ቡና ባንክ ለመምህራንና ለጤና ባለሙያዎች አዲስ የቁጠባ አገልግሎት ይፋ አደረገ
- ለቁጠባ አገልግሎቱ ተሳታፊዎች ሽልማት ተዘጋጅቷል
ቡና ባንክ ለመምህራን እና ለጤና ባለሙያዎች አዲስ የቁጠባ ሽልማት መርሃ ግብር በይፋ ጀመረ።
በሁሉም ደረጃ ላይ የሚገኙ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች ተካፋይ በሚሆኑበት በዚህ አዲስ የቁጠባ መርሃ ግብር ላይ ለሚሳተፉ ደንበኞቹ ባንኩ የተለያዩ ሽልማቶችንም አዘጋጅቷል።
ሃገር ጤናማ ስርዓት ገንብታ ወደዕድገት የምታመራው አንድም በዕውቀት የታነጸ ፣ በሌላ በኩልም ጤናው የተጠበቀ ትውልድ ሲኖራት ነው። ትውልድን በእውቀት የማነጽ እና የህዝብን ጤና የመጠበቅን ከባድ ሃላፊነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚሸከሙ ምሰሶዎች ደግሞ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች መሆናቸውን ቡና ባንክ ያምናል።
ብዙ ነገር ባልተመቻቸበት ፣ አድካሚ በሆነ ነገር ግን ቁርጠኝነትን በሚጠይቅ ስፍራ ሁሉ ተገኝተው ትውልድንና ሃገርን ለማስቀጠል የሚተጉት እነዚህ የሃገር ባለውለታዎች አንድም የቁጠባ ባህላቸውን እያሳደጉ የባንኩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፣ በሌላ በኩልም በመቆጠባቸው ብቻ ተሸላሚ መሆን የሚችሉበት መርሃ ግብር ነው የተዘጋጀው።
በዚህ የቁጠባ አገልግሎት ላይ ለመሳተፍ ማናቸውም በመምህርነት ሙያ ላይ የተሰማሩና ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ የሚያገለግሉ መምህራን ፣ እንዲሁም በትምህርት አስተዳደርና ድጋፍ ስራዎች ላይ የሚገኙ ሁሉ ብቁ ናቸው።
በተመሳሳይም በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ነርሶች፣ የጤና መኮንኖችና ጤና ረዳቶች፣ የማህበረሰብ ጤና ባለሙያዎች፣ የህክምና ዶክተሮች፣ ራዲዮሎጂስቶች እንዲሁም ከህክምና ሙያ ጋር ተያያዠነት ያላቸው ስራዎችን የሚያከናውኑ እና በህክምና ተቋማት ውስጥ በድጋፍ ሰጪነት የሚያገለግሉ ባለሙያዎች ሁሉ የዚህ የቁጠባና ሽልማት መርሃ ግብር ተሳታፊ ለመሆን ብቁ ናቸው።
በቁጠባ አገልግሎቱ ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች ቁጠባውን እንደጀመሩ ተሸላሚ የሚያደርጋቸውን የዕጣ ቁጥር የሚቀበሉ ሲሆን ከ 400 ብር ጀምሮ መቆጠብ ለሽልማቱ ብቁ ያደርጋል። የባለሙያዎቹ የቁጠባ መጠን ባደገ ቁጥርም ዕድለኛ የሚያደርጋቸው ዕጣ ቁጥሮች መጠን በዚያው ልክ የሚያድግ ይሆናል።
ባንኩ በቀጣይ የሚያካሂደው ይኸው ይቆጥቡ ይሸለሙ ፕሮግራም ሲጠናቀቅ ያዘጋጃቸውን ሽልማቶች በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ድርጅት ውስጥ በይፋዊ ስነስርዓት ዕጣ በማውጣት አሸናፊዎቹን ያሳውቃል።
በዚህ መሰረት ለሽልማት የተዘጋጁት አንድ ዘመናዊ 2020 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር መኪና ፣ 12 ዘመናዊ ላፕቶፖችና 12 ታብሌቶች እንዲሁም 24 ስማርት የሞባይል ስልክ ቀፎዎች፣ ስድስት የእረፍት ጊዜ ሽርሽር ሙሉ ወጪ የተሸፈነላቸው የታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝት ፓኬጆች ለአሸናፊዎቹ ይተላለፋሉ።
ቡና ባንክ አ.ማ ከ11 ዓመታት በፊት የተቋቋመና ከ275 በላይ በደረሱ ቅርንጫፎቹ በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ የግል ባንክ ሲሆን ከ13ሺህ በላይ በሆኑ ባለአክሲዮኖች ባለቤትነት የሚተዳደርና በሃገሪቱ ከሚገኙ ባንኮች ውስጥ የብዙሃን ባንክ ተብሎ በመጠራት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ የግል ባንክ ነው።
ባንኩ ከ 1.1 ሚሊዮን በላይ ለደረሱ ደንበኞቹ ቀልጣፋ የባንክ አገልግሎት በመስጠትና በየጊዜው አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት በብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ተዓማኒነትን ያተረፈ ባንክ ሲሆን ከሚለይባቸው ተግባራት አንዱና ዋናው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያማከለ፣ ፍላጎትና አቅማቸውን ያገናዘበ የልዩ ቁጠባና ብድር አገልግሎቶችን ማመቻቸቱ እንዲሁም ዘመኑን የዋጁ የዲጂታል ቴክኖሎጆዎችን ለደንበኞቹ ቅርብ ማድረጉ ነው።
ከነዚህ መካከል ላለፉት ዓመታት ተግባራዊ ያደረገው የ ታክሲና ባጃጅ አሽከርካሪና ባለቤቶች ልዩ የቁጠባ ሂሳብ ተጠቃሹ ሲሆን ይህ ፕሮግራምም በርካታ ደንበኞችን በማፍራት የብዙሃኑን ህይወት መለወጥ ያስቻለ መሆኑ በደንበኞቹ ተመስክሮለታል።