እነ አቶ ጃዋር መሃመድ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ
ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ማግስት በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ሁከት በማነሳሳት ወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች እና በፖለቲከኛ ጃዋር መሃመድ ስም በተከፈተው መዝገብ ስር የተጠቀሱት ተከሳሾች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
ባለፉት አራት ተከታታይ የችሎት ቀጠሮ ላይ ሳይቀርቡ የቀሩት አቶ ጃዋር መሃመድ እና አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም በሁለትና ሶስት ችሎቶች ላይ ያልቀረቡት አቶ ሃምዛ አዳኔ እና አቶ ሸምሰዲን ጠሃን ጨምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ሁሉም ተከሳሾች ዛሬ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ታህሳስ 08 ቀን 2013 በዋለው ችሎት የተከሳሾቹ “ልዩ ችሎት” በማረሚያ ቤት አቅራቢያ የይቋቋምልን ጥያቄን ውድቅ ያደረገው ፍርድ ቤቱ በእለቱ በተከሳሾች ጠበቆች አማካኝነት ባደረሳቸው ትዕዛዝ ለዛሬው ችሎት “በኃይልም” ቢሆን እንዲቀርቡ የሚል ነበር፡፡
ይህንኑን በማስመልከት በዛሬው የችሎት ውሎ ላይ በእለቱ ለተሰየሙት ዳኞች ማብራሪያ የሰጡት የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ “ባለፉት የችሎት ቀጠሮዎች አራታችን ያልቀረብነው አገሪቱ ቀውስ ውስጥ የነበረች በመሆኑ ለደህንነታችን በመስጋታችን እና አስቀድመንም ማመልከቻ አስገብተን ነው” ብለዋል፡፡
በጠበቆቻቸው በኩል የደረሳቸው ትዕዛዝ “በኃይልም” ቢሆን እንዲቀርቡ የሚያዝ መሆኑን ለችሎቱ ያስታወሱት አቶ በቀለ ገርባ በዚሁ ንግግራቸው ከችሎቱ ሲቀሩ የነበረበት አግባብ ከቃሊቲው ማረሚያ ቤት ወደ ልደታ ፍርድ ቤት የችሎቱ ስፍራ ሲመላለሱ በደህንነታቸው ላይ የሚጋረጥ አደጋ ቢፈጠር “አገርንም ሌላ ቀውስ ውስጥ የሚያስገባት መሆኑን አስቀድመን በመገንዘብ እንጂ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ባለማክበር አይደለም” ነው ያሉት፡፡ ችሎቱ እና መንግስት ምንም አይነት አደጋ ላይደርስብን ኃላፊነቱን ሊወስዱ ይገባል፤ ወስደዋልም ብለን በማመናችን ነው በዚህ ችሎት ላይ ዛሬ የቀረብነው” ብለዋል፡፡
የኦፌኮ አመራር አቶ ጃዋር መሃመድ በበኩላቸው “እኛ ለህግ መከበር የታገልን በመሆኑ ህግ እናከብራለን፤ በወቅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተከፍቶ አገሪቱ ቀውስ ውስጥ የገባችበት ወቅት መሆኑና እኛም የተከሰስንበት አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት የሚል ክስ ስለሚገኝበት ሃገራችን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ለደህንነታችን ስጋት ገብቶን በችሎት ላይ ሳንታደም ቀርተናል” ብለዋል፡፡ ፖለቲከኛ ጃዋር መሃመድ አክለው ለችሎቱ ባቀረቡት ሃሳብ “ወደፊትም ጥቃት ቢፈጸምብን በሸነ አሊያም ሌላ ቡድን ነው በሚል ማሳበብ እንደ ማይገባና ጥቃት ቢፈፀምብን መንግስት እና ይህ ችሎት ተጠያቂነቱን እንደሚወስዱ ህዝብና ችሎቱ ላይ የታደሙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንዲገነዘቡልን እንፈልጋለን” በማለትም ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
የተከሳሾችን የቃል ማመልከቻ የሰሙት በእለቱ ችሎት የተሰየሙ ዳኛ የቀረበውን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ይረደዋል ብለዋል፡፡ “የተከሰሱ ማንም ሰው የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አያከብሩም ብለን አናምንም፤ ትዕዛዙንም ስንሰጥ በዚሁ በመተማመን ነው” ብለዋል፡፡ ተከሳሾች ተገደውም ቢሆን ለዛሬው ችሎት ይቅረቡ የሚል ትዕዛዝ የተላለፈውም ጉዳዩ እንዳይጓተት በማሰብ የቀረበ አማራጭ ሃሳብ ነው ያሉት የእለቱ ዋና ዳኛ ተከሳሾች ያቀረቡትን አቤቱታ በመንተራስ የችሎት ቁጥጥር እና ክትትል እንዲመቻች እናደርጋለን ብለዋል፡፡ “በችሎቱ እምነት እስካሁን የሚጎድል የለም” ያሉት ዳኛው በችሎቱ አመራሮችና በተከሳሾች በኩል ክፍተቶች ካሉም እያረምን እንሄዳለን በማለት ለጥያቄዎቹ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዛሬው ችሎት የተነበበው ብይን የጉዳዩ በፌዴራል ፍርድ ቤት መታየት አግባብነትን በህገመንግስቱ እና ሌሎችም አዋጆች በማጣቀስ ያስረዳ ሲሆን አቃቤህግ ባቀረበው ክስ ላይ ውድቅ የተደረጉ እና ተቀባይነት ያገኙ የተከሳሾች ጠበቃ የመቃወሚያ ሃሳቦችም በዝርዝር ቀርበዋል፡፡
ግልጽነት የሚጎድላቸው እና ማብራሪያ የሚያሻቸው የዐቃቤህግ የክስ ሃረጎችም በተብራራ መልኩ እና በማያሻሙ ቃላት ተደግፈው እንደገና ተስተካክለው እንዲቀርቡለት ችሎቱ ለአቃቤህግ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
የጠቅላይ ዐቃቤህግ ተወካይም እንዲሻሻሉ የተባሉትን የክስ አንቀፆች አስተካክለው እንደሚያቀርቡ በመግለጽ፤ ነገር ግን ክሱን ያዘጋጁ የተቋሙ ባለሙያዎች የመስክ ስምሪት ላይ በመሆናቸው የአንድ ወር የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡
የተከሳሾች ጠበቆች በፊናቸው ከቀረቡት የክስ መቃወሚያዎች ጥቂት ብቻ ተቀባይነት ማግኘቱ እንዳስከፋቸው አመልክተው፤ በዐቃቤህግ የተጠየቀው የአንድ ወር የቀጠሮ ጊዜ የሚረዝም፤ ፍትህን የሚያጓትት፣ የህግ የበላይነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ በመሆኑ፤ በተቋም የሚዘጋጅ ክስ ባለሙያዎች መስክ ናቸው በሚል ሊሳበብ እንደማይገባ አንስተው ተከራክረዋል፡፡ የክስ ሂደቱ በተራዘመ ቁጥር ደንበኞቻቸው እንደሚጉላሉ ያነሱት የተከሳሾች ጠበቆች እስራቱም አስተዳደራዊ እስራት እንዳይመስል የአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ ክሱን አስተካክለው ለማምጣት በቂ ነው ሲሉም ሞግተዋል፡፡
ከተከሳሾች በክሱ ላይ የቃል ክርክር ያሰሙት አቶ ሃምዛ አዳነ “መንግስት እኛን ያሰረው ወንጀል ሰርተን ሳይሆን ከምርጫ ጨዋታ ሊያገለን ነው” ብለዋል፡፡ “እስራታችን የፖለቲካ” ነው ያሉት አቶ ሃምዛ የፍርድ ሂደቱ ተቀላጥፎላቸው ወደ ቀጣዩ ምርጫ መሄድ እንዲቻል ፍርድ ቤቱ ጉልህ ሚናውን ሊጫወት ይገባል በማለት ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የፍርድ ቤት እና የፖሊስ ተቋማት ገለልተኝነት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አበርክቶው የጎላ መሆኑን ለችሎቱ ያስረዱት ሌላኛው ተከሳሽ የኦፌኮ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸው ቀጣዩ ምርጫ ለኢትዮጵያ ሰላምና ለዜጎቿ ወንድማማችነት ያለው ወሳኝነት ከፍተኛ በመሆኑ የፍርድ ሂደቱ እንዲቀላጠፍላቸው ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡ አቶ ደጀነ ችሎቱ መገናኛ ብዙሃን ከወገንተኝነት ፀድተው ትክክለኛ ዘገባ እንዲያቀርቡም ያሳስብልን ባሉት መሰረት መገናኛ ብዙሃን የችሎቱን ውሎ ብቻ ነው መዘገብ ያለባቸው ብሏል ችሎቱ፡፡
የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው የእለቱ ችሎትም የፍርድ ሂደቱን ለማቀላጠፍ ሲባል በአስር ቀናት ውስጥ ዐቃቤህግ የክስ ማስተካከያውን አጠኖቆ ይቅረብ በማለት ለጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን የአዲስ አበባ ወኪላችን ስዩም ጌቱ ያደረሰን ዘገባ ያስረዳል፡፡
በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ማግስት በቁጥጥር ስር የዋሉት እነ አቶ ጃዋር መሃመድ እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 24 ተከሳሾች በ1996 የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 240ን በመተላላፍ ብሔር እና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ግጭት ቀስቅሰዋል በሚል እና በሌሎች የሽብር ወንጀል በዐቃቤ ህግ ክስ እንደመሰረተባቸው ይታወሳል፡፡(የጀርመን ድምፅ)