ቡና ባንክ 8ኛ ዙር “የውጭ ገንዘብ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ “ መርሃ ግብሩን በሽልማት አጠናቀቀ
~ የዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል አሸናፊው የሎተሪ ዕጣ ቁጥር 00636 ሆኗል፣
ቡና ባንክ የውጭ ምንዛሪን ወደህጋዊ መስመር በማስገባት የጥቁር ገበያ ተጽዕኖን ለመከላከል በማቀድ ለስምንተኛ ጊዜ ያካሄደው “የውጭ ገንዘብ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ “ መርሃ ግብር የሎተሪ ዕጣ መጋቢት 8 ቀን 2013 ዓ.ም በብሄራዊ ሎተሪ በዕድል አዳራሽ በህዝብ ፊት በይፋ ወጥቷል፡፡
ባንኩ ላለፉት ሶስት ወራት ያካሄደው ይኸው የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ መርሃ ግብር “ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” በሚል መርህ የተካሄደ ሲሆን ደንበኞች ከውጭ ሀገር ከወዳጅ ዘመዶቻቸው በተለያዩ ገንዘብ ማስተላለፊያ ድርጅቶች በኩል ገንዘብ ሲላክላቸውና በቡና ባንክ በኩል ሲቀበሉ እንዲሁም የውጭ አገር ገንዘብ በቡና ባንክ ሲመነዝሩ እድለኛ የሚሆኑበት የሎተሪ መርሃ ግብር ነው፡፡
በዚሁ የሎተሪ ዕጣ አወጣጥ ስነስርአት ወቅት አንደኛ ዕጣ የሆነውን የ2020 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር መኪና ጨምሮ ዘመናዊ የውሃ ማጣሪያዎች ፣ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥኖችና ስማርት ስልኮች ለዕድለኞች ደርሰዋል፡፡
በስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የቡና ባንክ ቺፍ ስትራቴጂ መኮንን አቶ መንክር ሃይሉ እንደተናገሩት አንድ ሃገር በምጣኔ ሃብት ጎልብታ ዜጎቿን ተጠቃሚ ማድረግ የምትችለው ጤናማ የገንዘብ ዝውውር ስርዓት ማስፈን ስትችል ነው። የገንዘብ ዝውውር በኢኮኖሚው ውስጥ ገንቢ ሚና እየተወጣ እንዲቀጥል ለማድረግ ደግሞ ባንኮች የማይተካ ድርሻ አላቸው።
ቡና ኢንተርናሽናል ባንክም በየጊዜው በሚያካሂደው ጥናት ብዙሃኑን ህብረተሰብ ወደባንክ ስርዓት እንዲገባ፣ በዚህም የቁጠባ ባህሉን በማሳደግ ህይወቱን እንዲያሻሽል ለማስቻል የተለያዩ አገልግሎቶችን እየቀረጸ ለጥቅም ሲያውል ቆይቷል። በዚህም ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት ወደራዕዩ ስኬት የሚያደርገውን ግስጋሴ ቀጥሏል ብለዋል።
እንደ አቶ መንክር ገለፃ ወደሃገራችን ከሚመጣው የውጭ ገንዘብ ውስጥ አብዛኛው ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት ይልቅ በተለያየ ምክንያት ወደጥቁር ገበያ የሚገባ በመሆኑ ሃገሪቱ በተደጋጋሚ ጊዜ ለሚገጥማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንዱ ምክንያት ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል። የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንድ ሃገር ለሚያስፈልጋት ማናቸውም የንግድ ልውውጥ ተግባር ከፍተኛ እንቅፋት የሚፈጥር መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው ያሉት መኮንኑ በዚህም ሳቢያ የሚከሰት የገቢ ንግድ መቀዛቀዝ የሸቀጦች ዋጋ መጨመርን ብቻ ሳይሆን የአስፈላጊ ግብዓቶችን እጥረት በመፍጠር የኑሮ ውድነትን እንደሚያባብስና ዜጎችም በመሰረታዊ ግብዓቶች እጥረት ለችግር እንዲጋለጡ ምክንያት እንደሚሆን አብራርተዋል።
የውጭ ገንዘቦች ምንዛሪና መቀበል ሂደት በባንክ ብቻ እንዲተገበርና ከጥቁር ገበያ ተጽዕኖ እንዲላቀቅ ፣ በውጤቱም ሃገርና ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የበኩሉን ሃላፊነት ለመወጣት በተከታታይ ዙሮች ለውጭ ገንዘብ ተቀባዮችና መንዛሪዎች የማበረታቻ ሽልማት በማዘጋጀት የዘመቻ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ነው አቶ መንክር ያስታወቁት።
እስካሁን ባንኩ በስምንት ዙር ባካሄደው “የውጭ ገንዘብ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” መርሃ ግብር ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድርጉንና ወደጥቁር ገበያ የሚገባውን የውጭ ገንዘብ መጠን ለመቀነስ የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበርከቱንም አክለው ተናግርዋል።
እንደአቶ መንክር ገለጻ ቡና ባንክ ባለፉት ስምንት ዙሮች ባካሄደው የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ መርሀግብር ካገኛቸው ልምዶች በመነሳት የባንኩን ደንበኞች የበለጠ ለማበረታታትና ለማትጋት ዘጠነኛውን ዙር የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ ፕሮሞሽን መርሃግብሩን በቅርቡ ይጀምራል፡፡