ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በቤንሻንጉል ት/ቤት አስገነቡ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ13 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ወጪ በቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት የተገነባ የኮምሽጋ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ፡፡
በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸዉ ትምህርት ቤቱ በተለያዩ ምክንያቶች ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት አቅርቦት የማያገኙ ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዉ ዜጎች በተለይም ሴቶች ከጓዳ ወጥተዉ ለወደፊት ህይወታቸዉ መሰረት የሚሆናቸዉን ትምህርት እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡
ለሁሉም ዓላማ መሳካት ሰላም ወሳኝ እና ቅድሚያ ሊሰጠዉ የሚገባ በመሆኑ የሰዉ ልጆች በፈጣሪ የተሰጣቸዉን ሰላም በጋራ ሊጠብቁና ሊያስጠብቁ እንደሚገባም ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸዉ ተናግረዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ትምህርት የማንኛዉም ልማትና ብልጽግና ማሳለጫ ዋና መሳሪያ መሆኑን በማስታወስ ይህንንም ተረድቶ የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በክልሉ ላስገነባዉ ደረጃዉን የጠበቀ ትምህርት ቤት የላቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ መገንባት አንድም በቀደሙት ጊዜያት ትኩረት ተነፍጎት የቆየዉን የክልሉን የመልማትና የመሰረተ ልማት ጥያቄ የመለሰና እንደ ሀገር እኩል የመልማት እድል ያስገኘ በሌላ በኩል ደግሞ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸዉ እቅድ መሰረት በአጭር ጊዜ ዉስጥ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ተሞክሮ የተገኘበት ነዉ ብለዋል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ በበኩላቸዉ የትምህርት ቤቱ መገንባት በርካታ አቅመ ደካሞችና ሴቶች ትምህርት ቤት በአቅራቢቸዉ ባለመኖሩ ይደርስባቸዉ የነበረዉን እንግልትና ትምህርት የማቋረጥ ችግር መፍሄ እንደሚሆን ጠቅሰዉ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ከመፍታም ባሻገር ደረጃዉን የጠበቀ ትምህርት ቤት ገንብቶ ለትዉልዱ ላስረከበላቸዉ የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት የላቀ ክብርና ምስጋና እዳላቸዉ ገልጸዋል፡፡
የነባር ከምሽጋ ቀበሌና አካባበቢዉ ነዋሪዎችም ቀደም ሲል ልጆቻቸዉ ትምህርት ለማግኘት ረጅም ሰዓታት በእግር እንደሚጓዙ እና በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ ትምህርታቸዉን ለማቋረጥ እንደሚገደዱ ገልፀዉ የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት ይህንን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በማድረጉ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በቀበሌዉ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎችም የትምህርት ቤቱ መገንባት ከወላጆቻቸዉ ጋር ሆነዉ በቅርበት ትምህርታቸዉን እንዲከታተሉ እድል የፈጠረላቸዉ በመሆኑ በእጅጉ መደሰታቸዉን ተናግረዋል፡፡
በክብርት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸዉ በይፋ ተመርቆ የተከፈተዉ የኮምሽጋ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1 ሺህ 6መቶ በላይ ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም ያለዉና የአስተዳደር ህንጻን ጨምሮ የቤተ-ሙከራና ሌሎችም መሰረታዊ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ደረጃዉን የጠበቀ ግንባታ መሆኑን በመርሃ-ግብሩ ላይ ተመላክቷል፡፡
የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 20 የሚሆኑ ደረጃቸዉን የጠበቁ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እያስገነባ ሲሆን ከነዚህም መካከል ግንባታቸዉ ተጠናቀዉ ለምርቃት ከበቁት 10ኛዉ የኮምሽጋ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን ቀሪዎችም በቀጣይ ወደ ስራ እንደሚገቡ ከጽ/ቤቱ የተገኘዉ መረጃ ያመላክታል፡፡
(ኤፍ ቢ ሲ)