Connect with us

የጥምቀት በዓል የኮሮናን መከላከያ መንገዶች በመከተል ይከበራል

የጥምቀት በዓል የኮሮናን መከላከያ መንገዶች በመከተል ይከበራል
ኢኦተቤ ህዝብ ግንኙነት

ዜና

የጥምቀት በዓል የኮሮናን መከላከያ መንገዶች በመከተል ይከበራል

የጥምቀት በዓል የኮሮናን መከላከያ መንገዶች በመከተል ይከበራል

የከተራና የጥምቀት በዓላት የኮቪድ-19 መከላከያ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር እንደሚከበር ብጹዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ ገለጡ።

የከተራና የጥምቀት በዓላት በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ጥር 10 እና 11 ቀን ይከበራሉ።

ጥምቀት ጌታችን ፣መድሀኒታችን ፣ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ተጉዞ በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ የተጠመቀበትን ዕለት በማሰብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሀዶ ቤተክርስቲያን  ዘንድ በየዓመቱ የሚከበ የአደባባይ በዓል መሆኑ ይታወቃል ።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዕምነት ተከታዮች በዓሉን ከዋዜማው ከተራ ጀምሮ በተለያዩ ኃይማኖታዊና ባሕላዊ ስነ-ስርዓቶች ያከብሩታል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ  የከተራና የጥምቀት በዓላትን ለማክበር እየተደረገ ስላለው ዝግጅትና ኮቪድ-19ን ለመከላከል መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ለህዝበ ክርስቲያኑ መልዕክት አስተላልፈዋል ።

የ2013ዓ.ም የጥምቀት በዓል የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መወሰድ ያለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተግባራዊ በማድረግ ለራስና ለሰዎች ጤና በመጠንቀቅ ጭምር የሚከበር ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ አካላዊ ጥግግትን ለመቀነስ ፒያሳ የነበረውን የአትክልት ተራ ግብይት ወደ ጃንሜዳ አዛውሮት እንደነበር ያስታወሱት ብጹዕነታቸው፤

የከተማ አስተዳደሩ የጥምቀት በዓል ከመድረሱ በፊት ጃንሜዳን አጽድቶ እንደሚያስረክብ ቀደም ሲል የገባውን ቃል አክብሮ ከበዓሉ  አንድ ወር በፊት ጃንሜዳን አጽድቶ ለቤተክርስቲያኒቱ በማስረከቡ የተሰማቸውን ደስታና ምስጋና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በራሳቸው ስም ገልፀው ፤ በአሁኑ ጊዜ ቤተክርስቲያኒቱ ጃንሜዳን የበለጠ የማጽዳት እና በዓሉን በሚመጥን ደረጃ የማስዋብ ሥራ በተረኛው ደብርና በቤተክርስቲያኒቱ በተደራጁ ወጣት ልጆቿ አማካኝነት እያከናወነች መሆኑን ገልፀዋል።

የተረኛውን ደብር ጨምሮ በጃንሜዳ ታቦታትን የሚያወጡ ገዳማትና አድባራትም የከተራና የጥምቀት በዓላትን በደመቀ ሁኔታ ማክበር ይቻሉ ዘንድ በሊቃውንትና በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ዘንድ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በዓሉ ሠላማዊ ሆኖ እንዲከበር ቤተክርስቲያኗ ከፌደራል ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና  ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋራ በመሆን አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማከናወኗን  የገለጹት ብጹዕነታቸው በበዓሉ ወቅት ህዝበ ክርስቲያኑ በፍተሻ መተባበርና አጠራጣሪ የሆኑ ፤ ሰላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን ሁሉ በጥንቃቄ  ከመከታተል ባለፈ አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥመው ለፖሊስ በመጠቆም በዓላችንን  ያለምንም የጸጥታ ችግር ለማክበር  የሚደረገውን ጥረት በተግባር በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አደራ ብለዋል።

ህዝበ ክርስቲያኑ  በዓሉን ሲያከብር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ የቅድመ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሁሉ መተግበርና  በዓሉ ሠላማዊ በሆነ መልኩ ተከብሮ መዋል እንዲችል የበኩሉን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበት አሳስበው  ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ለማድመቅ የሚጠቀምባቸው አልባሳት እና የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች ሃይማኖታዊና የማንንም መብት የማይነኩ መሆን እንደሚገባቸው ገልጸዋል ።

   አያይዘውም በዓሉን ለማክበር የሚወጣው ህዝብ ህጋዊውን የፌዴራል መንግስት ሰንደቅዓላማ እና ቤተክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ያጸደቀችውን በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ላይ ያረፈውን ህጋዊ የቤተክርስቲያኒቱ አርማ ብቻ ይዞ በመውጣት በዓሉን ማክበር ይኖርበታል ብለዋል።

በከተራና በጥምቀት በዓላት ላይ ብጹአን ወቅዱሳን ፓትርያርኮቻችን፣ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ዲፕሎማቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ቱሪስቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ብጹዕነታቸው ጠቁመዋል።

ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሠላም፣ የጤ፣የደስታና የበረከት እንዲሆን ተመኝተዋል።(ኢኦተቤ ህዝብ ግንኙነት)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top