ብልጽግና እና ህወሓት ምንና ምን ናቸው?
(እሱባለው ካሳ)
የህወሓት ጎምቱዎች ተያዙ፣ ተደመሰሱ የሚለው ዜና ብዙዎችን አስደስቷል፡፡ እንደህወሓት ያለ የሕዝብ ጠላት መደምሰስ ማስደሰቱ ክፋት አልነበረውም፡፡ ግን ያልተመደሰሱ የህወሓት ራዕይ አራማጆች፣ በምግባርም በመልክም የህወሓት ልጆችን በጉያ ይዞ ብዙ መናገር በከንቱ ጉንጭን ማልፋት ነው፡፡
ህወሓቶች ለምን በሕዝብ ተጠሉ? በአጭሩ ከሕዝቡ ፍላጎትና አስተሳሰብ ተቃርነው በመቆማቸው ነው፡፡ “እንመራሃለን” የሚሉት ሕዝብ ጠላት ሆነው በመታየታቸው ነው፡፡ በጥጋብ መንፈስ ውስጥ ሆነው ጭቁኑን ሕዝብ አብዝተው በመናቃቸው ነው፡፡
የሕዝቡን አንድነት ይፈራሉ፡፡ እናም ሕዝቡን በዘርና በጎሳ ከፋፍለው እንዳይተማመን አደረጉት፡፡ አንድ ብሔር ለይተው “ነፍጠኛ”፣ “ጨቋኝ ገዥ መደብ” እያሉ ሲያጥላሉት፣ ከሌሎች ጋር ሲያባሉት ኖሩ፡፡
የአይን ቀለሙ ያላማረቸውን ሁሉ በጠላትነት መፈረጅና ማሳደድ የህወሓቶች ልዩ መለያ ነበር፡፡ በሃይማኖት ጉዳዮች ገብተው ሲፈተፍቱ ” ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ ናቸው፣ አንዱ በሌላው ጣልቃ አይገባም” ብለው የጻፉት ሕገመንግስት እንኳን አላገዳቸውም፡፡
ሌላው ቀርቶ በየዓመቱ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እያሉ ብዙ በጀት እየመደቡ የሚያከብሩት በዓል ከጭፈራ ያለፈ እርባና ያለው ቁምነገር ሳይታይበት ዓመታት የነጎዱት ታስቦበት ነው፡፡
አገዛዛቸውን በዘመድ አዝማድ፣ በትውውቅ፣ በዘርና በጎሳ ላይ መስርተው ሀገሪትዋን ከመጋጥ አልፈው ብዙሀኑን የበይ ተመልካች አደረጉት፡፡ ሙስናና ሌብነት መደበኛ ስራ አደረጉት፡፡ በስልጣን መባለግ መለያቸው ሆነ፡፡ የተቃወማቸውን ብቻ ሳይሆ ገና ለገና ሊቃመወን ይችላል ያሉትን ሁሉ እያጋዙ አሰሩ፡፡ አሳደዱ፡፡ አንዳንዱንም ገደሉ፣ በእስር ቤት ኢ ሰብኣዊ ግፍም ፈጸሙ፡፡
የፓርቲ ተለጣፊ የሆነና ኢንዶውመንት የሚባሉ ኩባንያዎችን ቀፍቅፈው ሕጋዊ ነጋዴውን ከጨዋታ ውጪ አደረጉት፡፡ ኩባንያዎቹ ከፍተኛ ትርፍ የሚዝቁ ቢሆኑም ገንዘቡ የትና ለምን አላማ እንደሚውል የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በአግባቡ ኦዲት ተደርገው ስለማወቃቸውም አይታወቅም፡፡
ዛሬስ? ምን አዲስ ነገር አለ? ከኢህአዴግ የተፋታው ብልጽግና የቀድሞ የህወሓት/ኢህአዴግ መስመር የቱን ያህል ተላቋል? የዜጎች መብት እየተከበረ ነው ወይ? ዜጎች በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ብቻ የመሳደዳቸው፣ለእስር የመጋዛቸው ጉዳይ የተዘጋ ፋይል ሆኗል ወይ? ስራ ለመያዝ፣ የተሻለ መንግስታዊ አገልግሎት ለማግኘት ትላንት ትልቅ መስፈርት የነበረው የዘር ካርድ ዛሬ ማስቀረት ተችሏል ወይ?
የዜጎች የእምነት ነጻነት፣ ሃይማኖታዊ ክብረበዓላቸውን በመረጡት አካባቢ በሰላም የማክበር መብታቸው ተረጋግጧል ወይ? ዜጎች በመረጡት አካባቢ ሀብት የማፍራት፣ የመኖር፣ የመንቀሳቀስ መብታቸው የተከበረ ነው ወይ?
በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች የሚገኙ ኢንዶውመንት ድርጅቶች የት ነው ያሉት? ምን እየሰሩ ነው? ከበፊቱ ምን የተለየ አካሄድ ይዘዋል?
መንግስታዊ ሙስናው፣ ከገቢ በላይ ሐብት አፍርቶ በአደባባይ እዩኝ፣ እዩኝ ማለቱ፣መንጎማለሉ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
የብልጽግና ፖለቲከኞች ከህወሓት በተለየ ምን እየሰሩ ነው? ሕዝብን ወይንም አንድ ብሔርና ቡድን እንደህወሓት “ነፍጠኛ”… መፈረጅ፣ ማሸማቀቅና ጥላቻ ማቀጣጠል ታርሟል ወይ? ሰዎች በገዛ ሀገራቸው መርጠው ባልተወለዱበት ብሔር እንደጠላት ታይተው ለጥቃት የሚጋለጡበት አሳፋሪ ክስተት በአስተማማኝ መልኩ ማስቆም ተችሏል ወይ? አጥፊዎችን በፍጥነት ለይቶ ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ዜጎችን በሚያሳምን መልኩ መተግበር ተችሏል ወይ?
የብልጽግና ሰዎች ለእነዚህና መሰል ጥያቄዎች ጥርት ያለ መልስ በመስጠት ውስጣቸውን ከህወሓት ራዕይ አስፈጻሚዎችና የህወሓት ቫይረስ ተሸካሚዎች ማጽዳት ካልቻሉ አሁንም ሀገራችን በእጅ አዙር በህወሓት የሙት መንፈስ መመራትዋ አይቀሬ ይሆናል፡፡