በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ሁለት ኮርፖሬሽኖች 257 ሚሊዮን ብር አተረፉ
በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ሥር ከሚገኙ 21 የልማት ድርጅቶች መካከል በኮንሥትራክሽ ዘርፍ የተሰማሩት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪው መንፈቅ ብር 300 ሚሊዮን ትርፍ ከታክስ በፊት ለማግኘት አቅደው ብር 257 ሚሊዮን በማግኘት የዕቅዳቸውን 86 በመቶ ማከናወናቸውን የካቲት 5 ቀን 2013 ዓ.ም በኤጀንሲው መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሔደ የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ታወቀ፡፡
ኮርፖሬሽኖቹ ይህን ትርፍ ሊያገኙ የቻሉት በኮንስትራክሽን፣ በዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች በግማሽ በጀት ዓመቱ ብር 2.4 ቢሊዮን ጠቅላላ ገቢ ለማግኘት አቅደው ብር 1.9 ቢሊዮን በማግኘት የዕቅዳቸውን 78 በመቶ ማከናወን በመቻላቸው ነው፡፡
ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በተለይም በአፍሪካ ሀገሮች በኮንስትራክሽን ገበያ ገብተው ለመሥራትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ኮርፖሬሽኖቹ ባደረጉት ጥረት የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በታንዛኒያ ፣ጅቡቲና ናይጄሪያ ገብቶ እየሠራ ሲሆን፣የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ደግሞ ጅቡቲ ሥራ ማግኘቱ በግምገማው ወቅት ተገልዷል፡፡
የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማውን የመሩት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሃብታሙ ኃ/ሚካኤል ሲሆኑ ፣የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች፣ የልማት ድርጅቶቹ ቦርድ እና የማኔጅመንት አመራሮች እንዲሁም ዘርፉን ሚከታተሉ የኤጀንሲው የሥራ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡ ግምገማውም ኦፕሬሽንን ፣ ፋይናንስን እና ፕሮጀክትን በተመለከተ በስድስት ወሩ የታቀዱ ግቦች አፈጻጸም እና በቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ተካሂዷል፡፡
በግምገማው ማጠቃለያ ላይ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር የኮርፖሬሽኖቹ ያለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸሞች የሚያበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ኮርፖሬሽኖቹ ያስመዘገቡትን ትርፋማነት በቀሪዎቹ የበጀት ዓመቱ ወራት አጠናክረው በመቀጠል ለዓመቱ የተያዙ ግቦችን እንዲያሳኩ አስገንዝበዋል፡፡
(በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ)