የኦነግ አቤቱታ፡- “ዋና ፅ/ቤታችን ያለአንዳች የፍርድ ቤት ማዛዣ እና ህገወጥ በሆነ አካል ጋባዥነት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋል ሁኔታውን ተራ የህግ ጥሰት ብቻ ሳይሆን የድርጅቱን ህልውና የሚፈታተን ሆኖ አግኝተነዋል።…”
(ኦነግ ለምርጫ ቦርድ የላከው አቤቱታ እነሆ)
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፅ/ቤት
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፦ የድርጅታችንን ማዕከላዊ ፅ/ቤትን ይመለከተል።
ድርጅታችን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር/ኦነግ/ ሰላማዊውን የትግል መስመር መርጦ፣ አመራሩ ወደ ሀገር ከተመለሰበት ቀን አንስቶ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት የሚጠበቅበት ሁሉ አሟልቶ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመመዝገብ ሰላማዊ እና ህጋዊ የፖለቲካ ትግል ሲያካሄድ እንደ ነበረ የሚታወቅ ነው።
በኣዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 76(1) መሰረት፣ አንድ በምርጫ ቦርድ የተመዘገበ ብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲ በመለው ሀገሪቱ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶችን ከፍቶ በሰላም እና በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ያለው መሆኑን እና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በማቋቋሚያ አዋጅ 1133/2011 አንቀጽ 7(3 እና 9) መሰረት የፖለቲካ ፓርቲ መመዝገብ፣በህጉ መሰረት መከታተልና መቆጣጠር፣ እንዲሁም በየጊዜው ለሚካሄድ ምርጫ ላይ ፓርቲዎች በነፃነት እና ፍትሃዊነት የሚሳተፉበትን ሁኔታን የማመቻቸትና የማረጋገጥ ሀላፊነት እንዳለበት በግልፅ ተደንግጓል።
በተጨማሪም በአዋጅ 1133/2011 ኣንቀጽ 7(19) መሠረት ምርጫ ቦርድም ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች መርምሮ አስቸኳይ መፍትሔ/ውሳኔ/ መስጠት እንደሚኖርበት ተቀምጧል።
ሆኖም ግን፣ በድርጅታችን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ላይ በተለያዩ ጊዜያት ከላይ የተጠቀሰውን የፖለቲካ ፓርቲዎችን መሠረታዊ መብት በጣሰ ሁኔታ በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች የሚደርሱትን መጠነ ሰፊ የህግ ጥሰቶች በተመለከተ በርካታ አቤቱታዎችን ስናቀርብ የነበረ ቢሆንም፣እስከ ዛሬ ድረስ የተሰጠን መፍትሄ አልነበረም።
ከእነዚህም አቤቱታዎች መካከል እንደ አጠቃላይ፣ የቅርጫፍ ፅ/ቤቶቻችን በየቦታው በፀጥታ ሀይሎች መዘጋት በተለይም ደግሞ፣ የማዕከላዊ ፅ/ቤታችን ከሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋልን የተመለከተው አቤቱታ አንዱ እንደነበረም ይተወሳል። ማዕከላዊ ፅ/ቤታችን በህገወጥ ሁኔታ በፖሊስ ከተያዘበት እና የድርጅቱን ሊቀመንበር ጨምሮ አብዛኛው የድርጅቱ የስራ ሀላፊዎች በፖሊስ ሀይል ከፅ/ቤቱ ከወጡበት ጀምሮ ወደ ድርጅታችን ዋና ፅ/ቤት ቅጥር ግቢ እንዳንገባ ግቢውን እንዲጠብቁት በቋምነት በተመደቡት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የፖሊስ አባላት ስለተከለከልን፣ በፓርቲያችን ዕለታዊ ድርጅታዊ ሥራዎች ላይ ከባድ ተፅዕኖ አሳድሮብናል፣በነፃነት የመንቀሳቀስና በየቦታው ቢሮ ከፍተን ህዝባችንን የማደራጀት፣ ለምርጫ ተወዳዳሪ እጩዎችን የመመልመል ስራዎችን ኣደናቅፎብናል።
ይህም የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመንቀሳቀስ መብት እና ነፃነት የሚጋፋ ህገወጥ ተግባር ብቻ ሳይሆን የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ የግንባታ ሂደትን የሚያደናቅፍ እና የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያጠብ በጣም አደገኛ ፀረ ዴሞክራሲያዊ መንግስታዊ ወንጀል ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህም ድርጊት ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ በተቃረበበት ወቅት ላይ መፈፀሙ ደግሞ፣ ድርጅታችንን በዚህ ሀገራዊ ምርጫ ላይ እንዳይሳተፍ ለማደናቀፍ፣ ብሎም ከሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ውጭ ለማድረግ በገዥው ፓርቲው ሆነ ተብለው ታቅዶበት እያተሰራ ያለው ህገወጥ ተግባር መሆኑ እየታወቀ እና እኛም በተደጋጋሚ አቤቱታ እያቀረብን፣ ቦርዱ ላለፉት አምስት ወራት ለዚህ አቤቱታችን ምንም መፍትሄ አለመስጠቱ አሳዝኖነል፤ የቦርዱንም ገለልተኛነት እና የማስፈፀም አቅም እንድንጠራጠር አስገድዶናል።
በዚህ ላይ፣ ለስድስተኛ ሀገራዊ አጠቃላይ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶ ድምፅ መስጫ ቀን አራት ወራት ብቻ በቀሩበት ወቅት፣ የዕጩ ምዝገባና የምርጫ ቅስቀሳ ሊጀመር አንድ ወር ብቻ በቀረበት ሁኔታ እና ከሶስት ሣምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገን በህገ ደንባችን ላይ የተሰጡትን ማስተካከያዎች አካተን ህገደንቡን ማሻሻል በሚጠበቅብን ሰዓት ላይ፣ ዋና ፅ/ቤታችን ያለአንዳች የፍርድ ቤት ማዛዣ እና ህገወጥ በሆነ አካል ገባዥነት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋል ሁኔታውን ተራ የህግ ጥሰት ብቻ ሳይሆን የድርጅቱን ህልውና የሚፈታተን ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህንንም ህገወጥ ተግባር የማረሙ እና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ እንቅስቃሴ ምቹ ከባቢን የማመቻቸቱ ተግባር በዋናነት የምርጫ ቦርድ ሀላፊነት ሆኖ ሳለ፣ ቦርዱ ከዚህ ረገድ ለድርጅታችን አቤቱታ ምንም ዓይነት የመፍትሄ እርምጃ ሲወስድ አላየንም።
በመሆኑም፣ ብሔራዊ ምርጫ፣ቦርድ ያለህግ የተወራራውን የድርጅታችን ማዕከላዊ ፅ/ቤት በአስቸኳይ እንዲያስለቅቅልን እና በነፃ የመንቀሳቀስ መብታችንን እንዲያረጋግጥልን በአፅንዖት እየጠየቅን፣የዋና ፅ/ቤታችን ሁኔታ መፍትሔ ሳያገኝ እና በሃገሪቱ ውስጥ የትም ቦ ታፅ/ቤት እንዳይኖረን በተደረገበት ሁኔታ፣ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግም ሆነ የምርጫ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት አዳጋች ሁኔታዎች ከፊታችን ላይ ሆንተብለው እየተጋረጡብን መሆኑ ታውቆ፣በዚህም ምክንያት ድርጅታችን ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ተፅዕኖና መገፋት ሀላፊነቱን የሚወስዱት ፅ/ቤቶቻችንን በየቦታው በፀጥታ ሀይሎች አጉሮ በነፃ የመንቀሳቀስ መብታችንን የነፈገው መንግስት እና ይህንን ሁኔታ በወቅቱ እንዲታረም መፍትሔ መስጠት ያልቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑን ከወድሁ ለማስገንዘብ እንወዳለን።
ድል ለሰፊው ህዝብ!
ዳውድ ኢብሳ አያና
የኦነግ ሊቀመንበር