቪድ19 ህክምና መዓከል ህይወታቸውን በነፃ ለህዝባቸው አሳልፈው ለመስጠት መምጣታቸው የሚደነቅ ነው። 

ሰሞኑን በአማራ ክልል ሀኪሞች ለረጅም ጊዜ ስራ ባለማግኘታቸው ያደረጉትን ሰላማዊ ሰልፍ ዙሪያ እየተወያየን ፤ ባለፈው ወር ሆስፒታላችን የስራ ማስታወቂያ ማውጣቱን ሰምተው እንደነበር ጠየኳቸው እና እነሱም ተፈትነው እንካልተሳካላቸው ገለፁልኝ።

ባለፈው ሳምንት የአማራ ክልል ሀኪሞች ከአንድ ሚዲያ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ተመልክቼዋለው። በቃለ መጠየቁ ሰዓት ሶስቱ ሀኪሞች ካነሷቸው ነጥቦች የእኔን ጆሮ የሳቡትን ነጥቦች ማንሳት ፈለኩኝ። በተለይ የክልሉን ጤና ቢሮ ሀላፊ ማግኘት እንዳልቻሉ የገለፁበት መንገድ በጣም አስገርሞኛል። 

በእኔ እውቀት የዛሬው የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ ( ዶ/ር መልካሙ) እጅግ ወጣት እና ከዚህ በፊት በጤናው ስርዓት ላይ ተነስቶ የነበረውን የሀኪሞች እንቅስቃሴ ላይ ተሳታፊ እና በከፊልም መሪ እንደነበሩ አስታውሳለሁ። የሀኪሞች የስራ አጥነት ጉዳይ በአንድ ጀምበር የማይፈታ እና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚፈልግ ቢሆንም የእርሳቸው የሀኪሞችን ሮሮ ለመስማት አለመፈለግ ግን በመንግስት የሚሳበብ ጉዳይ አይደለም። 

ማንኛውም መሪ በተቀመጠበት ስፍራ ባለ ጉዳዮችን በቀጠሮም ቢሆን የማስተናገድ ሀላፊነት አለበት። በተለይ እኚህ ሀኪም ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት በቅርቡ የወጣት ሀኪሞችን ችግር ለመፍታት ትልቅ ድምፅ የነበሩ ናቸው። የሀኪሞችን ችግር አለመስማት የራሳቸውን ድምፅ እንደመጠየፍ ይቆጠራል።

በሁለተኛ ደረጃ ክልሎች (በዚህ ቃለ ምልልስ የተጠቀሰው የኦሮሚያ ክልል ነው) የራሳቸውን ቋንቋ የማይናገር ሰው እንደማይቀጥሩ መገለፁ ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ምክኒያቱም ሰብአዊነት ድንበር የለሽ ነው። እኔ የጠቅላላ ሀኪም እና የቀዶ ህክምና ሀኪም ሆኜ የሰራሁበት ቦታ ቋንቋቸውንም ሆነ ባህላቸውን የማላውቅበት ስፍራ ደቡብ ኦሞ ይባላል ፤ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን ከማህበረሰቡ ከተካፈልኩት ህይወት የተነሳ ከተወለድኩበት ስፍራ በላይ ይናፍቀኛል።

 ብዙ ወዳጅ ዘመዶች አፍርቻለሁ፤ በአመት አንድ ጊዜ እዛ ያፈራዋቸውን ዘመዶቼን ለመጠየቅ እሄዳለው። የኦሮሚያ የጤና ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ዶ/ር መንግስቱ አፍንጫቸው ስር የተደቀነውን ፈተና እንዴት በጥበብ ማለፍ እንዳለባቸው ባላውቅም ይህ መስፈርት በክልሉ ምክር ቤት ፀድቆ የፌደራል መንግስት አውቆት ተፈፃሚ የተደረገ እስካልሆነ ድረስ የዜጎችን በነፃነት ተዘዋውሮ የመስራት መብት የሚጋፋ ነው። 

ይሄ ነገር በቶሎ እልባት ካላገኘ  በቅርቡ ስንመረቅ “የህፃናት ሀኪም” ወይም “የቀዶ ህክምና ሀኪም” የሚለው ማዕረግ ሳይሆን “የኦሮሞ የህፃናት ሀኪም” ወይም “የአማራ የቀዶ ህክምና ሀኪም” የሚል ማዕረግ ይሰጠናል።

በመጨረሻ ሀኪሞቹ ያነሱት ነጥብ ክልሉ ውስጥ ብዙ ክፍት ቦታዎች እያሉ አለመቀጠራቸው እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል። በተለይ የሆስፒታል ሀላፊዎች (እኔን ጨምሮ) በተፈቀደልን መደብ ቅጥር መፈፀም እንዳለብን እና ይህንን ባለማድረጋችን በስራ ባልደረቦቻችንና በወጣቱ ሀኪሞች ላይ ለሚፈጠረው መጉላላት ተጠያቂዎች ነን። የያዝነው ስልጣን ለማገልገል እንጂ ወንበር ለማሞቅ እንዳልሆነ ማወቅ አለብን። በተለይ የሆስፒታል ስራ አስኪያጆች ስራችሁን በአግባቡ ተወጡ። እያንዳንዱ የባለ ድርሻ አካላት ሀላፊነቱን ቢወጣ የሀኪሞችን ስራ አጥነት ማስቀረት ባይቻል መቅረፍ ይቻላል!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top