Connect with us

የአቶ ዮሐንስ ቧያለው ለፍርድ ቤት የሰጡት የምስክርነት ቃል

የአቶ ዮሐንስ ቧያለው ለፍርድ ቤት የሰጡት የምስክርነት ቃል
Photo: Social media

ዜና

የአቶ ዮሐንስ ቧያለው ለፍርድ ቤት የሰጡት የምስክርነት ቃል

የአቶ ዮሐንስ ቧያለው ለፍርድ ቤት የሰጡት የምስክርነት ቃል

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ባለስልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ በነመማር ጌትነት መዝገብ ስር የሚገኙ ተከሳሾችን የአቃቤ ህግ ምስክሮች መሰማት ቀጥሏል፣ በእለቱ አንድ ሽጉጥ ያነጣጠረ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባል የነበሩበትን ክፍል በር በኃይል በርግዶ መግባቱን በወቅቱ ቦታው ላይ የነበሩ አንድ የአቃቤ ህግ ምስክር ዛሬ ለተሰየመው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎት አስረድተዋል። 

ከሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ አቃቤ ህግ ካቀረባቸው ምስክሮች መካከል በወቅቱ ከሟቾቹ ጋር በአንድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የነበሩት አቶ ዮሐንስ ቧያለው  አንዱ ናቸው፡፡ ዛሬ ባሕር ዳር ላይ ለተሰየመው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በምስክርነት ቀርበው ከግድያው በፊት ጀምሮ እስከ ሰኔ 15ቱ ያለውን ክስተት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ ለፍርድ ቤቱ እንዳሉት በወቅቱ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ የሰላም መደፍረስ እንደነበር፣ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለማስተካከል ከክልሉ የተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

ምስክሩ አያይዘውም ችግሩ ከመቀነስ ይልቅ እየተባባሰ በመሄዱ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ለማሻሻል፣ እንዲሁም በወቅቱ በአማራና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ትህነግ (ህወሓት ማለታቸው ነው) ሲያደርግ የነበረውን ትንኮሳ ለመከላከል ተጨማሪ ኃይል ማሰልጠን አስፈላጊ ስለነበር  ከነበረው መደበኛ የአማራ ክልለ ፖሊስ በተጨማሪ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እንዲሰለጥን መደረጉን ተናግረዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ኢ- መደበኛ የሆኑ አደረጃጀቶችም ሌላ የሰላም እንቅፋት በመሆን የክልሉን አመራር ማጣጣል፣ በከተሞች አካባቢ ንጥቂያና የሰላም መደፍረስ ሲታዩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

“የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአማራ ሚሊሺያ ጽ/ቤትና የሰላም ግንባታና ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ፣ የልዩ ኃይል ከፍተኛ አመራሮች ከወቅቱ የአማራ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (አዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ከሌሎች አካላት ጋር ብዙ ውይይቶች ቢደረጉም ውጤቱ አጥጋቢ አልነበረም” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ሰኔ 12 ቀን 2011 ዓ ም በአዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉበት የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ በሰፊው መገምገሙን አመልክተዋል፡፡ በተለይ የክልሉ  የሰላም ግንባታና ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ችግሮችን እንዲያስተካከልና እርምትም እንዲደረግ ሁሉም ስምምነት ያደረገበት ሁኔታ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ሰኔ 16/2011 ዓም አጠቃላይ በክልሉ ሰላምና ፀጥታ ላይ ያተኮረ ግምገማ ከአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች ከተውጣጡ የፀጥታ አካላት ጋር ግምገማና ውይይት ለማድረግ እቅድ ተይዞ አንደነበር ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ሰኔ 15/2011 የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ የአማራ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (አዴፓ) ጽ/ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ዮሐንስ ቧያለው ራሳቸውን ጨምሮ 7 የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት በስብሰባ ላይ እንዳሉ በግምት ከቀኑ 11 ሰዓት ሲሆን  አንድ አዲሱን የአማራ ክልል ልዩ ኃይል የደንብ ልብስ የለበሰና ሽጉጥ ያነጣጠረ ፖሊስ የተሰበሰቡበትን በር በኃይል ገፍቶ መግባቱን ዘርዝረዋል፡፡ 

በነገሩ የተደናገጡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ የርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ የነበሩት አቶ እዘዝ ዋሴና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ የነበሩት አቶ ምግባሩ ከበደ ወደ ቀጣዩ ክፍል ሲሄዱ ባለሽጉጡ ፖሊስ ተከታትሎ መግባቱንና ተከታታይ የጥይት ድምፅ ማሰማቱን አብራርተዋል፡፡

ከተኩሱ በኋላ ሌላ ክላሽንኮቭ የታጠቀ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባል እነ ዶ/ር አምባቸው ከገቡበት ክፍል ውስጥ ማየታቸውንም አቶ ዮሐንስ አስታውሰዋል፡፡  “ከደቂቃዎች በኋላ ከሞት የተረፍነው ወደ ተተኮሰበት ክፍል ስንሄድ አቶ እዘዝና ዶ/ር አምባቸው ህይወታቸው ማለፉንና አቶ ምግባሩ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ቆስሎ አገኘነው” በማለት አቶ ዮሐንስ ገልፀዋል፡፡

“ሶስቱ ተመርጠው እንዴት ተገደሉ?” ተብለው በተከሳሾች ጠበቃ የተጠየቁት አቶ ዮሐንስ “ምናልባት 4ቶቻችን ተቆርጠን ከመጀመሪያው ክፍል ስለቀረን፣ አሊያም ገዳዮቹ በሌሎቹ ላይ ከተኮሱና ከገደሉ በኋላ ደንግጠው፣ ወይም ሌላ የራሳቸው ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል፣ መልሱን ምናልባት ገዳዮቹ ራሳቸው ያውቁት ይሆናል፣ እግዚአብሔር ያልቆረጣት ነብስ ስለሆነች ተርፈናል” ብለዋል፡፡

በወቅቱ በርከት ያሉ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት በርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ እንደነበሩና አንዳንዶቹን በስምም ጭምር እየጠሩ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ ሁሉም የል ዩኃይል አባላት የዚህ ሥራ ተባባሪዎች እንዳልነበሩ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ ከዚያ ውስጥ ግን ለጥፋት የተሰለፉ ጥቂት ቡድኖች ነበሩ ሲሉ አመልክተዋል፡፡

በዛሬው ችሎት ከግድያው ጋር በተያያዘ ክስ ከተመሰረተባቸው 55 ተከሳሾች መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ካልቀረቡት ውጪ 47ቱ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡

ዘገባ ፤ DW – ዓለምነው መኮንን ከባህርዳር

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top