ዓመታዊ የተሸከርካሪ ፈቃድ ማደሻ (ቦሎ) ክፍያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ሊፈፀም ነው
የኢትዮያ ንግድ ባንክ ዓመታዊ የተሸከርካሪ ፈቃድ ማደሻ ክፍያ ለመሰብሰብ ከመንገድ ፈንድ ጽ/ቤት ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡
በስምምነት ስነሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማእከላዊ ሪጂን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኪዳኔ መንገሻ እንዳሉት ስምምነቱ በሀገራችን የሚገኙ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተሸከርካሪዎች ባለቤቶችን የዘመናዊ ክፍያ አሠራር ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
ደንበኞች የክፍያ አገልግሎቱን በባንኩ ቅርንጫፎች፣ በፖስታ ቤት በሚገኙ የፖስ (POS) ማሽኖች እንዲሁም በኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት በኩል በፍጥነት ያለእንግልት ማግኘት ያስችላቸዋልም ነው ያሉት፡፡
አቶ ኪዳኔ እንዳሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 53 በመቶ የሚሆነውን አገልግሎቱን በዲጂታል ስርዓት አማካኝትት በመፈፀም ላይ እንደሚገኝ ገልፀው፣ ይህም የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በማስቀረት ህብረተሰቡን የዘመናዊ ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ የማድረግ ጥረት አካል ነው፡፡
በስምምነት ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የመንገድ ፈንድ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ራሺድ መሃመድ በበኩላቸው በዓመታዊ የተሸከርካሪ ፈቃድ ማደሻ ክፍያ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሰበሰብ ገልፀዋል፡፡ የክፍያ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መደረጉ ደንበኞችንም ጽ/ቤቱንም የተቀላጠፈ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
በተለይ ከዚህ በፊት ወደ መንገድ ፈንድ መግባት ያለበትን ገንዘብ ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ይፈፀም የነበረውን ማጭበርበር ያስቀራል፣ የጽ/ቤቱን የክፍያ መሰብሰብ አቅም ያሳድጋልም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሃና አራያሥላሴ በበኩላቸው በአዲሱ የክፍያ ስርዓት በባንኩ በቅርንጫፎች፣ ከፖስታ ቤት ቅርንጫፍ ጋር በተገናኘ የፖስ ማሽን እንዲሁም በኢንተርኔት ባንኪንግ አሠራር ክፍያቸውን የፈጸሙ ደንበኞች የሚያገኙትን የክፍያ ደረሰኝ እና የተሽከርካሪ ሊብሬያቸውን ለፖስታ ቤት በማቅረብ የክፍያ ማረጋገጫ ካገኙ በኋላ ለትራንስፖርት ባለሥልጣን በማሳየት ዓመታዊ ቦሎ መውሰድ ይቻሉ ብለዋል፡፡
ባንኩ ከዚህ በፊት ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት፣ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ እና ከሌሎች የመንግሥት እና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር የተለያዩ ክፍያዎች በባንኩ አገልግሎቶች እገዛ የሚፈጸሙበትን አሠራር ማመቻቸቱ ይታወቃል።(የኢት ንግድ ባንክ)